አቶ ገዙ አየለ መንግሥቱ፣ የሕግ ባለሙያ
አቶ ገዙ አየለ መንግሥቱ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሕግ ባለሙያነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ አቶ ገዙ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን (LL.B) ከጅማ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዚያው በሕግ ሙያ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል። በሥራ መስክም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት፣ በሕግ መምህርነትና በተመራማሪነት ከአምስት ዓመታት በላይ አገልግለዋል። በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸውም የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን አበርክተዋል። አቶ ገዙ አየለ፣ ከዚህ ባሻገር በጎንደር ፋና ኤፍኤም እንዲሁም በወላይታ ሶዶ ፋና ኤፍኤም ሬዲዮ የሕግ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት በማኅበረሰቡ ውስጥ የሕግ ግንዛቤን በመፍጠር ረገድ የድርሻቸውን ተወጥተዋል። ከዚህ በፊትም በተለያዩ የኅትመት ውጤቶች ሕግ ነክ ጉዳዮችን በመተንተንና በመጻፍ የሚታወቁ የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ በውጭ አገር የመጻሕፍት አሳታሚ ድርጅት ታትሞና በአማዞን ድረ ገጽ እየተሸጠ የሚገኝ መጽሐፍም ለኅትመት አብቅተዋል። አቶ ገዙ አየለ በቅርቡ “የኢትዮጵያ የባንክና የሚተላለፉ የንግድ ሰነዶች ሕግ” በሚል ርዕስ አዲስ መጽሐፍ ለንባብ ያበቁ ሲሆን፣ የመጽሐፉን ሁለተኛ ኅትመት ለገበያ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ሰለሞን ጎሹ በመጽሐፋቸውና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- መጽሐፉ በቅርቡ የታተመ በመሆኑና የተጻፈውም የንግድ ሕጉን ለማሻሻል አገሪቱ በሒደት ላይ ባለበችበት ወቅት በመሆኑ፣ መጽሐፉን የሚያነቡ ሰዎች ምን አዳዲስ ነገሮችን ሊያገኙ ይችላሉ?
አቶ ገዙ አየለ፡- መጽሐፉን የማዘጋጀት ሥራ የጀመርኩት ከዛሬ አራት ዓመት በፊት በመሆኑ፣ በንባብና አዳዲስ ሐሳቦችን በማካተት በዘርፉ ካሉ ባለሙያዎች ጋር የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ ሰፊ ጊዜ ወስጃለሁ። ጊዜው በመርዘሙ በተለይም የንግድ ሕጉ አሁን በመሻሻል ሒደት ላይ ስለሚገኝ፣ ይህንን መጽሐፍ መጻፍ ከማሻሻያው አንፃር ሰፊ ክፍተት እንዳይኖር፣ በማሻሻያ መድረኩ ላይ በመሳተፍና በፖሊሲ ሰነዱ የውይይት መድረክ ላይ በመገኘት ሊደረጉ የታሰቡ የማሻሻያ ነጥቦች ላይ ሙሉ የዳሰሳና የማጣቀሻ ነጥቦችን አካትቻለሁ። ከዚህ በተጨማሪም ሕጉ ሊያካተታቸው የሚገቡ አዳዲስ ጉዳዮችን በሰፊው በማንሳት ሕግ አውጪውም ከግንዛቤ ቢያስገባቸው ይበጃሉ የሚሉ ነጥቦችን ያነሳሁ በመሆኑ፣ እንደ ግብዓት ሊጠቅም ይችላል። በመሆኑም በየመድረኩ ሊሻሻሉ ይችላሉ ተብለው የተነሱ ነጥቦችን ከማካተት ጀምሮ በማሻሻል ሒደቱ ላይ ተሳታፊ ከሆኑ ባለሙያዎችም የተለያዩ ሰነዶችን በመውሰድ ለመመልከት ሞክሬያለሁ። ከዚህ በተጨማሪም የንግድ ሕጉ የወጣው በ1952 ዓ.ም. ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት በዘርፉም ከፍተኛ የባንኮች መስፋፋት፣ የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ የክፍያ ሰነዶች መለዋወጥ ጋር ተያይዞ በአገራችን ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎችን በማገናዘብ በዘርፉ የተጻፉ መጻሕፍት ባለመኖራቸው አብዛኞቹ ጉዳዮች አዲስ ነገሮችን የሚያስተዋውቁ ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ። በተለይም ደግሞ በየከፍተኛ የትምህርት ተቋማችን ያሉ ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን የኢትዮጵያን የባንክና የሚተላለፉ የንግድ ሰነዶች ሕግን ለማስተማር የሚጠቀሙት የውጭ አገሮች መጻሕፍትን ማለትም እንደ ህንድ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሣይና የሌሎች በውጭ ቋንቋዎች የተጻፉ የውጭ መጻሕፍትን ነው። እነዚህ ስለአገራችን ሕግ እንዲሁም በአገራችን በዚሁ ኢንዱስትሪ ላይ የሚነሱ ነጥቦች በቂ ዕውቀት የሚያስጨብጡ አይደሉም። በመሆኑም ይህ መጽሐፍ በከፍተኛ ትምህርት ተቋሞቻችን እንደ ማጣቀሻና ማስተማሪያነት የሚያገለግል ነው። መጽሐፉ ያካተታቸው ነጥቦች ከዚህ በፊት ያልተነኩ ግን ሊነሱ የሚገባቸው በርካታ አዳዲስ የሕግ ነጥቦችን በመሆኑ፣ የንግድ ሕጉ ማሻሻያም እንደ ግብዓት ሊጠቀምበት ይችላል የሚል እምነት አለኝ። አንባቢያንም በሕጋችን ሊካተቱ የታሰቡ አዳዲስ ነጥቦችን ከማግኘት በተጨማሪ ሰፊ የሕግ ትንታኔ የሚያስፈልጋቸውን ጉዳዮች፣ በተግባር የሚታዩ አሠራሮች ከነመፍትሔዎቻቸው ማግኘት የሚችሉበት፣ ስለዘርፉ የተጻፈ ፈር ቀዳጅ ሥራ ነው። በሌላ በኩል በባንኮች የሚጠቀሙ ደንበኞችም ሆኑ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት፣ በተለይ የባንክ ሠራተኞች በሙሉ ስለባንክ ሕግ፣ በጠቅላላውም ሕጉ የሚለውንና ወደፊት ሕጉ ምን ሊያካትት ይገባዋል የሚሉ ነጥቦችን እንደ አዲስ ግንዛቤ ሊያገኙበት የሚችሉበት መጽሐፍ ነው ብዬ አምናለሁ።
ሪፖርተር፡-መጽሐፉን በመጻፍ ሒደት ውስጥ ያጋጠመዎት መሠረታዊ ችግር ምን ነበር?
አቶ ገዙ አየለ፡-መጽሐፍ መጻፍ በራሱ እጅግ በጣም አድካሚ ሥራ ነው። በተለይም ለመጽሐፉ የሚሆኑ ማጣቀሻዎችን፣ የተለያዩ ጽሑፎችን፣ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችን በመፈለግ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አንብቦ ጠቃሚ የሆኑት መለየት በእውነቱ እጅግ አድካሚ ሥራ ነው። መጽሐፉን ለመጻፍ በአገራችን ስለባንክ አሠራር የተጻፉ በቂ መጻሕፍት የሉም። እኔ ለመጻፍ ስነሳም በባንክ ዘርፍ ያሉ ሕጎች ላይ እንደማጣቀሻ የሚውል ደረጃውን የጠበቀ መጽሐፍ ለመጻፍ በመሆኑ፣ ለማንኛውም የሕግ ሰውም ሆነ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንደ ማጣቀሻነት እንዲያገለግል በማሰብ ማጣቀሻዎችን ለማንበብ ብዙ ጊዜ ወስጃለሁ። ሌላው ግን መጽሐፉን ለማሳተም ኅትመቱን የሚያግዝ ተቋም ወይም ባንክ መፈለጉም በጣም አድካሚ ነበር። በአገሪቱ ቁጥራቸው በርከት ያሉ ባንኮች ቢኖሩና መጽሐፉም የባንኮቹን የየዕለት እንቅስቃሴ የሚያግዝ፣ ለሠራተኞቻቸውም ዕውቀትን የሚያስገበይ እንደሚሆን እርግጥ ነው። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ ባንኮቹ ሠራተኞቻቸው ሀብቶቻቸው በመሆናቸው፣ ሠራተኞቻቸውን ለማሠልጠን ትኩረት እንደሚሰጡ እየገለጹልህ፣ በባንክ ዘርፍ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራተኛ እንደተሰማራ እየታወቀ እንኳ ይህንን መጽሐፍ ለማሳተም የሄድኩበትን ርቀት ሳስበው በጣም አድካሚ ነበር። በመጨረሻ ከእነዚሁ ተቋማት ውስጥ የመጽሐፉን ኅትመት አቢሲኒያ ባንክ ስፖንሰር በማድረጉ ለመታተም በቅቶ የመጀመርያው ዕትም እያለቀ ስለሆነ፣ የተሰጠኝ ማበረታቻም የገጠሙኝን ችግሮች እንዳልቆጥራቸው አድርጎኛል።
ሪፖርተር፡- የሚተላለፉ የንግድ ሰነዶችን ማለትም እንደ ቼክ፣ የሐዋላ ወረቀት፣ የተስፋ ሰነድ ሌሎችም እንደ ሲፒኦ ያሉ ሰነዶች ያላቸው የሕግ ሽፋን በመጽሐፉ ተካቷል። ይሁንና ቼክ በሰፊው በንግዱ ማኅበረሰብ ዘንድ አገልግሎት ላይ የሚውል ሰነድ ከመሆኑ አንፃር ከቼክ ጋር ግንኙነት ላላቸው የሕግ ጉዳዮች በፍርድ ቤት ክርክሮችን ያስነሳሉ። እነዚህን ስፋት ያላቸውን ከቼክ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በተመለከተ የእርስዎ አጠቃላይ ግምገማ ምንድን ነው?
አቶ ገዙ አየለ፡-ቼክ በሰፊው ሥራ ላይ የዋለ በመሆኑ፣ የመጽሐፉ ሰፊ ክፍልም ከቼክ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይሸፍናል። በተግባር ቼክ እንደ ዋስትና ሰነድ፣ ለዋስትና የሚጻፍባቸው ሁኔታዎች እጅግ በርካታ እንደሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሠረቱ ቼክ እንደቀረበ የሚከፈል የገንዘብ ሰነድ ነው፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮም ቼክ በዋስትና የሚሰጥ የዋስትና ሰነድ ሳይሆን፣ እንደቀረበ የሚከፈል ሰነድ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ቼክን በዋስትና ሰነድነት መስጠት መለመዱ በሕጋችን ሰፊ ሽፋን የተሰጣቸውንና ለዚሁ ተግባር የሚውሉትን የሐዋላ ወረቀትና የተስፋ ሰነድ አገልግሎቶችን አቀጭጯል ብዬ አስባለሁ። ለዚህ ዋነኛ ማሳያው እነዚህ ሰነዶች የቼክን ያህል ቀርቶ በትንሹም እንኳ እንደሚገባቸው ያልተዋወቁ፣ በሰፊው አገልግሎት ላይ የማይውሉ መሆናቸው ነው። ሌላው የክፍያ ጊዜው ወደፊት ተደርጎ የሚጻፍ ቼክን ወይም Postdated Cheque የተመለከቱ ጉዳዮች ላይም ጥያቄዎች ይነሳሉ። በመሠረቱ በሕጋችን ውስጥ ወደፊት ተከፋይ የሚሆን ቼክ መፈቀድና አለመፈቀዱን በተመለከተ የንግድ ሕጉ አንቀጽ 855 እና ሌሎችም አንቀጾች በመጥቀስ በሕግ ባለሙያዎች መካከል ክርክሮች ይነሳሉ። እኔ በበኩሌ ሕጉ ወደፊት ተከፋይ እንዲሆን ተደርጎ የሚጻፍን ቼክ ፈቅዷል የሚል ድምዳሜ የሚያደርስ የሕግ አንቀጽ አላገኘሁም። በአጠቃላይ ሲታይም ቼክ እንደቀረበ የሚከፈል ሰነድ መሆኑን ሕጉ አስቀምጦ ሳለ፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እንዲከፈል ብሎ በዚሁ ሕግ ውስጥ ሊፈቅድ የሚችልበት አግባብ አይኖርም። ይህ ከተደረገም ከላይ እንደገለጽኩት ቼክን እንደ ዋስትና ሰነድ ተገለገልንበት ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ቼክ እንደቀረበ የሚከፈል የገንዘብ ሰነድ መሆኑ ቀረ ማለት ነው። በተግባር ይህ ሁኔታ ለብዙ ክርክሮች መነሻ ሆኖ እናየዋለን። አንዳንድ ጊዜም ቼኩ የተጻፈው ወደፊት ተደርጎ በመሆኑ፣ ቼኩ ተጻፈ ከተባለበት ቀን በፊት ቼኩን የጻፈው ግለሰብ ሊሞት ይችላል፡፡ በዚህም ቼኩን ጽፏል የተባለው ግለሰብ፣ ቼኩ በተጻፈበት ወቅት በሕይወት ስላልነበር፣ የተጭበረበረ ቼክ ነው በማለት የሚቀርቡ ክርክሮች የተለመዱ ናቸው። በሌሎች አገሮች ሁኔታም ብታይ ወደፊት ተከፋይ የሚሆን ቼክ በግልጽ የተከለከለ ከመሆኑም በላይ ይህን ዓይነት ቼክ የሚጽፍ ሰው፣ ቼኩ በቀረበ ጊዜ እንደሚከፈልበት አውቆ መጻፍ አለበት የሚል አቋም የሚያንፀበርቅ የሕግ ድንጋጌ እስከ ማስቀመጥ ደርሰዋል። ይህ ሁኔታ የሚያመለክተው ለወደፊቱ የንግድ ሕጉ በዚህ ረገድ ጥርት ያለ አቋም መያዝ እንዳለበት ነው። በአጠቃላይም በተለይ ከቼክ ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ግብይቶች የንግድ ሕጋችን አሁን ባለበት እንኳን ካስቀመጠው በተቃራኒውና በልማድ በዳበሩ በርካታ ተግባራት እየተመራ መሆኑንና ይህ ተግባርም መቀጠል እንደሌለበት ታውቆ የሕግ ማዕቀፉ ሊከበርና ሊሠራበት እንደሚገባ አመላካች ሆኖ አግኝቸዋለሁ። የሕግ ማዕቀፍ የሚያስፈልጋቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉም ለመረዳት ችያለሁ።
ሪፖርተር፡- ከዚሁ ጋር በተያያዘ በመጽሐፍዎ ትኩረት የተሰጠው የደረቅ ቼክ ጉዳይ ነው፡፡ የሕጉ ድንጋጌዎች ምን ያህል ከተግባሩ ጋር የተጣጣሙ ናቸው?
አቶ ገዙ አየለ፡- ደረቅ ቼክ፣ የቼክን ተዓማኒነትና የንግድ እንቅስቃሴን የሚጎዳ ሕገወጥ ተግባር ነው። ለደረቅ ቼክ ዋነኛ ምክንያቶች አንዳንድ ጊዜ በአውጪውና በተከፋዩ መካከል የሚደረጉና ቼክን በዋስትናነት ለመስጠት የሚገፋፉ የውስጥ ስምምነቶች ናቸው። በንግድ ሕጉ መሠረት አንድ ሰው ቼክ ሲጽፍ በሒሳቡ ውስጥ ሊያዝበት የሚችለው በቂ ስንቅ (ሒሳብ) መኖሩን አውቆ መሆን አለበት ይላል። ይህም ቼኩ በሚጻፍበት ጊዜና የቼኩ የመክፈያ ጊዜ እስከሚያልቅ ድረስ ባለው ስድስት ወር ጊዜ ውስጥ በሒሳቡ ውስጥ በተጻፈው ቼክ ልክ ገንዘብ መኖር ይጠበቅበታል። ይህ ካልሆነ ግን ቼኩ ለክፍያ ሲቀርብ ሒሳብ ወይም ገንዘብ የሌለው ከሆነ እንደ ደረቅ ቼክ ተቆጥሮ የወንጀል ተጠያቂነትን ጨምሮ፣ የፍትሐ ብሔር ኃላፊነትንና በብሔራዊ ባንክ የሚወሰድን አስተዳደራዊ ዕርምጃን እንደሚያስከትል ከብሔራዊ ባንክ መመርያዎች አንፃርም ተብራርቷል። ይሁንና ሕጉ ደረቅ ቼክን በተመለከተ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ደረቅ ቼክን በመጻፍ በተለያዩ መንገዶችና ምክንያቶች የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ በመስጠት ወይም ቼኩ ከመጀመሪያውንም ማሟላት የሚገባውን በሕጉ የተቀመጡትን መስፈርቶች ሆነ ብሎ በማጓደል የተጻፈው ቼክ፣ በደረቅ ቼክነት እንዳይመታ የሚደረጉባቸው ሁኔታዎች አሉ። እነዚህ ነጥቦች በተለይም ብሔራዊ ባንክ በየጊዜው በሚያወጣቸው መመርያዎች ውስጥ በግልጽ እየተደነገጉ በመምጣታቸው፣ በዚህ ረገድ ደረቅ ቼክን ለመግታት ግልጽ ሕጎች አሉ ማለት እንችላለን።
ሪፖርተር፡- የሕጉ ማዕቀፍ እንደዚህ ግልጽ ከሆነ፣ ሕጉ በተደጋጋሚ ሲጣስ የሚታየው ለምድን ነው? የቼክ የክፍያ እንዲቆም በተደጋጋሚ ጥያቄ የሚቀርበውስ ለምንድን ነው?
አቶ ገዙ አየለ፡- ቼክ ሕጉ የሚፈልገውን መጠይቆች አሟልቶ ለከፋዩ ባንክ ክፍያ እንዲፈጸም ከቀረበ በኋላ፣ ከፋዩ ባንክ ለአምጪው ክፍያ አልፈጽምም ሊል ከሚችልባቸው ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝ በአውጪው ለባንኩ የተሰጠ እንደሆነ ነው። በንግድ ሕጋችን አንቀጽ 857 በእንግሊዝኛው ቅጂ እንደተመለከተውም በአውጪው የሚሰጥ የክፍያ ይቁም ትዕዛዝ የቼኩ ከፋይ ባንክ ክፍያ አልፈጽምም ለማለት በቂ ምክንያት ነው እንደሆነ ያስቀምጣል። በተመሳሳይ መልኩ የአማርኛው የንግድ ሕግ አንቀጽ 857 ቅጂ ቼኩ ከመከፈሉ በፊት አውጪው እንዳትከፍል ብሎ የነገረው እንደሆነ፣ ባንኩ የቼኩን ዋጋ አልከፍልም ለማለት ይችላል ይላል። እነዚህ የንግድ ሕጉ ድንጋጌዎች አንደኛ በጣም ጥቅል ሐሳብ የያዙ በመሆናቸው የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝን የሚያስፈጽሙት ባንኮች በምን በምን ምክንያት ክፍያ ይቁም ትዕዛዝን ተቀብለው ማስፈጸም እንዳለባቸው ባለመግለጹ፣ ለቼክ ተገልጋዮችም ሆነ ለባንኮች አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር ይሆናል። ሁለተኛውና ዋናው ችግር አንቀፁ የቼክ ከፋይ ባንኮች የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝን እንደ ግዴታ መፈጸም እንዳለባቸው ሳይሆን፣ አልከፍልም ለማለት ይችላሉና በቂ ምክንያት ነው በሚሉ የላሉ ቃላቶች በማስቀመጡ ባንኮችም ቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝን መቀበልና ያለመቀበል መብት ያላቸውና በባንኮች በጎ ፈቃድ (ሥልጣን) ላይ የተመሠረተ እንደሆነ የሚያሳብቅ የሕግ አንቀጽ ነው። በቅርቡ የወጣው የብሔራዊ ባንክ መመርያ፣ መመርያ ቁጥር SBB/61/2016 ግን በአንቀጽ 6 የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝን የተመለከቱ አንቀጾችን አስቀምጧል። መመርያው በአንቀጽ 6 እንዳስቀመጠው ከሆነ፣ ቼኩን የጻፈው አውጪው አካል የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝ ቢደርሰው እንኳ፣ የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዙ ለከፋዩ ባንክ የተሰጠው በዚሁ መመርያ አንቀጽ 5 ላይ የተቀመጠውንና በቂ ስንቅ ሳይኖር ቼክ መጻፍ የሚያስከትለውን አስተዳደራዊ ኃላፊነት ወይም የወንጀል ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ ከሆነ ላይቀበለው ይችላል ይላል። በነገራችን ላይ ይህ ጉዳይ በሌሎች አገሮችም ያለ ነው። ሌላው የቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝን ከወንጀል ተጠያቂነት ለማምለጥ ሲባል መስጠት የተከለከለ ተግባር መሆኑ ነው። ይሁንና ግን በአንዳንድ አጋጣሚዎች በቼክ የተገበያዩ ግለሰቦች በራሳቸው በሚፈጥሩት አለመግባባት ምክንያት ወይም ቼኩ የተቆረጠው በወቅቱ በሒሳቡ ውስጥ በቂ ስንቅ ሳይኖር በሚሆንበት ሁኔታ፣ የቼክ ክፍያ ይቁም ተግባር ሲፈጸም ማየት የተለመደ ተግባር ነው። ይሁንና አሁን ቼክ ክፍያ ይቁም ትዕዛዝ መስጠት የሚቻለው ቼኩ ጠፍቶብኛል ወይም ተሰርቄያለሁ በሚሉ ደንበኞች ብቻ መሆን እንዳለበት ብሔራዊ ባንክ መመርያ በማውጣቱ የቼክ ክፍያ ይቁም ተግባር እንደሚቀንስ እሙን ነው።
ሪፖርተር፡- በመጽሐፍዎ በአንዳንድ ባንኮች አሠራር ሒደት ውስጥ ልማዳዊ አሠራሮች እንደሚዘወተሩ ጠቅሰዋል። እነዚህ አሠራሮች ግልጽ የሕግ ድንጋጌ ባለበት አግባብ የተለመዱ ናቸው ወይስ የባንኩ አሠራር የሕግ ክፍተቶችን ለመሸፈን የተጠቀማቸው ናቸው?
አቶ ገዙ አየለ፡- በጣም የሚገርምህ እነዚህ ጉዳዮች ናቸው መጽሐፉን ለመጻፍ ዋነኛ አነሳሽ ምክንያቶች የሆኑኝ። አንዳንዶቹ ልማዳዊ አሠራሮች ግልጽ ከሆነው ሕግ በማፈንገጥ የዳበሩ ናቸው። በዚህ ረገድ ለምሳሌ ቼክን በከፊል መክፈል በሕጉ የተፈቀደ ተግባር ሆኖ ሳለ፣ በአሠራር ግን ቼክ በከፊል የሚከፈልባቸው አጋጣሚዎች ጠባብ ወይም የሉም ለማለት የሚጋብዙ ናቸው። ቼክን ለክፍያ ማረጋገጥ የሚባል አሠራርም አላቸው፡፡ ቼኩ ከተጻፈና ለክፍያ ለባንኮቹ ሲቀርብ ባንኮቹ ቼኩን አውጪው ስለመጻፉ በስልክ የማረጋገጥ ተግባር ይሠራሉ። ይህ ሙሉ ለሙሉ ከቼክ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደቀረበ የሚከፈል መሆኑን የሚያስቀር ነው። እነዚህና ሌሎችም ብዛት ያላቸው ጉዳዮች ግልጽ የሕግ ድንጋጌዎችን በማፈንገጥ የባንኩ ዘርፍ ያዳበራቸው አሠራሮች በመሆናቸው፣ ሕጉን ሊከተሉ የሚገባቸው ናቸው። ሌላው ሕጉ ሳይኖር የዳበሩ በርካታ ልማዳዊ የባንክ አሠራሮችና የሕጉን ክፍተት ሞልተዋል የምንላቸው ጉዳዮችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ከሐዋላ የገንዘብ ዝውውር ጋር በተገናኘ፣ የፊርማ ጉዳይን የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ፍርድ ቤቶችም የባንኮችን ልማዳዊ አሠራሮች በመመርኮዝ ውሳኔ የሚሰጡበት አግባብ እንደ ሕግ የሚቆጠሩበትን አሠራሮች ስለፈጠሩ፣ እነዚህን ጉዳዮች የሚሸፍን የሕግ ማሻሻያ እስከሚወጣ ድረስ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው።
ሪፖርተር፡- ከባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በተለይ ከወጪ ንግድ መስፋፋት አኳያ እንዲሁም ባንኮች ከሚያቀርቧቸው ብድሮች አንፃር የወጪ ንግድን የሚመለከቱ የሕግ ክፍተቶች አሉ። በዚህም በሰነድ ብድር የመስጠት አገልግሎት ወይም ሌተር ኦፍ ክሬዲት የመሳሰሉትን በሚመለከት የንግድ ሕጉ ሊሸፍናቸው የሚገቡ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?
አቶ ገዙ አየለ፡-የንግድ ሕጋችን ከወጣ ረዥም ጊዜ በማስቆጠሩ፣ ሕጉ በሰነድ ብድር የመስጠት አገልግሎትን በተመለከተ ያስቀመጣቸው ድንጋጌዎች የሕጉን ተራማጅነት የሚያመላክቱ ናቸው። ይሁንና ግን ከዓለም አቀፍ የንግድ መስፋፋት፣ የወጪና የገቢ ንግድ አገልግሎቶችም በዚያው መጠኝ ከመስፋፋታቸው አኳያ፣ በአሁኑ ወቅት የሚነሱ አለመግባባቶችን የሚፈቱ ድንጋጌዎች በሕጉ ውስጥ በበቂ ሁኔታ አልተካተቱም። ከዚሁ አገልግሎት በመነሳት የንግድ ግንኙነቶቹ የሚከናወኑት በባንኮች አማካይነት በመሆኑ፣ ባንኮቹ የብድር ሰነዶቹን ገዥና ሻጭ ወገንን በመወከል የሚሰጡ እንዲሁም ገዥና ሻጭን የሚያማክሩ ጭምር ናቸው። በተጨማሪም በዕቃዎቹ የግብይት ሒደት የሚፈጠሩ ጉዳዮችንም እስከ መከታተልና ለደንበኞቻቸውም ስለግብይቱ ምክር እስከ መለገስ የሚደርስ ኃላፊነት አለባቸው። ከዚህ አንፃር በንግድ ሕጋችን አንቀጽ 959 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች ውስጥ የተመለከቱ ሐሳቦች፣ አንድ ባንክ አማካሪ ባንክ የሚባለው መቼ ነው? አረጋጋጭ ባንክ ምንድን ነው? የአማካሪም ሆነ የአረጋጋጭ ባንኩ ኃላፊነቶችና ግዴታዎች በግብይት ሒደቱ ምን መምሰል አለበት? የሚሉና ሌሎችም ጉዳዮች በግልጽና በስፋት አልተቀመጡም፡፡ ይህ በመሆኑም በተለይም የሌተር ኦፍ ክሬዲት አገልግሎትን በተመለከተ የሚያጋጥሙ ክርክሮችን በዓለም አቀፍ ደረጃ አስገዳጅነት በሌላቸውና ለርካታ አገሮች ሕጎች እንደ መነሻ በሚያገለግሉ ዓለም አቀፍ ሕጎች ማለትም እንደ UCP600 ባሉ ሕጎች ላይ በመመሥረት ክርክሮች ሲቀርቡ ይስተዋላል። በመሆኑም ይህ የሕጉ ክፍል እየሰፋ ከመጣው የሰነዶቹ ተጠቃሚ አንፃር ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና በጥልቀት ከሌሎች አገሮች የሕግ ተሞክሮ፣ ከፍርድ ቤት ክርክሮች እንዲሁም ከባንኮቹ አሠራር አንፃር ታይቶ በአጥጋቢ መንገድ መሻሻል አለበት።
ሪፖርተር፡- ከባንኮች ብድር አኳያ የዋስትና ሰነዶችን ወይም Letters of Guarantees በተመለከተም የሚነሱ ክርክሮች አፈጻጸም ላይ ብዥታዎች አሉ። ስለዚህ ጉዳይ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
አቶ ገዙ አየለ፡- የዋስትና ሰነዶች በአሁኑ ወቅት በጣም ሰፊ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው። የዋስትና ሰነዶችን የተመለከቱ እስከ ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ ደርሰው ውሳኔ የተሰጠባቸው ጉዳዮች አሉ። በመጽሐፉ እንዳስቀመጥኩትም የሰበር ውሳኔዎቹ የዋስትና ሰነዶችን በፍትሐ ብሔር ሕጋችን ውስጥ ከአንቀጽ 1920 ጀምሮ ስለሰው ዋስትና የተቀመጡትን ድንጋጌዎች በማንሳት የዋስትና ሰነዶችን ከሰው ዋስትና ጋር ለማመሳሰል የተከረበት አግባብ፣ በሰነዶች ዋስትናን የሚሸፍን ሕግ በግልጽ እንደሚያስፈልገን አመላካች ናቸው። ሁለቱም ጉዳዮች በመሠረታዊነት የተለያዩ ናቸው፡፡ አንደኛ በባህሪያቸው የሰው ዋስትና ካለምንም ክፍያ የሚሰጥ ሲሆን፣ የዋስትና ሰነዶችን የሚሰጡ ባንኮች ግን ተመጣጣኝ ክፍያ በኮሚሽን መልክ ይቀበላሉ። ሌላው የሰው ዋስትና በሕጋችን በግልጽ ሽፋን የተሰጠው የዋስትና ዓይነት ሲሆን፣ የዋስትና ሰነዶችን የሚመለከቱ ሕጎች በዓለም አቀፍ ደረጃ መውጣት የጀመሩት እ.ኤ.አ. ከ1992 እስከ 2010 ባሉት ጊዜያት መሆኑን ስንመለከትም፣ ሰነዶቹን የሰውን ዋስትና ከሚገዛውና በ1952 ዓ.ም. ቀደም ብሎ ከወጣው ሕግ እኩል ይጓዛሉ ማለት መሠረታዊ ስህተት እንደሆነ እንረዳለን። በመሆኑም በአብዛኞቹ ሰነዶች ከጽሑፍ ጀምሮ ይዘታቸው ልማዳዊ አሠራርን መሠረት ያደረገ እንጂ በግልጽ የሰፈረ የሕግ አግባብ አለው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ፍርድ ቤቶቹም ሆኑ ባንኮቹ የዋስትና ሰነዶችን በተለመከተ የሚከተሉት አሠራርና የሰው ዋስትናን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ለሰነዶች ዋስትናነት እንደሚያገለግሉ አድርጎ መውሰዱም በመሠረታዊነት ከላይ ካነሳኋቸውና ከሌሎችም ምክንያቶች አአኳያ ለእኔ የሚያሳምነኝ ጉዳይ ባለመሆኑ፣ ከዚሁ የተለየ አቋም እንዳለ አንስቻለሁ።
ሪፖርተር፡- ብድር መስጠት የባንኮች ዋነኛ ሥራ እንደመሆኑ መጠን በተበዳሪዎችና በባንኮች መካከል ያለው ግንኙነት በሕጉ በበቂ ሁኔታ ተደንግጓል የሚል አቋም አለዎት?
አቶ ገዙ አየለ፡- ብድር ጥንትም ባንኮች ሲመሠረቱ ጀምሮ ዋነኛ የሥራ ድርሻ ሆኖ የቀጠለ ተግባር ነው። በመሆኑም በሕግ በግልጽ ተቀምጠው የማናገኛቸው ነገር ግን ብድር ለመውሰድ አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ብድር ከተወሰደ በኋላም ቢሆን በአበዳሪው ባንክና በተበዳሪ ግለሰቦች ወይም ተቋማት መካከል የመያዣና የብድር ውልን መሠረት አድርገው የሚነሱ ጉዳዮች አሉ። ከዚህ አንፃር ብድርን በተመለከተ የብድር አገልግሎቶች እየሰፉ ከመምጣታቸውም አንፃር ለምሳሌ እንደ የዋስትና ሰነድ ብድሮች ያሉት በሕጉ ውስጥ በግልጽ መካተት ይኖርባቸዋል። ሌላው ብድር ለመስጠት ሕጉ እንዲሟሉ የሚፈልጋቸው ቅድመ ሁኔታዎችም ቢሆኑ፣ በግልጽ ቢደነገጉ እንኳ እዚህም እዚያም በሕጉ የተጠቀሱትን ነጥቦች በአንድ ማድረጉም ሌላው ጉዳይ ነው። የብድር ግንኙነቱን የሚገዙ ውሎችም ለአንድ ወገን ያደሉ እንዳይሆኑ ገዥ ሕጎች ቢኖሩ የሚሻል ይመስለኛል። ሌላው የብድር ዓይነቶችን ለምሳሌ የንግድ ተቋም አስይዞ መበደርን በተመለከተ በቂ የሕግ ሽፋን ተሰጥቷቸው በስፋት አገልግሎት ላይ ያለመዋል ሁኔታዎች አሉ። በመሆኑም እነዚህንና ሌሎች ጉዳዮችን በበቂ ሁኔታ አጣጥሞ ማስኬድ በጣም አስፈላጊ ነው።
ሪፖርተር፡- የባንክ አገልግሎት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ በተለይ የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት በተመለከተ በሕጉ ቢካተቱ ብለው ያነሷቸውና አሁን ግን ተፈጻሚነት ሊኖራቸው አይገባም ብለው የጠቀሷቸው በርካታ ነጥቦች አሉ። ባንኮችን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ሲባል ለማድረግ ለውጥ ሊደረግባቸው የሚገቡ መሠረታዊ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
አቶ ገዙ አየለ፡- አሁን ዓለም የደረሰበት የአስተሳሰብና የዕድገት ደረጃ በራሱ የሰዎች የሰብዓዊና ተፈጥሯዊ መብቶች የሚከበሩበትና እንዲከበሩም በስፋት እንቅስቃሴ የሚደረግበት ዘመን ነው። ከአካል ጉዳተኞች የባንክ አገልግሎትና ተጠቃሚነት አኳያ የሚነሱ ነጥቦች መሠረታዊ የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችን እንደያዙ አምናለሁ። ስለሆነም አንድ ባንክ አገልግሎቱን ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ማድረግ አለበት ሲባል ዝም ብሎ ባንኩ ለንግድ እንቅስቃሴው ስለሚያስፈልገው ብቻም ሳይሆን፣ የእነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች መብት ማክበር ስላለባቸውም ጭምር ነው። አሁን ባሉት የንግድ ሕጋችን እንዲሁም የፍትሐ ብሔር ሕጋችን ድንጋጌዎች ላይ ማየት የተሳናቸው ሰዎች ፊርማ የራሳቸው ስለመሆኑ በውል አዋዋይ ፊት ቀርቦ ካልተረጋገጠ ድረስ በሕግ ፊት የሚጸና ውል መዋዋል እንደማይችሉ ተደንግጎ እናገኘዋለን። በተለይ መጻፍ የማይችሉ ወይም ሕጉ ባስቀመጠው ድንጋጌ ፈርማ ለመፈረም እጅ ወይም እግር ወይም ሁለቱም የሌላቸው የካል ጉዳተኞች ሲያጋጥሙ፣ የገንዘብ ወጪና ገቢ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን አዳጋቸ ይሆንባቸዋል። ዘመኑ ያመጣቸውን የኤሌክትሮኒክስ የባንክ አገልግሎቶች ማለትም የኤቲኤምና ሌሎች የካርድ አገልግሎቶችም በሕግ ዕውቅና ተሰጥቷቸው እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዲጠቀሙባቸው አልተደረጉም። ቼክ ጽፎ መሰጠትን በተመለከተ መፈረም የማይችሉ ሰዎች አገልግሎቱን ማግኘት የሚያስችላቸው የሕግ ድንጋጌ ባለመኖሩ፣ ይህንን አገልግሎት ከማግኘት ተገድበዋል። እነዚህ ሁሉ የሕግ ድንጋጌዎችና የልምድ አሠራሮች ቢኖሩም ኢትዮጵያ በዓለም አስገዳጅነት ያለውን የአካል ጉዳተኞች መብት ኮንቨንሽን እ.ኤ.አ. ጁላይ 7 ቀን 2010 አጽድቃለች፡፡ በመሆኑም የዚህ ኮንቬንሽን ድንጋጌ የአካል ጉዳተኞች የእኩልነት መብትን በተለይ የራሳቸውን የገንዘብ እንቅስቃሴ በራሳቸው የመጠቀምና የመቆጣጠር መብትን በግልጽ ደንግጓል። ከዚህ አንፃር የንግድ ሕጉ ሲወጣ አካል ጉዳተኞችን ለመከላከል በማሰብ የተቀመጡት ድንጋጌዎቸ መሠረታዊ የእኩልነት መብትን የሚጋፉ ስለሆኑ፣ አካል ጉዳተኞችም ቢሆኑ በጥቂቱ እንኳ ሒሳብ ለመክፈት ደጋፊም ሆነ ሌላ ምስክር ሳያስፈልጋቸው ራሳቸው በፈለጉትና በመረጡት መንገድ ሁሉንም የባንክ አገልግሎቶችና እንቅስቃሴዎች ከሌላው ማኅበረሰብ እኩል የማግኘት መብት አለባቸው። ለዚህም መሠረታዊ የሕግ ማሻሻያዎች ከዓለም አቀፍ ሕጎች አንጻር እየታዩ መደረግ አለባቸው።
