የሰሊጥን አጠቃላይ የግብይት ሥርዓት ለመለወጥ ምክር ተጀምሯል
ከቡና ቀጥሎ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት የሚጠቀሰውን ሰሊጥ አጠቃላይ የግብይት ሥርዓት ለመለወጥ የሚያስችል አደረጃጀትና አሠራር ለመዘርጋት የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ምክር መጀመራቸው ታውቋል፡፡ የአገሪቱን ሰሊጥ ከምርት እስከ ወጪ ንግድ ድረስ ያለውን አጠቃላይ የግብይት ሒደት ለመለወጥ ታስቦ የተጀመረው እንቅስቃሴ ጉዳዩ በሚመለከታቸው መንግሥታዊ ተቋማትን ጨምሮ የአቅራቢዎችና ላኪዎች ማኅበራት የተወከሉበት ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተመከረበት ነው፡፡
በቅርቡ የቡናን አጠቃላይ የግብይት ሥርዓት ለመለወጥ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች ጋር ተመሳሳይ የሆነ አሠራር ለመዘርጋት ያስችላል የተባለ ጥናት ቀርቦ፣ በችግሮችና በመፍትሔ ሐሳቦች ላይ እየተመከረበት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዘርፉ የተሰማሩ ላኪዎች፣ አምራቾችና ሌሎች ተዋንያኖች የሰሊጥ የወጪ ንግድ ገበያ መቀዛቀዝና ከግብይት ሥርዓቱ ጋር ተያይዘው የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላትና ከዚህ በኋላ ግብይቱ እንዴት መሄድ አለበት የሚለውን የመፍትሔ ሐሳብ ይህ ኮሚቴ ይቀርፃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የሰሊጥ ምርት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ግብይቱ እንዲፈጸም ግዴታ የተጣለበት እንደመሆኑ መጠን፣ ለሰሊጥ የውጭ ምንዛሪ ግኝት መቀዛቀዝ አንዱ ከምርት ገበያው አሠራር ጋር የተያያዘ ነው ይባላል፡፡ በመሆኑ ይህም ጉዳይ ታይቶ የተሻለ አሠራር ለመዘርጋት በባለድርሻ አካላቱ መፍትሔ ሊበጅ እንደሚችል ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ በምክክሩ በሰሊጥ ግብይት ዙሪያ እስካሁን ያሉትን ችግሮች በመርመር፣ የአፈጻጸም ስልቶችና ተያያዥ ጉዳዮችን የያዘ ረቂቅ በማሰናዳት በቅርቡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቀርባልም ተብሏል፡፡
በረቂቁም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩትና በዘርፉ ያሉ ተዋንያን ሁሉ በሚገኙበት ከተመከረ በኋላ፣ የራሱ የሆኑ መመርያዎች ተዘጋጅተውለት ሥራ ላይ ለማዋል እንደታሰበም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አሁን በሰሊጥ ዘርፍ የተሰማሩ ማኅበራት የተወከሉበት፣ ንግድ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ተወካዮችን ይዞ የሰሊጥ ጉዳይን እየተመለከተ ያለው ኮሚቴ የሚመራው፣ በእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሰሊጥን ምርት ለዓለም ገበያ ከሚያቀርቡ ጥቂት አገሮች አንዷ ብትሆንም በበቂ እየተጠቀመችበት አይደለም፡፡ የሰሊጥ ምርት ግብይትን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በተለይ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የሰሊጥ ምርት እየተሸጠበት ያለው አማካይ ዋጋ በኩንታል ከ1,600 እስከ 2,000 ብር ነው፡፡
ነገር ግን ከአራት ዓመት በፊት የአንድ ኩንታል ሰሊጥ እስከ 4,400 ብር ይደርስ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሰሊጥ ዋጋ በዚያን ያህል መውረድ የዓለም አቀፉ ገበያ ዋጋ በመውረዱ ብቻ ሳይሆን የምርት ጥራት እንደ ዋነኛ ችግር ይታያል፡፡ ዘርፉን ለመለወጥ ይወሰዳሉ ተብለው ከሚጠበቁ ውሳኔዎች መካከል የምርት ጥራትን ማሻሻል ከዚህ ምክክር እንደሚጠበቅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በቅርቡ ይፋ የሆነው የንግድ ሚኒስቴር መረጃም ከቅባት እህሎች የተገኘው ገቢ መውረዱን ይጠቁማል፡፡ ሆኖም ይህም ዘርፍ እንደሌሎች ምርቶች የወጪ ንግድ ገቢው እየወረደ ከመምጣቱ አንፃር አለበት የተባሉ ችግሮች ተቀርፈው ገቢውን ማሳደግ እንደሚገባ የባለድርሻ አካላቱ ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ በሚኒስትር ዴኤታው እየተደረገ ያለው ውይይት ከአንድ ወር ተኩል በላይ ጊዜ ተወስዶ እየተመከረበት ነው፡፡
በየዓመቱ ለውጭ ገበያ ከሚቀርበው የሰሊጥ ምርት ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ምርት በመሸመት ቻይና ቀዳሚ መሆኗ ይታወቃል፡፡
