- ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ አገሮች በተናጠል ዕድሉን ያገኛሉ
በአፍሪካ በያመቱ በሺሕ ለሚቆጠሩ ባለሙያዎች የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ኮሙዩኒኬሽን መስክ ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎችን ለመሥጠት ‹‹ሲድ ፎር ዘ ፊውቸር›› የተባለ ፕሮግራም የነደፈው ሁዋዌ ቴክኖሎጂስ ኩባንያ፣ ሰሞኑን ወደ ቻይና የሚያቀኑ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ባለሟሎች ለሁለተኛ ጊዜ የሥልጠናው ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስታውቋል፡፡
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኤራስተስ ሞኤንቻ በተገኙበት በተደረገ ሥነ ሥርዓት የኅብረቱ ሠራተኞች፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ ቻይናዋ ሼንጀን ከተማ በማቅናት ከሚከታተሉት የአይሲቲ ሥልጠና በተጓዳኝ የባህል ጉብኝት እንደሚያደርጉም ተገልጿል፡፡ ባለፈው ዓመት 20 የኅብረቱ ባለሙያዎች ወደ ቻይና ተጉዘዋል፡፡ ዘንድሮ ደግሞ አሥር ተጨማሪ ሠልጣኞች ወደ ቻይና እንደሚያቀኑ ታውቋል፡፡
ባለፈው ዓመት በኅብረቱና በሁዋዌ ኩባንያ መካከል ስምምነት መደረጉ ይታወሳል፡፡ በሁለቱ ወገኖች መካከል በተፈረመ የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ሁዋዌ ኩባንያ ለአፍሪካ ኅብረት የአቅም ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ መስማማቱ አይዘነጋም፡፡ ስምምነቱ በወቅቱ ሲፈረም በአፍሪካ ኅብረት ጽሕፈት ቤት በመገኘት ከኅብረቱ ኮሚሽነር ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ ጋር የተነጋገሩት የሁዋዌ ምክትል ፕሬዚዳንት ቻርልስ ዲንግ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ኩባንያው እስካሁን ለ15,000 አፍሪካውያን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ሥልጠና ሰጥቷል ማለታቸው ተዘግቧል፡፡
ከኅብረቱ ባለሙያዎች በተጓዳኝ ለአፍሪካ አገሮች በተናጠል ሥልጠና እየሰጠ የሚገኘው ሁዋዌ፣ ሲድ ፎር ዘ ፊውቸር በተሰኘው ፕሮግራም አማካይነት በያመቱ አንድ ሺሕ አፍሪካውያን የሥልጠና ዕድል በመስጠት ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በአፍሪካ ለወጣት ባለሙያዎች ከሚሰጠው የሥልጠና ዕድል ኢትዮጵያውያንም ተጠቃሚ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ባለፈው ዓመት ዕድሉን ያገኙ 11 ያህል ኢትዮጵውያን ወጣቶች ወደ ቻይና ያቀኑ ሲሆን፣ ዘንድሮም ያህንን ያህል ቁጥር ያላቸው ወጣቶች ወደ ቻይና እንደሚያቀኑ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ ባሻገር ሁዋዌ የ5G ኔትወርክ ዝርጋታን በሚመለከት ጥናቱን እያጠናቀቀና ሙከራዎችን እያካሄደ እንደሚገኝ፣ በአፍሪካ ይህንን ኔትወርክ ለመዘርጋት እንደሚፈልግ የሁዋዌ ምክትል ፕሬዚዳንት መናገራቸው ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ በምዕራፍ ሁለት የ1.6 ቢሊዮን ዶላር የኔትወርክ ማስፋፊያ ፕሮጀክትን ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር በመጋራት የሚሳተፈው ሁዋዌ፣ በ3G እና በ4G ኔትወርክ ዝርግታ ሥራዎች ላይ እየሠራ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
