ከአንድ ዓመት በላይ ሲያወዛግብ የቆየው የኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫ፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ውሳኔ ተሽሮ በድጋሚ ተካሄደ፡፡ ዳግም በተካሄደ የአመራሮች ምርጫም አዲስ ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሁም የቦርድ አባላትን በመምረጥ ተቋጭቷል፡፡ ተሰናባቹ ቦርድ የፈጸማቸው የሕግ ጥሰቶች ይፋ ተደርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት ከአንድ ዓመት በፊት ያካሄደው ጉባዔና ምርጫ የሕግ ጥሰት እንደነበረበት በመረጋገጡ ጠቅላላ ጉባዔ ዳግመኛ እንዲካሄድ በተጠራውና ሐሙስ፣ ሐምሌ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው የማስተካከያ ምርጫ መሠረት፣ የኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ የተመረጡት በዕለቱ ብቸኛ ዕጩ ሆነው የቀረቡት አቶ ኢያሱ ሞሲሳ የተባሉ ተወዳዳሪ ናቸው፡፡
የኦሮሚያ የዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የኦሮሚያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ኢያሱ፣ ለኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትነት ብቸኛው ተወዳዳሪ ሆነው በቀረቡበት ምርጫ፣ ድምፅ ከሰጡ 99 አባላት ውስጥ የ97ኙን አብላጫ ድምፅ ማግኘት ችለዋል፡፡ ሆኖም ለፕሬዚዳንትነት የቀረቡት አቶ ኢያሱ ብቻ መሆናቸው ጥያቄ አስነስቷል፡፡
ይሁን እንጂ የማስተካከያ ምርጫውን ለማካሄድ ሁሉም የዘርፍ ምክር ቤቶች ለፕሬዚዳንትነት፣ ለምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲሁም ለቦርድ አባልነት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን እንዲጠቁሙ ለጉባዔተኞቹ ዕድል ቢሰጥም፣ የኦሮሚያ የዘርፍ ምክር ቤት በብቸኝነት፣ ለፕሬዚዳንትነት ሊወዳደር የሚችል ዕጩ በማቅረቡ አቶ ኢያሱ ተመርጠዋል፡፡ ቀሪዎቹ የዘርፍ ምክር ቤቶች ለቦታው ዕጩዎችን ማቅረብ አልቻሉም፡፡
ለምክትል ፕሬዚዳንትነት ግን የአዲስ አበባና የአማራ ዘርፍ ምክር ቤቶች ዕጩዎችን በማቅረባቸው ከአማራ የዘርፍ ምክር ቤት የተወከሉት አቶ ልሳኑ በለጠ የኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ተመርጠዋል፡፡
ለቦርድ አባልነት በዕጩነት ከቀረቡት 16 ተወዳዳሪዎቸ ውስጥ አቶ አቶ ቢተው ዓለሙ፣ ሻለቃ ኃይሉ ጉርሙ፣ አቶ ወዮማ ገሜሳ፣ አቶ ሰዒድ አብዱራህማን፣ አቶ ደስታው ሰመነ፣ አቶ ጋሻው ጉግሳ፣ አቶ ሐሰን አብዱላሒም (ዶ/ር)፣ አቶ አበባየሁ ግርማና አቶ ደስታ ብዙየነ ለቦርድ አባልነት የሚያበቃቸውን ድምፅ በማግኘት ተመርጠዋል፡፡ ከተሰናባቹ ቦርድ ሰባቱ በድጋሚ መመረጣቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ከነባር የዘርፍ ምክር ቤቱ አመራሮች ውስጥ በተለይ በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉት አቶ ገብረ ሕይወት ገብረ እግዚአብሔር፣ በጉባዔው ቢታደሙም በምርጫ ሳይሳተፉ ቀርተዋል፡፡ በዕለቱ ንግግር ማድረግ ያልቻሉት አቶ ገብረ ሕይወት፣ እንደ ጠቅላላ ጉባዔ አባል ድምፅ መስጠትም አልተፈቀደላቸውም ነበር፡፡ ይህ የሆነውም የማስተካከያ ምርጫውን ለማካሄድ የሁሉም ክልሎች የዘርፍ ምክር ቤቶች ተወካዮቻቸውን እንዲልኩ በተጠየቁት መሠረት፣ ከዚህ ቀደም አቶ ገብረ ሕይወት የትግራይ ክልል የዘርፍ ምክር ቤት ለእሳቸው የውክልና መተማመኛ ባለመስጠቱ ለመምረጥም ሆነ ለመመረጥ የሚያስችላቸውን ዕድል እንዲያጡ አድርጓል፡፡
የትግራይ ክልል የዘርፍ ምክር ቤት በሐሙሱ ጠቅላላ ጉባዔ እንዲሳተፉ የመምረጥና መመረጥ መብት ኖሯቸው ከተወከሉት 11 ልዑካን ውስጥ የአቶ ገብረ ሕይወት ስም ባለመኖሩ በታዛቢነት በጠቅላላ ጉባዔው ለመታደም ተገደዋል፡፡ ከሕግና ደንብ ውጪ ነሐሴ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የዘርፍ ምክር ቤት በተካሄደው ምርጫ በምክትል በፕሬዚዳንትነት ተመርጠው ነበር የተባሉት አቶ አበባው መኮንንም በዚህ ምርጫ በዕጩነት አልቀረቡም፡፡
ከአንድ ዓመት በላይ ሲያጨቃጭቅ የነበረው የዘርፍ ምክር ቤት የምርጫ ሒደት አወዛጋቢ ሆኖ ከቆየባቸው ምክንያቶች አንዱ ከዘርፍ ምክር ቤት ሕገ ደንብ ውጪ ፕሬዚዳንቱና ምክትል ፕሬዚዳንቱ በተደጋጋሚ ራሳቸውን በማስመረጥ በኃላፊነት ቦታ ቆይተዋል የሚለው ይገኝበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ባለፈው ዓመት በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ፣ ከአባላት ዕውቅና ውጪ ሕገ ደንቡን ለማሻሻል ተሞክሯል የሚለው ትችትም ሲሰነዘር መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ሲመረምር የቆየው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የደረሰበትን ድምዳሜ ይፋ አድርጓል፡፡ በሐሙሱ ጉባዔ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቦጋለ ፈለቀ ይህንኑ ገልጸዋል፡፡
በአቶ ገብረ ሕይወት ይመራ የነበረው ቦርድ አገር አቀፉ የዘርፍ ምክር ቤት ነሐሴ 28 እና 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ባካሄደው ስምንተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ፣ አዲስ የሥራ አመራር ቦርድ ምርጫ ማካሄዱን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ጠቅላላ ጉባዔው የሕግ ጥሰቶች ተፈጽመውበታል በማለት በበርካታ አባላት ቅሬታዎች ቀርበውበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በቅሬታዎቹ መነሻነት ሚኒስቴሩ የማጣራት ሥራውን ሲያከወናውን እንደቆየ ገልጸዋል፡፡ የተገኘውን ውጤትም ለጠቅላላ ጉባዔው አሳውቀዋል፡፡
ነሐሴ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የተደረገው ምርጫ የንግድና የዘርፍ ምክር ቤቶችን ለማቋቋም ከወጣው አዋጅ ቁጥር 341/96 እንዲሁም ይህንኑ አዋጅ ለማስፈጸም በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከወጣው መመርያ፣ ከማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብና ከጠቅላላ ጉባዔው የስብሰባ ቃለ ጉባዔ አንፃር ጉዳዩን በጥልቀት ሲመረምር እንደቆየ በማብራራት፣ የተደረገው ምርጫ የምክር ቤቱን መተዳደሪያ ደንብ አለመከተሉ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ በአቶ ገብረ ሕይወት የሚመራው ቦርድ አዋጅና ደንብ ያልጠበቀ ምርጫ አካሂዷል በተባለው የዓምናው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት ቀርቦ የነበረው የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያም ቢሆን አስፈላጊውን ሕጋዊ አካሄድ ጠብቆ እንዳልተዘጋጀ ሚኒስትር ዴኤታው ጠቁመዋል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 341/1995 መሠረት የዘርፍ ማኅበራትም ሆኑ የምክር ቤት አባላት፣ የአምራች ድርጅት ባለቤት መሆን አለባቸው የሚለውን ድንጋጌ ያልጠበቁ አካሄዶች መኖራቸውንና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የዘርፍ ማኅበራትም በተደረገው የጠቅላላ ጉባዔ እንዲሳተፉ በአግባቡ ጥሪ ስላልተላለፈላቸው ምርጫውም ሆነ ጉባዔ ችግሮች እንደነበሩበት መረጋገጡን ጠቅሰዋል፡፡
የታዩትን ክፍተቶች በመሙላት የምክር ቤቱን ህልውና ማስጠበቅ በማስፈለጉ፣ ሚኒስቴሩ ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን የጠራውን የማስተካከያ ምርጫ፣ ያለ ችግር ለማካሄድ ሲጥር ቆይቷል ተብሏል፡፡ የተፈጠሩት ክፍተቶች የምክር ቤቱን ሕጋዊነትና ህልውና ጥያቄ ላይ መጣላቸውን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ እነዚህን ችግሮች በማረም የምክር ቤቱን ሕጋዊነትና ህልውና መመለስ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
ስለተፈጸሙት የሕግ ጥሰቶች የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሕግ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተካልኝ ከድር አቅርበዋል፡፡ ትኩረት ሰጥተው ያብራሩት በዓምናው ጠቅላላ ጉባዔ ወቅት የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያው እንዲሁም የተመረጠው ቦርድ ሕጋዊነት ላይ ነበር፡፡
ምክር ቤቱ ሁለት መተዳደሪያ ደንቦች እንዳሉት የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፣ አንዱ በ1999 ዓ.ም. የወጣው ደንብ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ዓምና በነሐሴ ወር ተሻሽሎ የወጣው አዲሱ ደንብ ነው፡፡ በ1999 ደንብ መሠረት አንቀጽ 24 ውስጥ ‹‹ደንቡን ለማሻሻል ከጠቅላላ ጉባዔው ተሳታፊዎች በ2/3ኛው መደገፍ አለበት፤›› የሚለው ተካቷል፡፡ በመሆኑም ነባሩን መተዳደሪያ ደንብ ለማሻሻል ድምፅ በመስጠት መሳተፍ የነበረባቸው 120 አባላት ቢሆኑም፣ የተሳተፉት ግን 73 ብቻ በመሆናቸው የማሻሻያ ደንቡን ለማፅደቅ ሕጋዊ መሠረት እንዳልነበረው ተጠቅሶ ተሻሻለ የተባለው ደንብ ውድቅ ተደርጓል፡፡
በ1999 ዓ.ም. በወጣውና ዓምና በተሻሻለው ደንብ መካከል ስላለው ልዩነት በሰጡት ማብራሪያም፣ ተለውጠዋል የተባሉትን ነጥቦች ጠቅሰዋል፡፡ በ1999 ዓ.ም. በወጣው ደንብ አንቀጽ 16 መሠረት አንድ የቦርድ አባል የአገልግሎት ዘመኑ ሁለት ዓመት ብቻ እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ አንድ ተመራጭ ማገልገል የሚችለውም ለሁለት የምርጫ ዘመን ብቻ መሆኑን አስፍሯል፡፡ ተሻሻለ በተባለው ደንብ ደግሞ የአንድ ተመራጭ የአገልግሎት ዘመን ሁለት ዓመት እንደሆነ ቢጠቅስም፣ በነባሩ ደንብ የተጠቀሰውን የአንድ ተመራጭ የሁለት የምርጫ ዘመን ቆይታን ሰርዞታል፡፡ ይህም ማለት አንድ ተመራጭ ያለጊዜ ገደብ ደጋግሞ እንዲመረጥ መፍቀዱን እንደሚያሳይ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡ ይህም ከቀረቡት ቅሬታዎች መካከል የቦርድ አባላት ከሁለት የምርጫ ዘመን በላይ በተደጋጋሚ ተመርጠዋል የሚለውን አቤቱታ እንደሚያሳይ ተጠቅሷል፡፡ ስለዚህ ይህ አንቀጽ ያለ ጊዜ ገደብ ለመመረጥ እንዲያስችል ተብሎ መዘጋጀቱ፣ በግልጽ ችግር እንዳለበት ማሳየቱን ከተደረገው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ሌላው ሰፊ ምርመራ ተደርጎበታል የተባለው ጉዳይ፣ የተመረጠውን ቦርድ ሕጋዊነትን የተመለከተ ሲሆን፣ ነሐሴ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ተመረጠ የተባለውን ቦርድ ሕጋዊነት ለመወሰን በየትኛው ደንብ አግባብ ተመርጧል ከሚለው በመጀመር ፍተሻ መደረጉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ነሐሴ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የተደረገውን ጠቅላላ ጉባዔ በተመለከተ የተሰናዳው ቃለ ጉባዔ እንደሚያመለክተው፣ አዲሱን ደንብ በተመለከተ በቃለ ጉባዔው የሰፈረው ማሻሻያ፣ ደንቡን በጥልቀት ተመልክቶ እንዲያፀድቀው ለሚመለከተው የሥራ አመራር ቦርድ ውክልና ሰጥቷል የሚል እንደነበርም ታይቷል፡፡
ይህ የሚያሳየውም አዲሱ ደንብ በዚያን ቀን የፀደቀ ሳይሆን ነሐሴ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚመረጠው ቦርድ ተመልክቶት ውክልና መስጠቱን አመላካች ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ሆኖም በአቶ ገብረ ሕይወት የሚመራውና ነሐሴ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የተመረጠው ቦርድ፣ የተሻሻለውን ደንብ መስከረም 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በማፅደቁና ሥራ ላይ በማዋሉ፣ የቀድሞው ቦርድ ነሐሴ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ከተመረጠ ተፈጻሚ መሆን የነበረበት ነበሩ እንጂ አዲሱ ደንብ ባለመሆኑ ምርጫው ትክክል አይደለም ወደሚለው ድምዳሜ አድርሷል፡፡ ‹‹ይህ ከሆነ የተመረጡትን አባላት በነባሩ ደንብ አንቀጽ 16/5 መሠረት አዲስ የተመረጡት የቦርድ አባላትን ስንመለከት አብዛኛዎቹ ተመራጮች ከሁለት ጊዜ በላይ እንደተመረጡ በግልጽ ያመለክታል፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ሌሎችም መረጃዎች ይህንኑ እንደሚያረጋግጡ ገልጸዋል፡፡ ስለዚህም በአቶ ገብረ ሕይወት ይመራ የነበረው ቦርድ በሕጋዊ መንገድ እንዳልመጣ ማረጋገጡን ተናግረዋል፡፡
የሕግ ባለሙያው ማብራሪያ ከተሰማ በኋላ በዕለቱ የተገኙት የጠቅላላ ጉባዔ አባላት አስተያየት እንዲሰጡ ሲደረግ የሕግ ጥሰቱ መኖሩ እየታወቀ ውሳኔ ለመስጠት አንድ ዓመት መፍጀቱ ተገቢ እንዳልነበር የገለጹ ሲሆን፣ ሚኒስቴሩም ለውሳኔ መዘግየቱን በማመን ጥራት ያለው ሥራ ለመሥራት ሲባል ጊዜ መውሰዱን አስታውቋል፡፡
በዕለቱ ቅሬታቸው ካሰሙ አባላት መካከል በቃለ ጉባዔ ከተያዘው አጀንዳ ውጪ ሐሳባቸው ተጣሞ ቀርቧል በማለት፣ ቦርዱ ከዕውቅናቸው ውጪ የራሱን ቃለ ጉባዔ እንዳዘጋጀ በመግለጽ የወቀሱም ነበሩ፡፡ በጠቅላላ ጉባዔው የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የምክር ቤቱን ህልውና ለመጠበቅ፣ ጣልቃ ላለመግባት ሲል መንግሥት ብዙ መታገሱን፣ ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላም ቢሆን ለመፍታት የተደረጉ ምርመራዎችና ነገሩ በአፋጣኝ እንዳይቋጭ ማድጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ‹‹ቃለ ጉባዔ ተጣሞብናል፣ እኛ ያልነው አልተካተተም የሚባል ከሆነ የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ብርቱ አመራር መምረጥ ይኖርባቸዋል፤›› በማለት የምክር ቤቱን አባላት ወርፈዋቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዘርፍ ምክር ቤት ጉዳይ በዚህ መንገድ ሲቋጭ፣ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከአዲሱ አመራር ጋር በጋራ ለመሥራት ቃል በመግባት ጉባዔውን አጠቃሏል፡፡
