ባለፈው ወር አጋማሽ አዲስ አበባን ጨምሮ በየክልሉ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች ደብዳቤዎች ወጪ ተደርገው ነበር፡፡ ደብዳቤዎቹ የደረሷቸው ደግሞ ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የብድር ጥያቄዎችን ያቀረቡ ተበዳሪዎች ናቸው፡፡ የብድር ጥያቄዎቻቸው ተገምግመው፣ ብድር ለማግኘት የሚያስችላቸው የመጨረሻው ዕርከን ላይ ቢቃረቡም ድንገት ግን ‹‹የፕሮጀክት ብድር ጥያቄ መቋረጡን ስለማሳወቅ›› በሚል ርዕስ ለብድር ፈላጊዎቹ የተጻፈው ደብዳቤ ያልተጠበቀ ዱብ ዕዳ ነበር፡፡
ሚያዝያ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በተላለፈ ውሳኔ መሠረት፣ ንግድ ባንክ ለሥራ ማስኬጃ የሚቀርቡ የብድር ጥያቄዎች ላይ ብቻ አተኩሮ እንዲሠራ በመታዘዙ ምክንያት፣ ለፕሮጀክት የሚቀርቡ ብድሮችን እንደማያስተናግድ የሚጠቅስ መልዕክት የያዘ ደብዳቤ ተሰራጭቷል፡፡ ይኸው ደብዳቤ የብድር ጥያቄዎች የግምገማ ሒደት መቋረጡንም አስታውቋል፡፡ ነገር ግን የፕሮጀክት የብድር ጥያቄዎች ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቢቀርቡ ሊስተናገዱ እንደሚችሉም ይጠቅሳል፡፡
ለብድር ፈላጊዎቹ የተጻፈው ደብዳቤ ከመሰራጨቱ ቀደም ብሎ ብሔራዊ ባንክ ልማት ባንክ በፕሮጀክት ፋይናንስ ላይ አተኩሮ እንዲሠራ ንግድ ባንም በሥራ ማስኬጃ ብድሮች ላይ እንዲያተኩር የሚያስገድድ መመሪያ አስተላልፎ ነበር፡፡ ንግድ ባንክ ለፕሮጀክት ሥራዎች የሚሰጠውን ብድር እንዲያቆም በምትኩ ልማት ባንክ ለፕሮጀክት ያበድር የሚለው ትዕዛዝ የደረሳቸው የሁለቱም ባንኮች የሥራ ኃላፊዎች ግርታ ውስጥ ቢገቡም፣ ንግድ ባንክ የተላለፈውን ትዕዛዝ መተግበር ጀምሯል፡፡
ያልተጠበቀው የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ለጅምር ፕሮጀክቶቻቸው ማስፈጸሚያ ከንግድ ባንክ ብድር እንደሚያገኙ እምነት አድሮባቸው የነበሩት ላይ ድንገተኛ መርዶ ከመሆኑ ባሻገር፣ ከአንድ ወር ቆይታ በኋላም አሁንም ድረስ ብዥታው እንደረበበ ይገኛል፡፡ የተወሰኑ ብድር ፈላጊዎች በተነገራቸው መሠረት ወደ ልማት ባንክ ቢሄዱም ጥያቄያቸውን ሊስተናገድ ባለመቻሉ ሥጋት አድሮባቸዋል፡፡
ለሚገነቡት ሆቴል ማጠናቀቂያ ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር ጠይቀው ምላሽ በመጠባበቅ ላይ የነበሩና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ባለሀብት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተላለፈው ውሳኔ ያልጠበቁት ከመሆኑም በላይ ንግድ ባንክን ተማምነው የጀመሩት ሥራ ላይ ጫና አሳድሯል፡፡
እንደ ባለሀብቱ ገለጻ፣ ለጀመሩት ግንባታ ማስፈጸሚያ የብድር ጥያቄ ከማቅረባቸው በፊት ብድሩን ለማግኘት በቅድሚያ የፕሮጀክቱን 50 በመቶ ግንባታ ማጠናቀቀቅ ነበረባቸው፡፡ ብድር የጠየቁበት ቅርንጫፍ መሐንዲሶችም የፕሮጀክቱን 50 በመቶ እንደተጠናቀቀ፣ ለቀረው የግንባታ ሥራ እንዲውል ብድር ማግኘት እንደሚችሉ ተረጋግጦ፣ አስፈላጊ ሒደቶች በሙሉ ተሟልተው ብድሩን ለማስለቀቅ ውል ለመፈራረም በሚዘጋጁበት ወቅት የፕሮጀክ ብድር መቋረጡን የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሷቸዋል፡፡ እንደ እኚሁ ባለሀብት ሁሉ ከሆቴል ባሻገር ለትምህርት ቤት፣ ለፋብሪካና ለመሳሰሉት ፕሮጀክቶች ብድር የጠየቁ ደንበኞች ግራ ተጋብተዋል፡፡
‹‹ብድር ለማግኘት የሚጠበቅብኝ የፕሮጀክቱን 30 በመቶ ግንባታ ማጠናቀቅ ነበር፡፡ ብድሩን በአስተማማኝ መንገድ ለማግኘትና ባንኩም የበለጠ እምነት እንዲኖረው ስል ከዚህም ከዚያም በማለት ገንዘብ አሰባስቤ የግንባታውን ሥራ 50 በመቶ አድርሼው ነበር፤›› ያሉት ባለሀብት፣ ያቀረቡትን የብድር ዳር ለማድረስ ከዘጠኝ ወራት በላይ እንደፈጀባቸው፣ ያቀረቧቸው ማስረጃዎችና የፕሮጀክቱ ትልመ ሐሳብ ፋይናንስ ከማግኘት እንደማያግዳቸው ግልጽ ቢሆንም፣ ባንኩ ግን የፕሮጀክት ብድር ቀርቷል በማለቱ እስካሁን ወጪ ያደረጉት ገንዘብ መና ሊቀር ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሮባቸዋል፡፡ ልማት ባንክም ለሆቴል፣ ለሆስፒታልና ለመሳሰሉት ፕሮጀክቶች ብድር አልሰጥም ማለቱን በመስማታቸው ይባስ ማጣፊያው እንዳጠራቸው ይናገራሉ፡፡
‹‹ልማት ባንክ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ አያስተናግድም የሚል ምላሽ በመስጠቱ ብድር ወደ ጠየቅንባቸው ቅርንጫፎች ተመልሰን አቤት ብንልም ይህ የብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ነው ተብለናል፤›› ይላሉ፡፡ እሳቸው ብድር በጠየቁበት መቐለ ከተማ የሚገኘው የልማት ባንክ ቅርንጫፍም እንደ እሳቸው ያሉ የብድር ጥያቄዎችን ለማስተናገድ አቅም እንደሌለው ስለተረዱ፣ የፕሮጀክት ብድር ጥያቄዎችን ያስትናግዳል መባሉ ከምን የተነሳ ነው? በማለት እንዲጠይቁ ገፋፍቷቸዋል፡፡
የኮሌጅ ባለቤት የሆኑ ሌላኛው ብድር ፈላጊም ኮሌጃቸውን ለማሳደግ ያቀረቡት የብድር ጥያቄ ውድቅ መደረጉ እንዳሳዘናቸው ገልጸው፣ ለብዙ ጊዜ ሲጠብቁ ቆይተው ቀርቷል የሚል ውሳኔ መተላለፉ አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡
ከአስተያየት ሰጪዎቹ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ብሔራዊ ባንክም ሆነ ንግድ ባንክ እንዲህ ያለውን ውሳኔ ከመወሰናቸው በፊት ቢያንስ ግምገማ ላይ የነበሩና የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ የደረሱ ጥያቄዎች እንዲስተናገዱ መፍቀድ ነበረባቸው ይላሉ፡፡ ለፕሮጀክቶች ብድር መስጠት ያለበት ልማት ባንክ ቢባልም ባንኩ ግን የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች እንደማያስተናግድ እየታወቀ ስለምን እንዲህ ይዳረጋል? በማለት የደረሰባቸውን እንግልት በምሬት አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የብድር ጥያቄያችን ምላሽ ማጣት የለበትም ያሉ ከሐዋሳ፣ ከመቐለ፣ ከባህር ዳርና ከአዲስ አበባ የተውጣጡ ባለሀብቶች ጉዳያቸውን ለባንኩ ኃላፊዎች በግንባር ቢያቀርቡም ለአቤቱታቸው ምንም ምላሽ እንደላገኙ ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ የባንኩ ኃላፊዎች በብሔራዊ ባንክ ውሳኔ ግር መሰኘታቸውን ቢገልጹላቸውም፣ ከተላለፈው መመሪያ ውጪ መሥራት እንደማይችሉ እንደነገሯቸው ጠቅሰዋል፡፡
እንዲተገበር የተፈለገው አሠራር በአጭሩ ሲገለጽ፣ ልማት ባንክ ለፕሮጀክት ብድር እንዲሰጥ ፕሮጀክቱ ሥራ ከጀመረ የሚያስፈልገውን ገንዘብ ደግሞ ንግድ ባንክ እንዲያበድር የሚያዝ ነው፡፡
አዲሱ የብድር አሰጣጥ ለፕሮጀክት ፋይናንስ የሚለው ገንዘብ በመካከለኛና በረዥም ጊዜ ውስጥ ተመላሽ የሚደረግ ብድር እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ የረዥም ጊዜ የሚባለው በ20 ዓመታት ውስጥ የሚከፈል ሲሆን፣ መካከለኛው ደግሞ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚጠቃለል ነው፡፡
በዚህ መሠረት የአጭር ጊዜ የሥራ ማስኬጃ ብድር የማቅረብ ሥራ የንግድ ባንክ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ብድርም ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚከፈል ይሆናል ማለት ነው፡፡
ሁለቱ የመንግሥት ባንኮች የተቋቋሙበትን ዓላማ ለማፈጸም እንዲሠሩ የሚጠይቀው ብሔራዊ ባንክ፣ ምንም እንኳ ተቋማቱ በሜዳቸው ይጫወቱ ቢልም ሳይታሰብ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የብድር አሰጣጥ ሥርዓት ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት በመገንዘብ ብሔራዊ ባንክ ጉዳዩን መልሶ እንዲያይላቸው ባለሀብቶቹ እየጠየቁ ነው፡፡
ብሔራዊ ባንክን ለማነጋገር ሞክረው እንዳልተሳካላቸው የገለጹ ባለሀብቶች፣ አሁንም ጥያቄ ማቅረባቸውን እንደሚቀጥሉበት አስታውቀዋል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ ንግድ ባንክ እንዲቋረጥ ያደረገው የብድር ጥያቄ በቢሊዮኖች የሚገመት ገንዘብ ሲሆን ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ባሻገርም የውጭ ኩባንያዎች ጥያቄም እንደሚገኝበት ታውቋል፡፡
