የዓለም የሥራ ድርጅት (ILO) በ1911 ዓ.ም. ሲመሠረት ኢትዮጵያ ከመጀመርያዎቹ አባል አገሮች አንዷ ነበረች፡፡ በ1916 ዓ.ም. ደግሞ የዓለም የሥራ ድርጅት አባል ሆና ተመዝግባለች፡፡
ከዚህ በኋላ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ወዳጅ አገሮች ኢትዮጵያ ባርነትንና ተገዶ መሥራትን በሕግ እንድትከለክል በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ላይ ግፊት ማድረግ ጀመሩ፡፡
የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት በወቅቱ የዓለም የሥራ ድርጅት ያወጣቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነቶች (ኮንቬንሽን) በመቀበል፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ወዳጅ አገሮች ግፊት አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ጀመረ፡፡
በዚያ ወቅት የውጭ ባለሀብቶች በልዩ ልዩ ፋብሪካዎች፣ በትራንስፖርትና በንግድ ሥራዎች መሰማራት ጀምረው ነበር፡፡ በጭሰኛና በባለርስት የፊውዳል ሥልት ምርት ይመራ የነበረው ኃላቀር ኢኮኖሚ፣ ወደ ኢንዱስትሪ የማደግ አዝማሚያ ማሳየት ጀመረ፡፡
በወቅቱ የነበረው የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ይህ ዕርምጃ ለዲፕሎማሲ ብቻ ሳይሆን ለአገሪቱም ዕድገት አስተዋጽኦ እንዳለው በመረዳት በኢትዮጵያ የመጀመርያውን፣ ‹‹የሠራተኛ ጤናና ደኅንነት አዋጅ ቁጥር 58/1936›› ደነገገ፡፡
ይህ የቁጥጥር አካል በጊዜው በነበረው የኢንዱስትሪና ንግድ ሚኒስቴር ሥር በተደራጀ ቦርድ ይመራ ነበር፡፡ የቁጥጥር ተቋሙ በ1944 ዓ.ም. በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በአሥመራና በምፅዋ ከተሞች የሥራ ሁኔታዎችን ቁጥጥር ማድረግ ጀምሮ እንደነበር የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር በ1996 ዓ.ም. ያካሄደው ጥናት ያመለክታል፡፡
ይህ የሕግ ሰነድ መሠረታዊ የሆኑ የሥራ ሁኔታዎች ለመወሰን የቻለ ሲሆን በተለይ የሥራ ሰዓት፣ የሳምንት ዕረፍት፣ የዓመት ዕረፍት፣ የሕመም ፈቃድና የአገልግሎት ካሳ ክፍያ በተመለከተ ፋብሪካዎች በተቋቋሙባቸው የአገሪቱ ክፍሎችና የወደብ እንቅስቃሴ በሚታዩባቸው እንደ ምፅዋ ባሉ ከተሞች የሥራ ሁኔታዎች በሕጉ መሠረት ተፈጻሚ ይሆኑ ዘንድ በድርጅቶችና ንግድ ቤቶች የቁጥጥር ተግባር እንዲካሄድ መሠረት መጣሉ ይነገራል፡፡
ይህ አሠራር እስከ ንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ውድቀት ቢቀጥልም፣ በወታደራዊው መንግሥት የሥልጣን ዘመን ግን ፈሩን ለቋል፡፡
በ1966 ዓ.ም. የተካሄደው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ያስከተለው የሥርዓት ለውጥ በአገሪቱ የወታደራዊ አገዛዝ እንዲሰፍን፣ የመንግሥት የአስተዳደር ዘይቤም የዕዝ ሥርዓት የሚያራምድና ሶሻሊስታዊ መርህ የተከተለ እንዲሆን አደረገ፡፡ ለውጡ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ መስኮች መሠረታዊ ዕርምጃዎችን የወሰደ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የመሬት ላራሹ ታወጀ፣ ትርፍ የመኖሪያ ቤቶች፣ ባንኮችና የግል ኢንዱስትሪዎች በአዋጅ ወደ መንግሥት እንዲዛወሩ አድርጓል፡፡
እንዲሁም ሶሻሊስታዊ ባህሪ ያነገበ ‹‹የሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 64/1968›› እንዲታወጅ አድርጓል፡፡ በድርጅቶችና የሥራ ክርክር ኮሚቴዎች መደራጀት፣ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበር በአዋጅ ቁጥር 222/1974 በአዲስ መልክ በመንግሥት ድጋፍ መደራጀትን፣ የአሠሪዎች ማኅበር በሕጉ መፍረስንም አስከትሏል፡፡
ይህ አካሄድ ከሶሻሊስት መርህ አንፃር ለሠራተኛው ክፍል ከፍተኛ የሆነ የሕግ ጥበቃ የሰጠ፣ በተቃራኒው ደግሞ የድርጅት አሠሪዎች በሕግ የመደራጀትና ጥቅምን በተመለከተ የተደነገገውን ዓለም አቀፍ መብት የተጋፋ አዋጅ በመሆኑ በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ተወግዟል፡፡
ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት በ1983 ዓ.ም. አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ በሽግግር መንግሥቱ ቻርተርም ሆነ ሕገ መንግሥቱ በአዋጅ ቁጥር 1/1987 ዓ.ም. ከፀደቀ በኋላ የሠራተኞች ጉዳይ በድጋሚ አዲስ መልክ ያዘ፡፡
‹‹ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 31 ላይ ማንኛውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራጀት መብት አለው፤›› ሲል ደንግጓል፡፡
በአንቀጽ 36 ላይም የሕፃናት ጉልበት ከመበዝበዝ ልማዶች የመጠበቅ፣ በትምህርት፣ በጤናና በደኅንነት ላይ ጉዳት የማያደርሱ ሥራዎችን እንዲሠሩ ያለመገደድ ወይም ከመሥራት የመጠበቅ መብት ተደንግጓል፡፡
በአንቀጽ 42 ላይም እንዲሁ፣ በማምረቻና በአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ውስጥ የተሰማሩ ሠራተኞች፣ በእርሻ ሥራ የተሰማሩ ሠራተኞች፣ ገበሬዎችና የገጠር ሠራተኞች የጤናና የኢኮኖሚ ጉዳዮችን ለማሻሻል በማኅበር የመደራጀት መብት አላቸው፡፡ እነኚህ ሠራተኞች ሥራ ማቆምን ጨምሮ ቅሬታቸውን የማሰማት መብት እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ የተደነገገ ሲሆን በፋብሪካ፣ በአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶችና በሌሎችም የተሰማሩ ሠራተኞች የተወሰነ የሥራ ሰዓት እረፍትና የመዝናኛ ጊዜ በየጊዜው ከክፍያ ጋር የሚሰጡ የእረፍት ቀናት፣ ደመወዝ የሚከፈልባቸው የሕዝብ በዓላት፣ እንዲሁም ጤናማና አደጋ የማያደርስ የሥራ አካባቢ የማግኘት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡
ነገር ግን ኢትዮጵያ የሠራተኞች መብትን ለማስከበር፣ የሥራ ላይ ደኅንነቶችን በማረጋገጥ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከገባች በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም፣ ችግሩ ከመቀነስ ይልቅ እስከዛሬ ድረስ ተባብሶና ተወሳስቦ ቀጥሏል፡፡
የሠራተኛ ማኅበራት ጩኸት ሰሚ በማጣቱም በርካታ ሠራተኞች፣ የመደራጀት መብታቸው ተነፍጎና የሥራ ደኅንነታቸው አደጋ ላይ ወድቆ ኑሮአቸውን ለመግፋት ተገደዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ከአሥር ዓመት በፊት ጥር 1998 ዓ.ም. ባካሄደው 12ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ባቀረበው ሪፖርት፣ በአገሪቱ ሕገ መንግሥትና በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/1996 የሠራተኛው የመደራጀት መብት የተደነገገ ቢሆንም፣ በተግባር ግን በርካታ ችግሮች ተደቅነውበታል፡፡ በተለይም በግል ድርጅቶች የሚሠሩ በርካታ ሠራተኞችን በማኅበር ለማደራጀት የሚደረገው ጥረት በአሠሪዎች ማናለብኝነት እየተከለከሉ ይገኛሉ በማለት ገልጿል፡፡
‹‹በማኅበር ለመደራጀት የሚፈልጉ ሠራተኞችን ድርጅቶች ያስፈራራሉ፣ ያባርራሉ፣ ሕገወጥ ዝውውር ያደርጋሉ፣ ፈቃድ ይከለክላሉ፤›› በማለት ኢሠማኮ ጉዳዩን ኮንኖታል፡፡ ኢሠማኮ ይህን ሪፖርት ካቀረበ ከአሥር ዓመታት በኋላ የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ከሪፖርተር ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ ይህ ችግር አሁንም ተንሠራፍቶ ቀጥሏል፡፡
‹‹የሠራተኛ የመደራጀት መብት በተመለከተ አሁንም የተፈታ ነገር የለም፤›› በማለት አቶ ካሳሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ በ79 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሞጆ ከተማ ሰሞኑን ያጋጠመን ክስተት መመልከት ያሻል፡፡ በሞጆ ከተማ ካሉ በርካታ የቆዳ ፋብሪካዎች ውስጥ እንዱ በቻይና ባለሀብቶች የተቋቋመው ፍሬንድሺፕ ታነሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ነው፡፡
ይህ ፋብሪካ 1,500 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ የኩባንያው ሠራተኞች ማኅበር አቋቁመው ነበር፡፡ ነገር ግን ኩባንያው ለሠራተኞች የሥራ ደኅንነት የሚጠብቅ ባለመሆኑ፣ በርካታ ሠራተኞች ለአካል ጉዳት እየተዳረጉ ነው፡፡፡
ይኼንን አስከፊ ሁኔታ የፍሬንድሺፕ ታነሪ ኩባንያ መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አታቄ አዶ ለሚዲያ በመግለጻቸው፣ ከሥራ መታገዳቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በዚህ ኩባንያ ውስጥ ባለፈው ሳምንት በተፈጠረ የሥራ ላይ አደጋ ሁለት ሠራተኞች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ አቶ አበሩ ንጉሤ የተባሉ የቆዳ ፋብሪካው ማሽን ኦፕሬተር በእጃቸው ላይ ከፍተኛ አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ ሌሎችም ሠራተኞች የተለያዩ የአካል ጉዳት እየደረሰባቸው ይገኛል፡፡
አቶ አታቄ፣ ‹‹በፋብሪካው ውስጥ በርካታ በደሎች እየተፈጸሙ ነው፡፡ የአካል ጉዳትም እየተበራከተ ነው፡፡ የፋብሪካው ማኔጅመንት ይህን አሠራር እንዲያስተካክል በተደጋጋሚ ቢነገረውም ማሻሻያ አላደረገም፤›› በማለት እየደረሰ ያለው በደል ሰሚ እንዳላገኘ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን የኢንዱስትሪ ሰላምና የማኅበራት ስምምነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ ጉዳዩ ሪፖርት እንደተደረገላቸው ለሪፖርተር ገልጸው፣ በቅርበት እየተከታተሉት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በሞጆ ከተማ ከ30 በላይ የቆዳ ፋብሪካዎች የሚገኙ ሲሆን፣ ከእነዚህ ፋብሪካዎች ውስጥ ግማሽ ያህሉ ብቻ የሠራተኛ ማኅበራት እንዳሏቸው ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት እየተስፋፋ ያለው ችግር ደግሞ ‹‹ሌበር ኤጀንሲ›› የሚሰኙ ኩባንያዎች፣ ሠራተኞችን እየመለመሉ ለድርጅቶች ማቅረባቸው፣ የሙያ ደኅንነትና ጤንነት ተግባራዊ አለመሆን፣ የዓመት ፈቃድ መከልከል፣ በቂ ደመወዝ አለመክፈል፣ የሴት ሠራተኞችን የወሊድ ፈቃድ መከልከል፣ አደጋ መከላከያ የሥራ አልባሳት አለማቅረብና አደጋ ከደረሰ በኃላ ሠራተኛው ራሱ እንዲታከም መፍረድ፣ ኩባንያዎች የተጣለባቸውን ግዴታ ላለመወጣት የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በተለይ የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀሲዎች ‹‹ሌበር ኤጀንሲ›› ቀደም ባሉት ጊዜያት የፅዳት ሠራተኞች፣ የጥበቃ ሠራተኞንና የመሳሰሉ አነስተኛ ሥራዎች የሚሠሩ ሠራተኞችን ብቻ በመመልመል ያቀርቡ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሥልጡን ባለሙያዎችን ጭምር በመመልመል በሰፊው ማሰማራት ጀምረዋል፡፡
አቶ ፍሬው በቀለ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን፣ የኃይል ኬሚካልና ማዕድን ፌዴሬሽንን ለበርካታ ዓመታት በፕሬዚዳንትነት መርተዋል፡፡ ከዓመት በፊት ከኮንፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር በተፈጠረ ያለመግባባት ወደ እናት ማኅበራቸው ተመልሰዋል፡፡
አቶ ፍሬው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት ሌበር ኤጀንሲዎች እያከናወኑ ያሉት ተግባር በፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ ምክንያታቸውን አቶ ፍሬው ሲገልጹ፣ ሥራውን የሚሠራው ቅጥር ሠራተኛው ሆኖ ሳለ፣ ተጠቃሚዎቹ ግን ኤጀንሲዎች ናቸው፡፡ ይህ የዓለም አቀፍ የሠራተኛ ድርጅት በሚያዘጋጃቸው መድረኮች ሁሉ ሲወገዝ የቆየ ጉዳይ ነው፡፡
‹‹ውግዘቱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ሠራተኛ ማኅበራት ያወገዙትና የሚያወግዙት ጉዳይ ነው፤›› ያሉት አቶ ፍሬው፣ ‹‹ነገር ግን ሌበር ኤጀንሲ ጭራሽኑ ይጥፋ ማለት ሳይሆን፣ የጥቅሙ ጉዳይ ሕጋዊና ፍትሐዊ ሊሆን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉት አገሮች መካከል አንዷ ሆናለች፡፡ በዚህ ሒደት ኢኮኖሚዋ እያደገ በርካታ መንግሥታዊና የግል ኮርፖሬሽኖች በስፋት ዘርፉን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ፡፡
መንግሥት ሥራ አጥነትን ለመቅረፍም እየተፈጠሩ ባሉ ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሰው ኃይሉን ማሰማራት ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እየተፈጠሩ ባሉ የሥራ መስኮች እየገቡ ያሉ ሠራተኞች የሠራተኛ ማኅበራት ለማቋቋም በሚሞክሩበት ወቅት እየተከለከሉ ይገኛሉ፡፡
አቶ ካሳሁን እንደሚገልጹት በተለይ በተቋቋሙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሠራተኛ ለማደራጀት ተሞክሮ ነበር፡፡ ‹‹ከተቋቋሙት ዘጠኝ ኢንዱስትሪ ዞኖች አንዱ ብቻ ለሠራተኛ ማኅበሩ መልካም ነው፡፡ የተቀሩት ስምንቱ ለተቋቋሙት የሠራተኛ ማኅበራት ዕውቅና አልሰጡም፤›› ብለዋል አቶ ካሳሁን፡፡
በኢትዮጵያ ሠራተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ቢሆንም ችግሩን ለመፍታት የፌዴራል መንግሥት፣ የክልል መንግሥትና የአሠሪዎች ትልቅ ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል፡፡
የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ባሳዝን ደርቤ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከዓለም የሠራተኛ ድርጅት መርህ፣ ከሕገ መንግሥቱና ከአዋጅ 377/1996 አንፃር ማኅበራት በነፃ የመደራጀት መብታቸውን አስጠብቃለች፡፡ ‹‹ሠራተኞች በራሳቸው አነሳሽነት ተደራጅተው ሲመጡ ሚኒስቴሩ ዕውቅና ይሰጣል፤›› በማለት የገለጹት አቶ ባሳዝን፣ ‹‹ከሶሻሊስት አስተሳሰብ በመነሳት በሠራተኛ መደራጀት በኩል ጣልቃ ለመግባት የሚመክሩ አሉ፡፡ ይህ ልክ አይደለም፤›› በማለት አቶ ባሳዝን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የሠራተኞች መደራጀት ለመብት ብቻ ሳይሆን ለልማትም አስፈላጊ በመሆኑ፣ የሠራተኞች መደራጀት መሥሪያ ቤታቸው ይፈልገዋል፤›› በማለት አቶ ባሳዝን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም በላይ ግን የኢትዮጵያ ሠራተኛ መሠረታዊ ማኅበራት ያቋቋሙት ኮንፌዴሬሽን ችግሮቹን ለመፍታት ትልቅ ድርሻ ሊኖረው ይገባል፡፡
አቶ ፍሬው ግን ኮንፌዴሬሽኑ ይህንን ኃላፊነቱን በብቃት እየተወጣ ነው ብለው አያምኑም፡፡ አቶ ፍሬው ምክንያታቸውን ሲያስረዱ፣ የኮንፌዴሬሽኑ አመራሮች የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሯሯጡ፣ ሰፊውን ሠራተኛ ዘንግተውታል፡፡
‹‹አመራሮቹ በከፍተኛ የሀብት ቅርምት ውስጥ ናቸው፡፡ አላሠራ ያላቸውንም ጠልፈው ለመጣል በሰፊው ይንቀሳቀሳሉ፤›› በማለት የችግሩን ጥልቀት ያብራራሉ፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በአዲስ አበባ ላይ ለማቋቋም ሲሞከር የካዛብላንካና የሞኖሮቪያ ቡድኖች የሚባሉ ተፈጥረው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የካዛብላንካና ቡድን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዲስ አበባ ላይ እንዳይቋቋም ካስተጋቧቸው ተቃውሞዎች መካከል፣ ‹‹ኢትዮጵያ የሠራተኛ ሕግ የሌላት፣ የሠራተኛ መብት የማታከብር፣ ባርያ የሚሸጥበት አገር ናት፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አዲስ አበባ ላይ ሊቋቋም አይገባም፤›› የሚሉ ይገኙበታል፡፡
ይህንን ተቃውሞ ለመግታትም ጭምር በወቅቱ ኢትዮጵያ የዓለም የሠራተኛ ድርጅት አባል ለመሆን መወሰኗም ይነገራል፡፡
ያም ሆነ ይህ፣ ኢትዮጵያ የሠራተኞችን መብት ለማክበር ከተነሳች 100 ዓመታት ቢቆጠሩም አሁንም ችግሩ ጎልቶ እየተነሳ ነው፡፡
