- ወንጀሉን ለመከላከል ግብረ ኃይል ተቋቁሟል
ከተለያዩ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች በኢትዮ ቴሌኮም ሳተላይት ኔትወርክ በኩል ማለፍ ሲገባቸው፣ ሕገወጥ የቴሌኮም መሣሪያዎች ያስገቡ ግለሰቦች ዓለም አቀፍ ጥሪዎቹን በመጥለፍ በራሳቸው መስመሮች ለደንበኞች እያቀረቡ እንደሆነ ታወቀ፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአብዛኛው ከውጭ አገሮች የሚደወሉ የስልክ ጥሪዎች በተለይ በሞባይል ስልኮች ላይ የሚወጡት፣ በአገር ውስጥ ሞባይል ቁጥር ነው፡፡ ከውጭ የሚደወሉ ጥሪዎችን ተቀብሎ ለደንበኞቹ የማቅረብ ሥልጣን ያለው ብቸኛው ኢትዮ ቴሌኮም ቢሆንም፣ ይህንን ሥራውን በግለሰቦች እየተቀማ እንደሆነ ታውቋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም ከውጭ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች ተቀብሎ ለደንበኞቹ ለሚያስተላልፍበት የአገልግሎት ክፍያ ከውጭ ቴሌኮም ኩባንያዎች ይፈጸምለታል፡፡ ይሁን እንጂ ግለሰቦች ቪሳት፣ ሲም ቦክስ፣ ራውተር የተባሉ መሣሪያዎች በድብቅ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ከውጭ አገሮች የሚደረጉ ጥሪዎች የኢትዮ ቴሌኮምን ኔትወርክ በመተላለፍ ጠልፈው ለደንበኞች በማቅረብ ላይ እንደሆኑ ታውቋል፡፡ ግለሰቦቹ ለሚሰጡት አገልግሎት ከውጭ ቴሌኮም ኩባንያዎች ክፍያ እንደሚሰበስቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ከሙዩኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም አህመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ግለሰቦቹ የውጭ ጥሪዎችን በመጥለፍ የሚሰጡት አገልግሎት ሕገወጥ ነው፡፡ ‹‹ሕገወጥ የቴሌኮም አገልግሎት መስጫ መሣሪያዎች ወደ አገር ውስጥ በድብቅ በማስገባት፣ በተለያዩ መንገዶች ከውጭ የሚደረጉ ጥሪዎች በመጥለፍ የሚፈጸም ድርጊት ሕገወጥ ነው፡፡ የቴሌኮም ማጭበርበር ነው፡፡ በሕግ የሚያስቀጣ ወንጀል ነው፤›› ብለዋል፡፡ ግለሰቦቹ በሕገወጥ መንገድ በሚሰጡት አገልግሎት ኢትዮ ቴሌኮምን ከፍተኛ ጥቅም እንዳሳጡት ተገልጿል፡፡
አቶ አብዱራሂም እንደሚሉት፣ የቴሌኮም ማጭበርበሩን ለመቆጣጠር በአገር አቀፍ ደረጃ ግብረ ኃይል ተቋቁማል፡፡ ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከኢንፎርሜሽን መረጃ መረብ ደኅንነት አገልግሎት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከደኅንነት መሥሪያ ቤት የተውጣጡ ባለሙያዎችን ያቀፈ ብሔራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ክትትል በማድረግ ላይ መሆኑን የገለጹት አቶ አብዱራሂም፣ በተካሄዱ የተለያዩ ኦፕሬሽኖች ውጤት መገኘቱን አስረድተዋል፡፡ ‹‹በሕገወጥ የቴሌኮም ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ የተለያዩ ሕገወጥ መሣሪያዎች ተይዘዋል፡፡ ግለሰቦቹም ለፍርድ እየቀረቡ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ደረጃቸውን ያልጠበቁ ተመሳስለው የተሠሩ የሞባይል ቀፎዎችን በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከአገልግሎት ውጪ እንደሚያደርግም ኢትዮ ቴሌኮም አስታውቋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮምና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም፣ የተንቀሳቃሽ ስልክ ቀፎዎችን ምዝገባ ለማከናወን የሚያስችል የአሠራር ሥርዓት በሥራ ላይ ማዋላቸውን አስታውቀዋል፡፡
የሁለቱ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ሐሙስ መስከረም 4 ቀን 2010 ዓ.ም. በጋራ በሒልተን ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ደንበኞች እየተጠቀሙባቸው የሚገኙ የሞባይል አገልግሎት መጠቀሚያ ቀፎዎች በሲስተም ላይ መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በደንበኞች እጅ የሚገኙና በተለያዩ ምክንያት እየተጠቀሙባቸው የማይገኙ ሞባይል፣ አይፓድና ሌሎች በሲም ካርድ የሚሠሩ የቴሌኮም መገልገያ መሣሪያዎች የኩባንያው ኔትወርክ ውስጥ ባለመመዝገባቸውና ኔትወርኩ ስለማያውቃቸው፣ ደንበኞች በእጃቸው ላይ የሚገኙና በተለያየ ምክንያት ጥቅም ላይ ያልዋሉ የቴሌኮም መሣሪያዎችን እስከ መስከረም 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲም ካርድ በማስገባት ከኢትዮ ቴሌኮም ኔትወርክ ጋር በማገናኘት ሲስተም ውስጥ እንዲያስገቡ አሳስበዋል፡፡
ኃላፊዎቹ ደረጃቸውን ያልጠበቁ የሞባይል ቀፎዎች በተገልጋዩ ኅብረተሰብ ጤና ላይ ችግር እንደሚፈጥሩና ኔትወርክ እንደሚያጨናንቁ ገልጸው፣ ተገልጋዮች እነዚህን ቀፎዎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማስወገድ እንደሚኖርባቸው አስታውቀዋል፡፡
አቶ አብዱራሂም የሞባይል ደንበኞች ቁጥር 58 ሚሊዮን መድረሱን ጠቁመው፣ 2.7 ሚሊዮን ቀፎዎች ደረጃቸውን ያልጠበቁ ተመሳስለው የተሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ደንበኞች “*#06” በመደወል በሞባይል ስልካቸው ዓለም አቀፍ ሞባይል መሣሪያ መለያ ቁጥራቸውን ማወቅ እንደሚችሉና *868#” በመደወል ቀፎዋቸውን ደረጃውን የጠበቀና በሕጋዊ መንገድ የተመዘገበ መሆን አለመሆኑን ማጣራት እንደሚችሉ ተነግሯል፡፡
የሞባይል ስልክ ምዝገባ በኬንያ፣ በአሜሪካና በአውሮፓ አገሮች የተለመደ ዘመናዊ አሠራር መሆኑን ገልጸው የሞባይል ኮንትሮባንድ ንግድና ስርቆትን ለመከላከል እንደሚረዳ አስታውቀዋል፡፡
የአገር ውስጥ የሞባይል ስልክ አምራቾች በኮንትሮባንድ ንግድ ክፉኛ እየተጎዱ እንደሆነና መንግሥት እነዚህን ኢንቨስትመንቶች የመታደግ ኃላፊነት አንዳለበት አስረድተዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት 60 በመቶ ምርታቸውን በመግዛት በድጎማ ለኅብረተሰቡ እንደሚያቀርብ አቶ አብዱራሂም ተናግረዋል፡፡ ‹‹በስድስት መቶ ብር የገዛነውን አገር ውስጥ የተመረተ የስልክ ቀፎ በ240 ብር ለተጠቃሚ ደንበኞች እያቀረብን ነው፤›› ብለዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በሚያካሂዳቸው መጠነ ሰፊ የቴሌኮም መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች፣ ከናይጄሪያው ኤምቲኤን ቀጥሎ አፍሪካ ውስጥ ሁለተኛው ግዙፍ የቴሌኮም ኩባንያ ለመሆን እንደበቃ ገልጸዋል፡፡
