Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

‹‹የመድን ኩባንያዎች ውድድር ዓረቦንን በመቀነስ ላይ ብቻ ማተኮሩ ራሳቸውን ወደ መብላት ይወስዳቸዋል››

$
0
0

 

አቶ አሰግድ ገብረ መድኅን፤ የኢንሹራንስ ባለሙያ

አቶ አሰግድ ገብረ መድኅን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሒሳብ አሠራር ተመርቀዋል፡፡ ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት ተጨማሪ ዲግሪያቸውን ከዚያም የማስትሬት ዲግሪያቸውን ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አግኝተዋል፡፡ የተለያዩ የኢንሹራንስ ትምህርቶችንም ተከታትለዋል፡፡ ወደ ሥራው ዓለም የተቀላቀሉት ከ17 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ መድን ድርጅት ባልደረባነት ነው፡፡ በዚሁ መሥሪያ ቤት ከገንዘብ ተቀባይነት እስከ ዲስትሪክት ዳይሬክተርነት ድረስ ባለው ኃፊነት ለ15 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ የቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅም ነበሩ፡፡ የመድን ድርጅት የቦርድ አባል ሆነውም ለሰባት ዓመታት አገልግለል፡፡ ከመድን ድርጅት ከለቀቁ በኋላ ላለፉት ሁለት ዓመታት በብርሃንና በኢትዮ ላይፍ ኩባንያዎች ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች  ሠርተዋል፡፡ የአገሪቱ መድን ኢንዱስትሪ ለውጥ ያሻዋል የሚሉት አቶ አሰግድ፣ ኢንዱስትሪው ማደግ ያለበትን ያህል እንዳላደገ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ጎላ ያሉ ችግሮች እየታዩበት እንደመጣ ስሚነገር፣ ዳዊት ታዬአቶ አሰግድን በመድን ኢንዱትሪው ልዩ ልዩ ችግሮች ዙሪያ አቶ አሰግድን አነጋግሯቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- የአገሪቱን የመድን ኢንዱስትሪ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ አሰግድ፡- የአገራችን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በበርካታ ችግሮች የተበተበ ነው፡፡ ኢንሹራንስ እዚህ አገር ውስጥ ብዙም የተወለደ አይደለም፡፡ እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ውስጥ በንጉሡ ዘመን የነበሩት ኩባንያዎች በነጮች የተመሠረቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች የመንግሥት ለውጥ ሲደረግ በደርግ ተወርሰው፣ በወቅቱ ብቸኛው የአሁኑ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ተመሠረተ፡፡

በንጉሡ ጊዜ የነበረው የሊበራሊዝም አስተሳሰብ ይመራ የነበረው ካፒታሊዝም ሳያ ውድድር ላይ ተመሥርቶ የተጀመረው የመድን አሠራር፣ ባህሪውንና ይዘቱን ሳይለቅ በዕዝ ኢኮኖሚ ውስጥ ለማለፍ ተገደደ፡፡ ከአንዱ ወደ ሌላኛው ሥርዓት መሻገር የነበረባቸው የመድን ዕውቀቶች፣ የአሠራር ባህሎች፣ ልምዶችና ዲሲፕሊኖች ሌላ መልክና ቅርፅ በያዘ ርዕዮተ ዓለም ውስጥ ወደቁ፡፡ በዕዝ ኢኮኖሚ መዋቅር ውስጥ በወቅቱ የተቋቋመው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አሠራርም በዚሁ ሥርዓት መነጽር የተቃኘ ሆነ፡፡ የሞኖፖል ቅርፅ ያዘ ማለት ነው፡፡ በንጉሡ ዘመን የነበሩት ግን የውድድር መንፈስ የያዙ ነበሩ፡፡ የሠለጠነው ዓለም የመድን ፖሊሲዎች የሚሸጡበት ወቅት ነበር፡፡ መድን ድርጅት ሲፈጠር ግን ገበያው በሞኖፖል ተያዘ፡፡ ይህም ኢንዱስትሪውን ውድድር አልባ አደረገው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የመድን ተገልጋዮች በሁለት የተለያዩ ርዕዮተ ዓለማት ውስጥ ወደቁ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ታሪክ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው አካሄድ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል ብዬ አምናለሁ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ተፅዕኖው በምን መልኩ እንደሚገለጽ ቢያብራሩት?

አቶ አሰግድ፡- ውድድሩ ቀርቶ በሞኖፖል ሲያዝ፣ የኢንሹራንስ ዓረቦን ዋጋ በአንድ ኢንሹራንስ ኩባንያ ብቻ ተቀርፆ የሚቀርብ ሆነ ማለት ነው፡፡ በዚህ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ኢንዱስትሪው በድጋሚ ነፃ ሲደረግ እንደገና ለተገልጋዩ በውድድር ላይ ተመሥርቶ ቀረበ፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ የኢንሹራንስ አሠራሩ ሒደት የተቀያየረና የተዘበራረቀ እንዲሆን ያደርገዋል ማለት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ሰነዶችን ወደኋላ ሄደን ስናይ፣ በንጉሡ ጊዜ የነበሩ የኢንሹራንስ ፖሊሲዎች፣ ከፖሊሲዎቹ ጋር ተያይዞ ለደንበኞች የሚቀርብላቸው መግለጫ፣ የሒሳብ አሠራር ሥርዓቱ፣ የሰው ኃይል አጠቃቀሙ፣ ሥራን ከደንበኛ ወደ ኩባንያዎቹ የሚያደርሱት የመሐል ተዋናዮች ሁሉ የምዕራባውያንን የአሠራር ቅኝት የተከተሉ ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢንዱስትሪው በተለያዩ ሥርዓቶች ውስጥ ማለፉ ከኢንዱስትሪው ጉዞ አኳያ ያስከተለው ለውጥ በምን መልኩ ይገለጻል?

አቶ አሰግድ፡- የኢንሹራንስ ዕውቀት ወደ መቀጨጩ፣ ቋንቋውም በተገቢ ሁኔታ ወደ ኅብረተሰቡ አለመድረሱ፣ በአንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ ጥላ ሥር መውደቅ፣ የራሱን ተፈጥሯዊ ዕድገት አለማሳየቱ፣ ደንበኞች የሚፈልጓቸው ፖሊሲዎች እንደልብ እንዳይገኙና ያሉት ብቻ እንዲቀጥሉ አድርጓል፡፡ የአልግሎት ብዝኃነት እንዳይኖር አድርጓል፡፡ በሞኖፖል ስትሠራ ሁሉን ራስህ ነህ የምትቀርበው፡፡ ዋጋውንም የምትወስነው አንተ ነህ፡፡ የገበያ ጥናት አካሂደህ ደንበኞች የሚፈልጉትን ዲዛይን አድርገህ ካላቀረብህ ተመሳሳይና ልማዳዊ ፖሊሲዎች እንደነበሩ ይቀጥላሉ ማለት ነው፡፡ ልማዳዊ ነው ሲባል የኢንሹራንስ ባህርይና ለዛ ለብዙ ዓመታት ሳይለዋወጥ ተመሳሳይ ሆኖ ከቀጠለ ፈጣን ለውጥ የለውም ማለት ነው፡፡ የኢንሹራንስ ተጠቃሚውን ፍላጎት እያዩ አዳዲስ ፖሊሲዎችን እያዘጋጁ አለመሄድ ማለት ነው፡፡ ውድድር ሲኖር ግን ኩባንያዎች የተሻለ የኢንሹራንስ አገልግሎት ያቀርባሉ፡፡ የተገልጋዮችን ፍላጎት የተከተለ አገልግሎት ይዘው ይመጣሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ያኔም ሆነ ከዚያም በፊት የኢኮኖሚ ማዕቀፉ የካፒታል ምሥረታን የሚከለክል ነበር፡፡ ሰዎች ሀብት ለመፍጠር ያላቸውን ፍላጎት ይዘጋል፡፡ ሰዎች ሀብት ካልፈጠሩ ዕድገት የለም ማለት ነው፡፡ ዕድገት ከሌለ ኢንሹራንሱም ይጎዳል፡፡ ኢንሹራንስ ድጋፍ ሰጭ ነው፡፡ ኢኮኖሚውን የሚቆጣጠር  ነው፡፡ ይኼ ባለመኖሩ ግን የኢንሹራንስ ዕድገቱን አንድ ቦታ እንዲገታ አድርጎታል ማለት ነው፡፡ በሞኖፖል ተይዞ ስለቆየም ዕድገቱ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ከንጉሠ ነገሥቱ በኋላ በለውጡ ምክንያት ኢንዱስትሪው በሞኖፖል ስለተያዘ ዕድገቱ ቢጓተትም ደርግ ከወደቀ በኋላ ግን በሩ ዳግመኛ ለውድድር ተከፍቷል፡፡ ይህም ሆኖ ኢንዱስትሪው እንደሚፈለገው አላደገም፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ ቢያብራሩ?

አቶ አሰግድ፡- አሁን ለውድድሮች ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው የኢንሹራንስ ሥራ በአራት መሠረታዊ ችግሮች ውስጥ የወደቀ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ የቆይታውን እና የሚገባውን ያህል ለውጥ አልመጣም፡፡

ሪፖርተር፡- የተፈለገውን ለውጥ ሊያመጣ ያልቻለበት ምክንያት ምንድን ነው? እንደ ዋና ዋና ችግሮች የሚጠቅሱትስ ምንድናቸው?

አቶ አሰግድ፡- ለምሳሌ የተቀየረ የኢንሹራንስ ፖሊሲ የለም፡፡ በአብዛኛው ተመሳሳይ አገልግሎቶች ናቸው ያሉት፡፡ የበሰለ የኢንሹራንስ ምርምርና ጥናት አይካሄድም፡፡ በዚህ የተነሳ ደንበኞች የሚፈልጉትን አላገኙም፡፡ ስለኢንሹራንስ ጠቀሜታ የሚሰጠው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በጣም አዝጋሚ ነው፡፡ ተቋማዊ ያልሆነ፣ አንዳንዱ እንደውም ኢንሹራንስም የማይመስል አገልግሎት አለ፡፡ ይኼ አገልግሎቱ ላይ የሚታይ ችግር ነው፡፡ ስለዚህ የምርት ልማትና ምርምር በእጅጉ ያልታየበት ሆኖ መቀጠሉ የኢንዱስትሪ ችግሮች ናቸው፡፡ አሁን የምናየው የውድድር መንፈስ በዓረቦን ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከፍተኛ የአረቦን ቅናሽ ውድድር አለ፡፡ ይህ ጥቂቶች ገበያውን የሚጫኑበት ባህሪይ (ኦሊጎፖሊ) ሊሆን ይችላል፡፡ እንዲህ ባለው ገበያ  ውስጥ የዋጋ ጦርነት አለ፡፡ የዋጋ ጦርነት ብቻም ሳይሆን ሌሎች በርካታ የመወዳደሪያ ስልቶች መኖር ነበረባቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ የኢንዱስትሪው የካሳ ክፍያ አስተዳደር እጅግ አሰልቺ ነው፡፡

ሌላው ችግር የሰው ኃይል አጠቃቀሙ ነው፡፡ ኢንሹራንስ ምን እንደሆነ የሚያውቁ አገሮች በነበሩበት ዘመን፣ ኢትዮጵያ የመድን ኢንዱስትሪ ነበራት፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ዕውቀት ደረጃ አሳሳቢ፣ እንዲያውም እጅግ አሳፋሪ እየሆነ መጥቷል ሊባል ይችላል፡፡ ትልቅ የዕውቀት ችግር አለ፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በዚህ ኢንዱስትሪ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ቀዳሚ ከሆነች ዘግይተው ከኋላ በጀመሩ አገሮች በኢንዱስትሪው መቀደሟስ ለምንድን ነው?

አቶ አሰግድ፡- ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለማደግ የሚያስቀምጡት ራዕይ ነው፡፡ የኩባንያዎች ራዕይ ምንድነው? እንደ ሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ ትርፍ እንደልብ እያገኙ መውጣት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ኢንሹራንስ በዳበረ ካፒታልና ኢንቨስትመንት መታገዝ አለበት፡፡ አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ በቂ ካፒታል ሊኖረው ይገባል፡፡ የሥጋት ቁጥጥሩ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ አገልግሎቱም ዕውቀት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ ለምን ሊደክም ቻለ ከተባለም እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው ቁጭ ተብሎ በበሰለና በሠለጠነ መንገድ ለረዥም ጊዜ ውጤት ሊያመጣ በሚያስችል ደረጃ በሰው ሀብት ልማት ላይ አልተሠራም፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መሠረታዊ ለውጥ የሚመጣው በሰበሰቡት ካፒታል ብቻ ሳይሆን፣ ካፒታሉን በሚያንቀሳቅሰው የሰው ጭንቅላት ጭምር ነው፡፡ ኢንሹራንስ ይበልጡኑ በሰው ልጅ ጭንቅላት ላይ የተንጠለጠለ ሥራ ነው፡፡ በባህሪው የማይጨበጥ ስለሆነ፣ ይህንን አገልግሎት በደንበኞች ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሰው ኃይል ማፍራቱ ላይ ብዙ መሠራት አለበት፡፡ ግን አልተሠራም፡፡ በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ የመተካካት ዕቅድ የለም፡፡ ሌላው ለአገሪቷ የሚመጥን ኢንስቲትዩትም የለም፡፡   

ሪፖርተር፡- የሥልጠና ተቋም ማለት ነው?

አቶ አሰግድ፡- አዎን፡፡ የኢንሹራንስ ማሠልጠኛ የለም፡፡ ኢንሹራንስ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ መሰጠት አለበት፡፡ የኢንሹራንስ ማሠልጠኛ ተቋም ያለመኖሩ በኢንዱስትሪው ዕድገት ላይ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ ከዚህ ቀደም ግን አንድ ተቋም ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሥር የነበረው የባንክና የኢንሹራንስ ባለሙያዎች ማሠልጠኛ ተቋምን ማለትዎ ነው?

አቶ አሰግድ፡- አዎን፡፡ ይህ ማሠልጠኛ ተቋም ወደ ፋይናንስ አካዴሚ እንዲያድግ ተሞክሮ ሕንፃዎችም ተገንበተው ነበር፡፡ አካዴሚው በመጀመሪያ ዲግሪ ደረጃ የኢንሹራንስ ትምህርት ሊሰጥበት የታሰበ ነበር፡፡ የባንክና የኢንሹራንስ ባለሙያዎችን ለማሠልጠን ያስችላል ተብሎ የታነፀ ነበር፡፡ ግን በመንገድ ቀረ፡፡ ኢንሹራንስና ባንክ ከ50 ዓመታት በላይ ዕድሜ ቢኖራቸውም እንደ አገር ይህንን ዘርፍ የሚደግፍ አንደም ኢንስቲትዩት የለም፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ የሚፈልገውን ጥያቄ የሚያሟላ አቅርቦት ያለው ተቋም የለም፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች አያስተምሩም፡፡ የተወሰነ ኮርስ ነው የሚሰጡት፡፡ ስለዚህ ዘርፉን የሚመግብ ብሔራዊ የትምህርት ተቋም የለም፡፡ ከዓመታት በፊት አገልግሎት ሲሰጥ የነበረው ማሠልጠኛም ተዘግቷል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ ባለሙያዎች ሥራቸውን ሊያራምዱ የቻሉት በነበረው ማሠልጠኛ በዲፕሎማ ደረጃ የኢንሹራንስ ትምህርት ይሰጥ ስለነበር በዚያ ታግዘው ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የማሠልጠኛው የትምህርት አሰጣጥ እንዴት ነበር?

አቶ አሰግድ፡- በዚያን ወቅት የነበረው ተቋም በተለያዩ የኢንሹራንስ ምርቶች የታገዘ ትምህርት ይሰጥ ነበር፡፡ በዲፕሎማና በሰርተፍኬት ደረጃ የሚሰጡ የኢንሹራንስ ትምህርቶች ነበሩ፡፡ የመድን ሥራ ፖሊሲዎች ላይ ጥልቅ ሥልጠና የሚሰጥበትም ነበር፡፡ እሱ አሁን የለም፡፡ ሌላው በቀደመው ጊዜ ኩባንያዎች ከሰው ኃይል ብቃት ጋር የሚከተሉት አንድ አሠራር ነበራቸው፡፡ ይኽም ተማሪዎችን ከዩኒቨርሲቲ ይወሰዱና ያሠለጥናሉ፡፡ እንደ ቴሌ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ ተቋማት ከዩኒቨርሲቲ የወሰዷቸውን ተማሪዎች በተቋሞቻቸው ለወራት ያሰለጥናሉ፡፡  መድን ድርጅት የተቀበላቸውን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኢንሹራንስ ትምህርት ዘርፍ ብቻ በየአገልግሎት ዓይነቱ ያሠለጥናቸው ነበር፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ተምረው ፈተናውን አልፈው ሥራ ላይ ሥልጠና በመውሰድ ሥራውን እንዲለማመዱ ተደርገው በዚያው መሠረት ወደ ሥራ ይገቡ ነበር፡፡ ጨምሮ በዚያ መንገድ መጥተን እንደገና በተልዕኮና በመሳሰሉት ያገኘነው ትምህርት አሁን ለምንገኝበት ደረጃ አድርሶናል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለው የሰው ኃይል ማፍሪያና ማጎልበቻ አሁን ቀርቷል ማለት ነው?

አቶ አሰግድ፡- አዎ እነዚህም ቀርተዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ሥልጠናዎች ኢንዱስትሪው ያለበትን ክፍተት በመጠኑም ቢሆን ለመቅረፍ ያግዙ ነበር፡፡ ነገር ግን በሰው ኃይል ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሀብት መፍጠር እንደሆነ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጠፍቷቸው አይደለም፡፡ በቅርቡ ግን በብሔራዊ ባንክ በኩል እያንዳንዱ የኡንሹራንስ ኩባንያ ከዓመት በጀቱ ሁለት በመቶውን ለሥልጠናና ልማት እንዲያውል ተደንጎበታል፡፡ ይህ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ኩባንያዎቹ ራሳቸው ይህንን ማድረግ ነበረባቸው፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ ልዩነት ማምጣት ከፈለጉ ለውጥ የሚያመጡት የሰው ኃይላቸውን በማብቃት ነው፡፡ በአንፃሩ ግን የሰው ኃይሉ አይበረታታም፡፡ ትኩረት አይሰጠውም፡፡ ዓለም ግን እየተቀየረ ነው፡፡ አዳዲስ ዕውቀቶች፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ አዳዲስ አሠራሮች  እየመጡ ነው፡፡ የበፊቶቹ እየወጡ ነው፡፡ እኛ ግን በነበረው እየሔድን ነው፡፡ የሰው ኃይሉ እንዳያድግ እንቅፋት የሆነው ራሱን የቻለ ተቋም በዘርፉ አለመኖሩ ነው፡፡ እዚሁ አጠገባችን እንደ ኬንያ ያሉ እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገሮች ኢንስቲትዩቶች አሏቸው፡፡ እነዚህ አገሮች በየዩኒቨርሲቲዎቻቸው ውስጥ የባንክና የኢንሹራንስ ትምህርት በዲግሪ ያስተምራሉ፡፡ እኛ አገር ውስጥ ግን ይህ የለም፡፡ የነበረውም እየተዳከመ ሄዷል፡፡

ሪፖርተር፡- ከገለጻዎ ለመረዳት እንደሚቻለው የሰው ኃይል ልማቱ ላይ አለመሠራቱ ክፍተት ፈጥሯል፡፡ ስለዚህ ለኢንዱስትሪው መንቀራፈፍ በተለይ በሞተር ኢንሹራንስ ላይ ተንጠላጥሎ ለመቆየቱ ምክንያት በሰው ኃይል ማብቃት ላይ አለመሠራቱ ሊሆን ይችላል ማለት ነው?

አቶ አሰግድ፡- በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በብዙዎቹ አገሮች ኩባንያዎች ውስጥ ትኩረት የሚሰጠው ቶሎ ዓረቦን መሰብሰብ የሚቻልባቸው አገልግሎቶች ላይ ነው፡፡ በቀላሉ ገንዘብ የምታገኝበትና የአንድ ዓመት ፖሊሲ በብዛት የምታገኝበት የሞተር ኢንሹራንስ ነው፡፡ 90 በመቶው በሞተር ኢንሹራንስ የሚንቀሳቀስ ገበያ ነው፡፡ ኢንሹራንስ ማለት  የሞተር ኢንሹራንስ ብቻ የሚመስላቸው አሉ፡፡ ኢንሹራንስ እሱ አይደለም፡፡ እስከ ጠለፋ ዋስትና ድረስ ይጓዛል፡፡ ሞተር ኢንሹራንስ የገነነው ለኅብረተሰቡ የተገለጸበት መንገድ ችግር ስላለበት ነው፡፡ ጥቂት ኩባንያዎች ናቸው የሠራተኛ ጉዳት ሽፋን ሲሰጡ የነበሩት፡፡ በአገራችን ግንዛቤ ሀብት የማፍራት አንዱ መገለጫ መኪና መግዛት ነው፡፡ መኪና አደጋ ያደርሳል፡፡ የቃጠሎ ኢንሹራንስ ከመኪና እኩል ሊሸጥ ይችል ነበር፡፡ ስለዚህ ከዕውቀት ማጣት ሳቢያም ከፍተኛ የሆነ የኢንሹራንስ ምርት ሥራ ውስጥ አልገባንም፡፡ የምናያቸውም ቢሆንም ያኔ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የነበሩ እንደ ኃይል ማመንጫ ላሉት ሽፋን የሚሰጣቸው በኢትዮጵያ መድን ድርጅት ነበር፡፡ ይህም የሆነው ሞኖፖል ይሠራ ስለነበር ነው፡፡ በንጉሡ ጊዜ ግን ከሞተር ኢንሹራንስ ውጭ የተለያዩ ፖሊሲዎች ይሸጡ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ባሉት የኢንሹራስ ኩባንያዎች የማይተገበሩ ከሚባሉት ውስጥ ለምሳሌ የሚጠቅሱት አለ?

አቶ አሰግድ፡- አዎን፡፡ ለምሳሌ የቤት ፖኬጅ ፖሊሲ ይሸጥ ነበር፡፡ የቃጠሎ ኢንሹራንስ ፖሊሲ ይሸጥ ነበር፡፡ ለቤት ንብረቶችህ ዋስትና የሚሰጡ የኢንሹራንስ ፖሊሲዎች ይሸጡ ነበር፡፡ እነዚህ ፖሊሲዎች የነጮቹ ነበሩ፡፡ የንጉሡ ጊዜ የኢንሹራንስ ፖሊሲዎችን እንደናሙና አውጥቶ ማየት ይቻላል፡፡ አንዳንድ አገሮች ኢንሹራንስ ምን እንደሆነ በማያውቁበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የኢንሹራንስ ፖሊሲ ይሸጥ ነበር፡፡ ሌላው ኢንሹራንስ በጣም ፈጣን ለውጥ ሳይኖረው እንዳይቀጥል ያደረገው የኢንሹራንስ ትምህርት የወሰዱ ሰዎች ዘርፉን አለማስተዋወቃቸው ነው፡፡ የሚሰጡት አስተያየት አይደመጥም፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ 17 የመድን ኩባንያዎች አሉ፡፡ ከአብዛኛዎቹ ኩባንያዎች እንደሚደመጠው የኩባንያዎቹ የዓረቦን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እያሽቆለቆለ እንደመጣ ነው፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት እስከ ሦስት እጥፍ የቀነሱ አሉ፡፡ ይህ የዓረቦን ቅናሽ ምን ያመለክታል?

አቶ አሰግድ፡- ሁለት ነገር አለ፡፡ የኢንሹራንስ መሠረታዊ ዓረቦን የምንለው አለ፡፡ ይኼ ለዓመታት ተሠርቶ የሚመጣ ነው፡፡ ይህ ግን የማይለወጥ መሆን የለበትም፡፡ እዚህ ላይ ክርክሩና ዕውቀቱ ሁለት ነው፡፡ አንድ ቦታ ላይ የቆመ መሆን የለበትም፡፡ ያለማቋረጥ መውረድም የለበትም፡፡ መጠናት አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ማኅበር በዚህ ዙሪያ ባለሙያ ቀጥሮ ጥናት እያስጠና መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ጥናቱ አገር ውስጥ ያሉትን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የዓረቦን ሁኔታ የዳሰሰ ሊሆን ይችላል፡፡ ዝቅተኛ የዓረቦን ዋጋ ሊቀመጥላቸው የሚገባቸው የኢንሹራንስ ዘርፎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ሥጋቱን ሊመጥን የሚችል ዓረቦን ያስፈልጋል፡፡ መተንተንና መታወቅ ያለበት ነገር ሥጋቱን ሊመጥን የሚችል ዓረቦን እንዴት ነው የሚንቀሳቀሰው የሚለው ነው፡፡ አንድ ደንበኛ ኢንሹራንስ ገብቶ እሱ ያስመዘገበው አደጋ ስለሚያደርሰው ጉዳት አይደለም፡፡ ኢንሹራንስ አንድ ለአንድ አይደለም፡፡ በአንድ ደንበኛ ብቻ የሚተዳደር የኢንሹራንስ ኩባንያ የለም፡፡ ዓረቦኑ ወደ ስብስብ የመጡ ደንበኞችን በሙሉ አስተናግዶ ከስብስቡ ውስጥ በጣም ጥቂት ዕድለኛ ያልሆኑት የሚያስመዘግቡትን የአደጋ ወጪና ሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎችን ሸፍኖ አትራፊ መሆን አለበት፡፡

ስለዚህ ዓረቦኑ ለአደጋው ሥጋት ተመጣጣኝ መሆን አለበት፡፡ በገበያ ተፈላጊም መሆን አለበት፡፡ ለሥጋቱ ተመጣጣኝ ይሆናል ብለህ የዓረቦኑን ዋጋ ብትሰቅለው ማንም አይገዛህም፡፡ ምክንያቱም አሁን ያለው ደንበኛ ስለ ኢንሹራንስ ግንዛቤ ያለው ነው፡፡ አሁን ባለው ቴክኖሎጂ ባነሰ ዋጋ ሰፋ ያለ ጥቅም ማግኘት የሚፈልግ ነው፡፡ ደንበኛው ይኼ አመለካከት አለው፡፡ ስለዚህ ስታጠና ሊያዋጣህ የሚችለውን ዓረቦን መስጠት አለብህ፡፡ ሊያዋጣ ይችላል ያልከውን የዓረቦን ዋጋ ስታስቀምጥ ውድድርም አለብህ፡፡ የተለያዩ ኩባንያዎች የተለያየ መነሻ አያላቸው፡፡ አንዳንዱ የራሱ ሕንፃ አለው፡፡ አንዳንዱ ተከራይቶ ነው የሚሠራው፡፡ የአንዳንዱ የሰው ኃይልና የሚከፍለው የደመወዝ መጠን እና የሚጠቀምበት ቴክኖሎጂም ይለያያል፡፡ እነዚህን ወጪዎች አስልተህ የዓረቦን ዋጋህን ታሰላለህ፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ እንዴት ነው የሚብራራው?

አቶ አሰግድ፡- ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያ ጋ ስትሄድ ዓረቦን ወረደ ይላሉ፡፡ ይኼ ስህተት ነው፡፡ ኢንሹራንስ ዓረቦንም ወርዶ ብዙ ተሠርቶ ወጪህን ተቆጣጥረህ አሸናፊ የምትሆንበት የአሠራር ሥርዓት አለው፡፡ ውድድሩ የገበያ ባህሪይ ነው፡፡ የኦሊጎፖሊ ገበያ ላይ እንደዚህ ዓይነት ጦርነት ይኖራል፡፡ ነገር ግን እኔ እንደማምነው አረቦን መሆን ያለበት ሥጋቱን የሚመጥን መሆን እንዳለበት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት አሥር ዓመታት እየወረደ የመጣው የዓረቦን መጠን አሁን በሚታየው መጠንም ወርዶ እየተሠራበት ነው፡፡ ኩባንያዎቹም አትራፊ ናቸው፡፡ ቅናሹ እየሰፋ መምጣቱ ግን ለኢንዱስትሪው አደጋ ሆኗል እየተባለ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ብሔራዊ ባንክም ደርሷል፡፡ ሥጋቱ የብዙዎች የሆነው ለምንድነው? ያልተገባ ዋጋ እየተሰጠ ነው የሚባለውስ ለምንድነው?

አቶ አሰግድ፡- ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያ አንድ ዓይነት ዓረቦን ሊኖረው አይገባም፡፡ ውድድር መኖር አለበት፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የበለጠ እያከሰራቸው ያለው ሁለተኛውን ክንፍ የኪሳራ ክፍያ ሥርዓታቸውን መርሳታቸው ነው፡፡ የዋጋ ንረት አለ፡፡ ዓረቦኑ ግን ከዋጋ ንረቱ አኳያ አልተስተካከለም፡፡ ብዙ አደጋ ግን እየደረሰ ብዙ ካሳም እየተከፈለ ነው ፡፡ ይኼ ነው ትልቁ ነጥብ እንጂ የሥር መነሻው ተመን አይደለም፡፡ ተመኑን እንዲህ አድርግልን ብሎ ወደ ብሔራዊ ባንክ መሄድ ተገቢ አይደለም፡፡ ነፃ የገበያ ሥርዓት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በነፃ ገበያ ሥርዓት መመራት እንዳለበት ግልጽ ነው፡፡ ብሔራዊ ባንክም የዓረቦን ዋጋውን ተመን ሊያስቀምጥ ይችላል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ አሁን እየታየ ያለው ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ መምጣቱ ግን አደጋ አለው የሚለው ጎልቶ እየተሰማ ነው፡፡ ስለዚህ መፍትሔ ያስፈልገዋል፡፡

አቶ አሰግድ፡- አዎ ብሔራዊ ባንክ ዋጋ ይተክላል ብዬ አላስብም፡፡ አይጠበቅበትም፡፡ ኩባንያዎች ግን አሸናፊ ሆነው ለመውጣት የራሳቸውን ሥራ መሥራት አለባቸው፡፡ ሌላ አካል ሠርቶላቸው አይደለም አትራፊ የሚሆኑት፡፡ የራሳቸውን ዓረቦን ቀርጸው የሚሸጡ ከሆነ ወጪያቸውን ተቆጣጥረው አሸንፈው ይወጣሉ፡፡ በነገራችን ላይ አሜሪካን ፕሮግሬሲቭ የሚባል የኢንሹራንስ ኩባንያ አለ፡፡ ይህ ኩባንያ ሞተር ኢንሹራንስ ላይ ብቻ ነው የሚሠራው፡፡ በጣም አትራፊ ኩባንያ ነው፡፡ በየጊዜው ዓረቦኑን ያስተካክላል፡፡ የዋጋ ንረት ሲከሰት ለዚያም ማስተካከያ አለው፡፡ ለደንበኞቹም ቅናሽ የሚያደርገበት አሠራር አለው፡፡ የዓረቦን ዋጋው መውረዱን ብቻ ነው ብዙዎቹ እያወሩ ያሉት፡፡ እኔ የምስማማበት ግን የካሳ ክፍያ ሒደታችን የተባባሰ በመሆኑ የበለጠ እየወረደ ያለውን ዓረቦን እንዲባባስ ማድረጉ ላይ ነው፡፡ በፍጥነት የካሳ ክፍያ ላይ ብንሠራ በፍጥነት የመለዋወጫ ዋጋቸው ሳይንር የመካስ ዕድል ይኖረናል፡፡ አንድ መኪና አደጋ ቢደርስበት በወር ውስጥ ብጠግን አሁን የምጠግንበት ዋጋና ከወር በኋላ የምጠግንበት ዋጋ ይለያያል፡፡ ስለዚህ የካሳ ክፍያውን ፈጣን በማድረግ አሁን ባለውም ዓረቦን ቢሆን ከሙስና በፀዳ አሠራር አትራፊ ይሆናሉ፡፡ እያከሰራቸው ያለውን ይኸኛውን ጉዳይ ረስተውታል፡፡ ይኼ የተረጋገጠ  ነገር ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ከሚጠቀሱት ተቋማት በተለይ ከባንኮች አንፃር ሲታይ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አካሄድ ዕድገቱ አዝጋሚ ነው፡፡ ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ያሳዩት ውጤት ከባንኮች ጋር ሲመዛዘን በፍፁም የሚገናኝ አይደለም፡፡ የዓረቦን ዋጋው እየወረደ መምጣቱም ኢንዱስትሪውን ሊጥለው ይችላል ይላሉ፡፡ በእርግጥ የዓረቦን እየወረደ መምጣት ምክንያት በአሁኑ ወቅት ሥጋት አለ?

አቶ አሰግድ፡- የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውድድር ዓረቦንን በመቀነስ ብቻ መሆኑ ወይም አንድ ነገር ላይ ያጠነጠነ መሆኑ ራሳቸውን ወደ መብላት ይወስዳቸዋል፡፡ ኢንዱስትሪው ተጠፍንጎ የተያዘው በሌሎችም በርካታ ችግሮች ጭምር ነው፡፡ ዓረቦን አንደኛው ማሳያ ነው፡፡ ያልተገባ የካሳ ክፍያም እየከፈሉ ነው፡፡ በኢንሹራንስ ካሳ ክፍያ መክሰርም ማትረፍም አይቻልም፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ምን ማለት እንደሆነ ቢገልጹት?

አቶ አሰግድ፡- የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ዋና ዓላማ አንድ ደንበኛ አደጋ ሳያደርስ ወደ ነበረበት ቦታ መወሰድ ነው፡፡ ነገር ግን እየወሰዱት አይደለም፡፡ የ1990 ሞዴል መኪና ዘንድሮ አደጋ ቢደርስበት እናስጠግናለን፡፡ ያገለገለ መኪና ነው፡፡ ዕድሜው የገፋ መኪና ነው፡፡ አዲስ ዕቃ ከገበያ አምጥተን ነው የምንቀይረው፡፡ የአሮጌውን የዕርጅና ተቀናሽ ከአዲሱ ላይ ቀንሰን ነው በጥሬ ገንዘብ የምንከፍለው፡፡ እንደፈለገን ብንቀንስም በዚህ አሠራር ደንበኞችን አትራፊ እናደርጋለን ማለት ነው፡፡ ዓረቦኑ ለዋጋ ንረት ማስተካከያ የለውም፡፡ ካሳ ክፍያው ግን ሁሌም በንረት ውስጥ ነው፡፡ የአገልግሎትና የዕቃ ዋጋ ግን እየጨመረ ነው፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይህንን ማመጣጠን አለባቸው፡፡ የሚያመጣጥኑትም ሳይቀንሱ ብዙ በመሥራት የካሳ ክፍያቸውን ቢያስተካክሉ፣ አዳዲስ አገልግሎቶችን ይዘው ቢመጡ የተሻለ አማራጭ ይፈጥራሉ፡፡ እኔ በጣም እየገረመኝ ያለው በዓረቦን መውረድ ላይ ብቻ ያጠነጠኑ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ በጣም ስህተት ነው፡፡  ብዙ ስትሠራ ታገኛለህ፡፡ አሁን ያለው እኮ የዛሬ 40 ዓመት በኢትዮጵያ መድን ድርጅት የነበረ መሠረታዊ ዋጋ ነው፡፡ አሁን እኮ እየተቀነሰ ያለውም ከዚህ ነው፡፡ ስለዚህ ኩባንያዎች ራሳቸውን ወደ መብላት እየሄዱ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን መጠኑ እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ አምስት በመቶ አካባቢ ነው፡፡ በሌላው ዓለም ግን ከጠቅላላው የኢንሹራንስ ሽፋን አብላጫውን እጅ የያዘው የሕይወት ኢንሹራንስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ለምን ተለየ? አምስት በመቶ ላይ ብቻ ለምን ቆመ?

አቶ አሰግድ፡- ሌላው ዓለም ይህንን ገንዘብ በተለያየ መንገድ ኢንቨስት አድርጎ ተጨማሪ ትርፍ የሚያገኝት ዕድል አለው፡፡ እዚህ አገር ግን የለም፡፡ ለኢንቨስትመንቱ ምቹ የሆኑ የፖሊሲ ማዕቀፎች የሉም፡፡ ስለዚህ በሕይወት ኢንሹራንስ የሰበሰብከውን ዓረቦን ልታደርግ የምትችለው ነገር በጊዜ ገደብ ታስቀምጣለህ፡፡ ከዚህ የምታገኘው የወለድ ጥቅም ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በሕይወት ኢንሹራንስ ፖሊሲ ላይ ከባንክ ከምታገኘው ወለድ ውጭ በዚያ ዓረቦን ልትጠቀምበት የምትችልበት ዕድል የለም፡፡ ስለዚህ አላደገም፡፡

ሪፖርተር፡- ለሕይወት ኢንሹራንስ እጅግ ዝቅተኛ ሽፋን ምክንያት ይህ ብቻ ነው?

አቶ አሰግድ፡- ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ካፒታሉም እያለ አላደገም ለማለት ነው፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ ከፍተኛ የግንዛቤ ክፍተት ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሠሩት ነገር የለም፡፡ የሕይወት ኢንሹራንስ ፕሮጀክቶችም ልማዳዊ ናቸው፡፡ የዛሬ 50 ዓመት የነበሩ የሕይወት ኢንሹራንስ ፕሮጀክቶች ናቸው ዛሬም እየተሸጡ ያሉት፡፡ ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚሸጡት እነዚህኑ ነው፡፡ ተለዋዋጭነት ይጎለዋል፡፡ ለደንበኞች ምቹ ፖሊሲዎች የለም፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ዘርፍ ኩባንያዎቹ መሸጥ የሚችሏቸው የሕይወት ኢንሹራንስ ፖሊሲዎች ወይም አገልግሎቶች ካሉ?

አቶ አሰግድ፡- ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት ቤቶች ተስፋፍተዋል፡፡ ልጆች ትምህርት ቤት ነው የሚውሉት፡፡ ነገር ግን ለትምህርት ቤት የሚሰጥ የኢንሹራንስ ፖሊሲ የለም፡፡ በስፖርቱም ዘርፍ ስንሄድ ስፖርቱ እየሰፋ ነው፡፡ የአንድ ስፖርተኛ ዋጋ በሚሊዮን ብር ደረጃ እያደገ ነው፡፡ ይህንን የሚሸፍን የኢንሹራንስ ፖሊሲ የለም፡፡ የሕይወት ኢንሹራንስ ፖሊሲ ከሰው ሕይወት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሕይወትን ከእምነት ጋር በማያያዝ ለረዥም ጊዜ የቆየ ማኅበረሰብ ስለሆነ፣ ይህንን አመለካከት ለመቀየር ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሠሩት ነገር የለም፡፡ ግንዛቤ የማስጨበጡ ሥራ በተለመዱ ነገሮች ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መፍትሔው ታዲያ ምንድን ነው?

አቶ አሰግድ፡- የኢንሹንስ ኩባንያ እንዲያድግ አሁን ዓለም የደረሰበትን የኢንሹራንስ አስተሳሰብ የተከተለ መሥረታዊ ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል፡፡ ለውጡ ጥገናዊ ለውጥ ሳይሆን፣ ሥር ነቀል ለውጥ መሆን ይኖርበታል፡፡ ዓረቦን ላይ በመሥራት ብቻ ዘርፉን የትም አያደደርሰውም፡፡ ዓረቦንን በማስተካከል የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ዓረቦን አንድ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ ቆሼ ላይ ለደረሰው አደጋ አንድም ኩባንያ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ይህ የሚያሳየው ዘርፉ እዚህ ድረስ የወረደ መሆኑን ነው፡፡ ለዚህ ነው ለውጥ የሚያስፈልገው፡፡ ኢንዱስትሪው በዕውቀት ላይ የተመሠረተ አመራር ሊኖረው ይገባል፡፡ ኢንሹራንስ ዕውቀት ነው፡፡ በዘልማድ ወይም በቆይታ የሚመራ አይደለም፡፡ በኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂ መታጠቅ አለበት፡፡ ይህ ከሆነ ለውጥ ሊመጣ ይችላል፡፡ 

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያለውን ለውጥ ለማምጣት ኩባንያዎች በራሳቸው መንገድ መሥራታቸው እንዳለ ሁኖ ኢንዱትሪውን ለመለወጥ እንደ ብሔራዊ ባንክ ያሉ የሚመለከታቸው ተቋማት ሚና ምን መሆን አለበት?

አቶ አሰግድ፡- ኢትዮጵያ አድጋለች፡፡ ትልቅ ነች፡፡ ባንኮች በቢሊዮን ደረጃ እያተረፉ ነው ብለናል፡፡ እዚህ ደረጃ የደረሱት ስለሠሩ ነው፡፡ ኢኮኖሚው ሲያድግ፣ ዕድገቱ ባለበት ቦታ ሁሉ ስለሄዱ ነው፡፡ ይህም ቢሆን መሠረታዊ የሆነ ችግር አለው፡፡ ባንክ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ሰዎች ካልተበደሩት ገቢ አይኖራቸውም፡፡ የባንኮች ዋና ገቢ አበድረው ከሚያገኙት የወለድ ገቢ የሚገኝ ነው፡፡ ኢንሹራንሱ ጋር ስንመጣ ይህንን ሊያሠራ የሚችል በኢትዮጵያ ስፋት ልክ የተዳረሰ አይደለም፡፡ ብሔራዊ ባንክ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር አስቀምጧል፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ኢንቨሰት የሚያደርጉበት ዕድል የለም፡፡

ሪፖርተር፡- የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከካፒታላቸው ከ15 እስከ 20 በመቶ ለተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲያውሉ ብሔራዊ ባንክ ይፈቀዳል እኮ፡፡

አቶ አሰግድ፡- እሱ አዎን አለ፡፡ ለኢንቨስትመንት ባዋሉት መጠን ሲታይ ግን ትንሽ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የብሔራዊ ባንክ መመርያ ትክክል ነው፡፡ በዚህ ደረጃ መገደቡም ትክክል የሚሆንበት ምክንያት ይኖራል፡፡ የደንበኛን የፖሊሲ ገንዘብ ሰብስበህ እንደፈለክ ማድረግ አይገባም፡፡ መቆጣጠሩ ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ተቀይራለች፡፡ ሜዳው ተቀይሯል፡፡ ሀብት እየተፈጠረ ስለሆነ የአደጋው ሥጋት ተቀይሯል፡፡ ስለዚህ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ከማሠር ይልቅ ፈታ ያለ አሠራር መኖር፣ የኢንቨስትመንት አቅማቸውም ሰፋ ማለት አለበት፡፡ በተለያዩ የአጭር ጊዜ ኢንቨስመንቶች ውስጥ እንዲገቡ መፈቀድ አለበት፡፡ ኩባንያዎች የተለያዩ ኢንቨስትመንት ሥራ ውስጥ ገብተው አትራፊ ሆነው የሚወጡበት ዕድል ቢፈጠር፣ በተለያዩ አክሲዮን ኩባንያዎች ውስጥ አክሲዮን ገዝተው ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ በንጉሡ ጊዜ የባንክ ኢንሹራንስ የሚባል ነገር ነበር፡፡ ገንዘብ ይቀበላሉ፡፡ ለተበደረው ሰው የኢንሹራንስ ሽፋን ይሰጣሉ፡፡ ይህ አሠራር እኮ ኢትዮጵያ ውስጥ ነበር፡፡ ደርግ ሲገባ ግን ቀረ፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራሮች መፈቀድ አለባቸው፡፡ ሌላው ዘርፉ እንዲያድግ ተቆጣጣሪው አካል መቀየጥ አለበት፡፡ በተቆጣጣሪው አካል ውስጥ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያሉበት ክፍል ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለው ካፒታል ግን የትም አያደርሳቸውም፡፡ የአገራችንን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከኬንያ ኩባንያዎች ጋ ሲወዳደሩ በጣም አነስተኛ ናቸው፡፡ ስለዚህ የካፒታል መጠናቸው መቀየር አለበት፡፡ በዚህ ላይ ብሔራዊ ባንክ ይሠራል ብዬ አስባለሁ፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles