Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

የኢትዮጵያ ተሞክሮዎች የታዩበት የአፍሪካ ማኑፋክቸሪንግ ጉባዔ

$
0
0

መነሻውን በሩዋንዳ ኪጋሊ ያደረገው የአፍሪካ ኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ማዕከል ዘንድሮ ሁለተኛውን ጉባዔውን በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡ በዚህም በአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን በመገምገም ያሉትን ለውጦችና ተግዳሮቶች የሚቃኙ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡

ከግንቦት 28 እስከ ግንቦት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በተካሄደው ጉባዔ ከ30 አገሮች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ታድመዋል፡፡ የጉባዔው የክብር እንግዳ በሚንስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ውጤታማነት ዘርፍ ኃላፊ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ናቸው፡፡

ዶ/ር አርከበ የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍን፣ የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማት ሥራዎችን፣ የኢኮኖሚ ዕድገትንና የመሳሰሉትን ነጥቦች ከኢትዮጵያ፣ ከናይጄሪያና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች አኳያ እያጣቀሱ ከቬትናም ጋር በማነፃፀር አፍሪካ በተለይም ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

በአፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ሲመዘገብ ቆይቶ ድንገት ከአራት ዓመታት ወዲህ ግን ኢትዮጵያን ጨምሮ እንደ ናይጄሪያ ያሉ ትልልቅ ኢኮኖሚያዊ አቅም ያላቸውን አገሮች የሚፈታተን አደጋ እንደተደቀነ ባተተው ንግግራቸው፣ ናይጄሪያ በአፍሪካ ግዙፍ የነዳጅ ሀብት ክችምት ካላቸው አገሮች ተርታ እንደመሠለፏ ከ90 በመቶ ያላነሰውን የውጪ ምንዛሪ ገቢ የምታገኝበት ሸቀጥ ነበር፡፡ ይሁንና በዓለም ገበያ የታየው የሸቀጦች ገበያ መዳከም ሳቢያ ገቢዋ ማሽቆልቆሉ ሲገሰግስ የቆየውን የኢኮኖሚ ዕድገት እየተቀዛቀዘ መምጣቱን ዶ/ር አርከበ አጣቅሰዋል፡፡

ያላደጉ አገሮች መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ለውጥ ለማምጣት በየዓመቱ እስከ ስምንት በመቶ የሚገመት የኢኮኖሚ ዕድገት ቢጠበቅባቸውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሊያስመዘግቡ የቻሉት ግን አምስት በመቶና ከዚያ ያነሰ እንደነበር ሲጠቀስ ላለፉት 15 ዓመታት በአፍሪካ የታየው የዕድገት ጉዞም በአማካይ ከሦስት በመቶ ያልበለጠ በመሆኑ የሚፈለገውን የማዋቅራዊ ለውጥ ሊያመጣ እንዳልቻለ ዶ/ር አርከበ ባቀረቡት ጽሑፍ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ዓመትም ሆነ በመጪው ዓመት የሚጠበቀው ዕድገት ብዙም ልዩነት እንደማይታይበት ከዚህ ይልቅ በኢትዮጵያ የሚገመተው የኢኮኖሚ ዕድገት 7.5 በመቶ ሊሆን እንደሚችል የዓለም ባንክን የቅርብ ትንበያ አጣቅሰው፣ አገሮች እንዲህ ያለውን ዕድገት ዘላቂ ለማድረግ የአምራች ኢንዱስትሪዎቻቸውን መገንባት አማራጭ እንደሌለው አስምረውበታል፡፡

ቬትናምና ናይጄሪያን ባነፃፀሩበት ኢኮኖሚያዊ ዓውድ ናጄሪያ በኢኮኖሚ አቅም የበላይነቱን ይዛ ተገኝታለች፡፡ ይኸውም አማካይ የነፍስ ወከፍ ገቢዋ 3000 ዶላር ሲሆን፣ የቬትናም ግን ከ2000 ዶላር በታች ሆኖ ይገኛል፡፡ ይህም ቢባል ግን በብዙ ጎኑ ቬትናም ከናጄሪያ አብላጫ የምትይዘበት አቅም አላጣችም፡፡ ትልቁና ዋናው ደግሞ ቬትናም የገነባችው የአምራች ዘርፍ ነው፡፡ ከ40 በመቶ ያላነሰው የኢኮኖሚው ዘርፍ በአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚወከልባት ቬትናም፣ ከ90 በመቶ በላይ የወጪ ንግዷን ገቢ የምታገኘውም ከዚሁ ዘርፍ ነው፡፡ በአንፃሩ በናይጄሪያ ነዳጅ ከፍተኛው የወጪ ንግድ ገቢ ምንጭ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከ20 በመቶ በታች ድርሻ ያለው አምራች ኢንዱስትሪዋ በሌሎች እንደ ንግድና አገልግሎት ባሉት መስኮች የተዋጠ ነው፡፡

ይህንን አመክዮ መነሻ በማድረግም መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት የግድ መካከለኛ ገቢ መሆን አይጠይቅም ያሉት ዶ/ር አርከበ የኢትዮጵያን ተሞክሮዎችም ለታዳሚዎቹ አጋርተዋል፡፡ ኢትዮጵያ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በመሠረተ ልማት መስክ፣ በትምህርት፣ በግብርና በሌሎችም ያስመዘገበቻቸውን ለውጦች አመላክተዋል፡፡ በባቡር፣ በታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ምንጮች ግንባታ፣ በመንገድ መሠረተ ልማት አውታሮች ገንባታ የተካሄዱትን እንቅስቃሴዎች ጠቅሰዋል፡፡ በትምህር ረገድ በአንድ ወቅት ከልማት አጋሮች ለኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበው ምክር በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህህርት ላይ ኢትዮጵያ አተኩራ እንድትሠራ የሚያሳስብ ምክር ሲለገሳት እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር አርከበ፣ መንግሥት ይህንን ምክር ውድቅ በማድረግ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛዎችን ማስፋፋቱን እንደረጠ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም ከ30 በላይ ዩኒቨርሲቲዎችን በመክፈት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ምሩቃን ከማፍራት ባሻገር፣ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበሩትን የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በጀርመን የቴክኒክና ሙያ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት የተስፋፉ ከ1,300 በላይ ማሠልጠኛዎችን ለመገንባት እንደተቻለ አብራርተዋል፡፡

በመሠረተ ልማት መስክ ከሚደረገው ኢንቨስትመንት በዋቢነት የጠቀሱት በኢትዮጵያ የሚካሄደው አዋጭነት ነው፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ የምትገኝ ‹‹አንዲት አገር›› 700 ሜጋዋት ኃይል ለማመንጨት ያወጣችውና ኢትዮጵያ 1,870 ሜጋዋት የሚያነጨውን ግልገል ጊቤ ለመገንባት ያወጣችው እኩል መሆኑ፣ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን መገንባት ብቻም ሳይሆን የአፈጻጸምና የፕሮጀክት ትግበራም ለመዋቅራዊ ለውጥ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አሳይተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ምሳሌ ያደረጉት ዶ/ር አርከበ፣ በፖለቲካዊ ጫና ምክንያት ከውጭ ምንጮች ግድቡን ለመገንባት የሚያስፈልገውን አምስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማግኘት ባለመቻሉ ከአገር ውስጥ ምንጮችና ከሕዝቡ መዋጮ በመነሳት ለመገንባት መቻሏም በማሳየት የተጠቀሙበት የለውጥ ምሳሌ ነበር፡፡

በአንፃሩ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለመዋቅራዊ ለውጥ ተስፋ ከሚደረጉ ጥቂት አገሮች ተርታ መሆኗን የጠቀሱት በዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ልማት ቡድን የምርምር አጋር የሆኑት ኒል ባልቺን ናቸው፡፡ ኒል እንዳብራሩት ከሆነ ዘጠኝ አገሮች በውጭ ኢንቨስትመንት የታገዘ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የመገንባት አቅም እንዳላቸው ተረጋግጧል፡፡ ኢትዮጵያ በተካተተችበት በዚህ ምድብ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያና ኡጋንዳ እንዲሁም ዛምቢያ ተካተዋል፡፡ ይሁንና ከእነዚህ አገሮች ውስጥ በተለይ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክና ናይጄሪያ በወጪ ንግድ ላይ ያተኮረ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚገነቡ ተብለዋል፡፡

አገሮችን በዘጠኝ ዋና ዋና ጠቋሚ መመዘኛዎች የፈረጀው የእነ ኒል ጥናት፣ ዝቅተኛ ተመራጭነት ያላቸው ከፍተኛ ተስማሚነት ካላቸው በመለየት አስቀምጧል፡፡ ለአብነትም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁን የኤሌክትሪክ ኃይል ግድብ ማመንጫ እየገነባች የምትገኝ ብትሆንም፣ እስካሁን ስታቀርብ የቆየችው የኤሌክትሪክ ኃይል ከሌሎች አገሮች አኳያ ሲታይ ርካሽ የሚባል ሆኗል፡፡ ርካሽ ሲባል ግን ውድ የሚያደርጉት መመዘኛዎችም ቀርበው ኢትዮጵያን ዝቅተኛ ውጤት ያሰጠበት መለኪያም ታይቷል፡፡ ይኸውም አስማማኝነት የጎደለውና ባሻው ጊዜ ቦግ እልም የሚል የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ማቅረቧ አገሪቱን በዝቅተኛ ተስማሚነት ደረጃዎች ውስጥ ከሚስቀምጧት መካከል የሚመደበው ነው፡፡

ዶ/ር አርከበ አበክረው እንደተናገሩት ከሆነ አገሪቱ ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚጠይቁ ኢንዱስትሪዎችን በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡ የስኳር ልማት፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ከሚጠቀሱት ውስጥ በጉልህ ይነገርላቸዋል፡፡ መንግሥት በአሥር ዓመት ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስባቸው ዘርፎች መካከል የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት በትልቁ ይቀመጣል፡፡ በተለይ የአምራች ኡንዲስትሪውን ለማስፋፋት የኢንዱትሪ ፓርኮች ግንባታ በተመራማሪዎቹ ዘንድ ለኢትዮጵያ ነጥብ አስገኝቶላታል፡፡ ይህም ቢባል ግን የኢንዲስትሪ ሠራተኞች ምርታማነት እጅጉን ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት አገሪቱ ከምታደርገው መስፋፋትና ከምታከናውናቸው የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እኩል ለአምራች የሰው ኃይሏም ትልቅ ትኩረት በመስጠት መሥራት ይጠበቅባታል ተብሏል፡፡

እንዲህ ያሉትን እውነታዎች በማስጨበጥ የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት በሌላው አካባቢ ከሚታየውም ይልቅ የተሻለ አቅም እንዳለው የታየበቱ ጥናት፣ በተለይ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን ጨምሮ በጣት የሚቆጠሩ አገሮች በማኑፋክሪንግ ኢንዱስትሪዎቻቸው የተመረቱን ለውጭ ገበያ በማቅረገቡ ረገድ ለውጥ ያሳዩ በማለት አስቀምጧል፡፡ ኢትዮጵያ በአማካይ እስከ 25 በመቶ የሚደርስ ዓመታዊ ዕድገት በማሳየት ዘጠኙን አገሮች ብትመራም፣ በአገልግሎት ጥራትና በኢንቨስትመንት ምቹነትና ተስማሚነት፣ በእሴት ጭመራና በመሳሰሉት ነጥቦች ተወስደውባታል፡፡

የአፍሪካን የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን መደገፍ (ሰፖርቲንግ ኢኮኖሚክ ትራንስፎርሜሽን) በተሰኘው የጥናት ውጤት መሠረት፣ ኢትዮጵያ በቀላል ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በመልካም ተራማጅነት ከመጠቀሱት ዘጠኑ አገሮች በጠቅላላ ውጤት አራተኛውን ደረጃ አግኝታለች፡፡ ዛምቢያ፣ ናይጄሪያና ኬንያ ኢትዮጵያን ሲቀድሙ፣ ሞዛምቢክ፣ ሩዋንዳ፣ ጋና፣ ታንዛንያና ኡጋንዳ ይከተላሉ፡፡

ለውጭ ገበያዎች የሚያመርቱ 16 ኩባንያዎችን ያቀፈው የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልዩ ልዩ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ምርቶችን መላክ ጀምሯል፡፡ ከሐዋሳ ፓርክ ቀድሞ ሥራ የጀመረው የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክም እንዲሁ በርካታ የአልባሳት ውጤቶችን ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ ትልልቅ አምራቾች የሚገኙበት ማምረቻ ነው፡፡ ከሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንደሚገኝ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ መንግሥት ከግብርና ሸቀጦች ወጪ ንግድ ይልቅ በኢንዱስትሪ ምርቶች ተፎካካሪ ለመሆን 13 የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመትከል ላይ ይገኛል፡፡

የአገሪቱ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከውጭ ገበያ ባሻገር በአገር ውስጥ በሚመረቱ ምርቶች ከውጭ የሚገቡትን በመተካት ረገድም ሚናቸው እየጎላ መምጣቱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ በሚኒስቴሩ ሥር ከሚተዳደሩ፣ ተጠሪ ተቋማት አንዱ የሆነው የኬሚካልና የኮንስትክሽን ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስቲትዩት በቅርቡ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት የፕላስቲክ፣ የጎማ፣ የበርና መስኮት ፍሬሞች፣ የወረቀት፣ የኅትመትና የምርት ማሸጊያ ምርቶችና የመሳሰሉት አገር ውስጥ በብዛት እየተመረቱ ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ወጭ ማዳን እንደቻሉ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የአፍሪካ የኢኮኖሚ ትራስፎርሜሽን ማዕከል በምሕፃረ ቃሉ አሴት የተሰኘው ይህ ተቋም፣ በእንግሊዙ ተራድኦ ድርጅት ዩኬ ኤድ በሚደገፈው የኦቨርሲስ ደቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት አማካይነት በየዓመቱ በአፍሪካ የሚታየውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ለማገዝና ለማጥናት የሚሠራ ተቋም ነው፡፡

 

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles