- በስድስት ወራት 1.1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ በኢትዮጵያ ሸጧል
- በአፍሪካ ከ15 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ለገበያ አቅርቧል
የናይጄሪያን 65 በመቶ የሲሚንቶ ገበያ እንደተቆጣጠረ የሚገመተው ዳንጎቴ ሲሚንቶ፣ በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ 1.1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ለገበያ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡ ይህ የምርት መጠን በናይጄሪያና በሴራሊዮን ለገበያ ከቀረበው ቀጥሎ በአፍሪካ ከፍተኛ ሽያጭ ያስመዘገበበት ሊሆን በቅቷል፡፡
ዳንጎቴ ሲሚንቶ ሰኞ ሐምሌ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ባሰራጨው መረጃ መሠረት፣ ከናይጄሪያ ውጪ በሌሎች የአፍሪካ ገበያዎች ከሚያካሂደው የሲሚንቶ ሽያጭ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ የ12.6 በመቶ ጭማሪ የተመዘገበበት የምርት መጠን ለሽያጭ አቅርቧል፡፡ በዚህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ከተመዘገበው የ24 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ76 ቢሊዮን ናይራ (አንድ ዶላር በ315 ናይራ ይመነዘራል) ገቢ ይልቅ ባለፉት ስድስት ወራት የ394 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ124.4 ቢሊዮን ናይራ ገቢ በማስመዝገብ የ63.7 በመቶ ጭማሪ ለማሳየት በቅቷል፡፡
ኩባንያው ምንም እንኳ በኢትዮጵያ የ1.1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሲሚንቶ ምርት በማምረት ለገበያ ማቅረቡን ቢጠቀስም፣ በገንዘብ ረገድ ምን ያህል ገቢ እንዳገኘበት አልገለጸም፡፡ ከኢትዮጵያ ባሻገር በናይጄሪያ የ6.9 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን እንዲሁም በሴራሊዮን የ4.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ በማምረት መንፈቀ ዓመቱን አገባዷል፡፡ ኦዲት ባልተደረገው ሪፖርት መሠረት፣ በናይጄሪያ የተመረተው ሲሚንቶ አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተመረተው የ8.8 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በንፅፅር የዘንድሮ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በአገሪቱ ዝናባማ ወቅት በመሆኑ የግንባታ ዘርፉ በመቀዛቀዙ እንደሆነ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኦን ቫን ድረ ዌድ መግለጻቸው ተዘግቧል፡፡
ከሦስቱ አገሮች በተጓዳኝ በሴኔጋል የ700 ሺሕ ሜትሪክ ቶን፣ በካሜሩን የ600 ሺሕ ሜትሪክ ቶን፣ በጋና የ500 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ ምርት ለገበያ ያቀረበው ዳንጎቴ፣ በታንዛኒያ የ400 ሺሕ ሜትሪክ ቶን እንዲሁም በዛምቢያ የ300 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ በመሸጥ በአፍሪካ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ በጠቅላላው ፓን አፍሪካ ገበያ እያለ በሚጠራው የአፍሪካ አገሮች መዳረሻ ገበያዎቹ ያከናወነው የሽያጭ መጠን የ64 በመቶ የገቢ ጭማሪ አስገኝቶለታል፡፡ ይህም ሆኖ በናይጄሪያ ከተመዘገበው የ291.4 ቢሊዮን ናይራ ገቢ አኳያ ሲታይ፣ ከአፍሪካ አገሮች የተገኘው 124.4 ቢሊዮን ናይራ በመገኘቱ የኩባንያው ዋና ገበያ የተመሠረተው በናይጄሪያ መሆኑን ያሳያል፡፡
በጠቅላላው በተገባደዱት ስድስት ወራት ውስጥ የናይጄሪያን ጨምሮ 15.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ ለገበያ ማቅረቡን የኩባንያው መረጃ ያመለክታል፡፡፡ በናይጄሪያ የተመረተውና ለገበያ የቀረበው ከሌሎች አገሮች አብላጫ ያለው ምርት ቢሆንም፣ በውጭ ምንዛሪ የተገኘው የሌሎች አገሮች ገቢ ወደ ናይጄሪያ መገበያያ ሲመነዘር ግን ከፍተኛ በመሆኑ ለኩባንያው ትልቅ የገቢ መጠን ማስመዝገብ እንዳስቻለው ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ በስድስት ወራት ውስጥ ለገበያ ያቀረበው የ1.1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የምርት መጠን አብዛኞቹ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በዓመት ውስጥ ለማምረት የሚጣጣሩበት መጠን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዳንጎቴ በኢትዮጵያ ሙገር አካባቢ በገነባው ፋብሪካ በዓመት የማምረት አቅሙ 2.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነው፡፡ ይህንኑ መጠን በእጥፍ የማሳደግ ውጥን እንዳለውና ለገነባው ፋብሪካ ያወጣውን የ500 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በእጥፍ በማሳደግና የማስፋፊያ ግንባታ በማካሄድ ምርቱን በእጥፍ እንደሚጨምር የኩባንያው ባለቤት አሊኮ ዳንጎቴ፣ ፋብሪካው በተመረቀበት ወቅት ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡ በአሁኑ ወቅትም ምርቱን ወደ ጎረቤት አገሮች በተለይም ወደ ኬንያ መላክ እንደጀመረ ይታወቃል፡፡
ምንም እንኳ በኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው የውጭ ኩባንያዎች አንዱ ቢሆንም፣ በሪፖርቱ እንዲህ ያሉትን ችግሮች አልጠቀሰም፡፡ ከዚህም ባሻገር ኩባንያው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ትልቅ ራስ ምታት ሆኖበት መቆየቱን ሲገልጽ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተደጋጋሚ የኃይል መቆራረጥ በምርት ሥራው ላይ ሳንካ መፍጠሩንም ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
ዳንጎቴ በአሁኑ ወቅት 14 አፍሪካ አገሮችን ያዳረሰ የኢንቨስትመንትና የንግድ እንቅስቃሴ የዘረጋ ግዙፍ አፍሪካዊ ኩባንያ ሆኗል፡፡ በሲሚንቶ ዘርፍ የሚያደርገው መስፋፋት እንደ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ያሉትን አገሮች በማካተት ላይ ይገኛል፡፡ ከሲሚንቶ ባሻገር በስኳር ፋብሪካዎች፣ በምግብ ሸቀጦች ማምረቻና ማከፋፈያዎች፣ ወዘተ. ሰፊ የገበያ ድርሻ ለመያዝ የበቃ ኩባንያ ነው፡፡ በኢትዮጵያም በስኳር ልማት ዘርፍ የመሰማራት ፍላጎት እንዳለው ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
