መንግሥት በአገሪቱ የኢኮኖሚ መቀዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ኢንዱስትሪ መር ጉዞ ጀምሬያለሁ ካለ ሰነባቷል፡፡ በመጀመርያውም ሆነ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች እየተተገበሩ ቢሆንም፣ በዘርፉ የሚፈለገው ውጤት ሊመዘገብ አልቻለም፡፡
በጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዓመታት ከማኑፋክቸሪንግ የኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ ከጠቅላላው የአገራዊ ኢኮኖሚ ድርሻው ከአምስት በመቶ በታች ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህም ቢሆን ሊመዘገብ የቻለው የግንባታ ዘርፉ በ8.5 በመቶ በማደጉ ነው፡፡ የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዓመታት የግምገማ ሪፖርት እንሚያሳየውም በኢንዱትሪ ዘርፍ ውስጥ ዋናው የዕድገት አንቀሳቃሽ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ነበር፡፡
በዚሁ ግምገማ መሠረት የአገሪቱ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ድርሻ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮችም ሳይቀር በዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ይህ ዝቅተኛ አፈጻጸም ከግብርና ዘርፍ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱትሪ ዘርፍ የሚደረገውን ኢኮኖሚያዊ ሽግግር ለማፋጠን የሚደረገው ርብርብ መስፋፋት እንዳለበት የሚጠቁም ነው፡፡ ዘርፉ ተፈላጊውን ውጤት እንዲያስመዘግብ ደግሞ የግል ባለሀብቱ ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ይሰመርበታል፡፡
የግል ባለሀብቶች ግን በሚፈለገው መጠን ወደ አምራች ዘርፉ እየመጡ አለመሆናቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ እንደ ንግድ ምክር ቤት ያሉ የግሉ ዘርፍ ወኪል ተቋማትም አባሎቻቸውም ሆኑ ሌሎች አካላት በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲሳተፉ የሚያግዙ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ እንደማይታዩ ይነገራል፡፡
በመንግሥት ውጥን በቀላል ማኑፋክቸሪንግ መስክ ኢትዮጵያን የአፍሪካ እንብርት ለማድረግ እንዲቻል የግሉ ዘርፍ አስተዋጽኦ እንደጠበቀ ሁኖ ዘርፉን ወደ ማኑፋክቸሪንግ እንዳይመጣ ያላስቻሉ ምክንያቶች እንዳሉ፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰሎሞን አፈወርቅ ይገልጻሉ፡፡ ችግር ሆነው ከሚታዩት አንዱ በቂ የግንዛቤ ሥራ አለመሠራቱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ቢዘገይም ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ዓይነተኛ ሚና የሚጫወት በመሆኑ፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ትኩረት እንዲደረግበት በማሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ማዘጋጀት ጀምሯል፡፡ በመሆኑም ‹‹ለኢንዱስትሪ ልማት እንሩጥ!›› በሚል ርዕሥ ያዘጋጀው የጎዳና ላይ ሩጫ ማሟሻ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የንግድ ትርዒትና ኩነት ዳይሬክተሮች ዳይሬክተር ወ/ሮ ባግናወርቅ ወልደ መድኅን እንደሚጠቅሱት፣ ለኢኮኖሚው ዋልታ በሆነው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ውስጥ ባለሀብቶች ገብተው እንዲሠሩ የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ ሆኖም የሚያጠግብ ለውጥ አልመጣም፡፡ ስለዚህ በተለየ ዘዴ ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ የቢዝነስ ሩጫ ለማሰናዳት ተነስተናል ይላሉ፡፡ እንደሳቸው ገለጻ፣ የግሉ ዘርፍ በሚጠበቀው መጠን ወደ ማኑፋክቸሪንግ ያልገባበት አንዱ ችግር ግንዛቤ ማስጨበጥ ስላልተቻለ ነው፡፡
ወ/ሮ ባግናወርቅ አባባላቸውን ለማጠናከር በቢዝነሱ ዓለም በተለይም በአስመጪነት ከ60 ዓመታት በላይ የቆዩ፣ የአንድ አንጋፋ ነጋዴን ተሞክሮ በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፡፡
‹‹እኝህ አዛውንት ነጋዴ ይህንን ያህል ዓመት ፍሪጅ በማስመጣት ሲሠሩ የቆዩ ናቸው፡፡ ፍሪጅ እያስመጡ ይሸጣሉ፡፡ ይህንን ሲሠሩ ነው ያረጁት፡፡ ልጆቻቸውም ይህንኑ ሥራ ቀጥለዋል፡፡ የተለወጠነ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ፍሪጁን እዚህ እንዲገጣጠም ባያደርጉ ራስዎንም አገርዎንም ይጠቅማሉ ስንላቸው፣ ‹ይህንን ማነገረኝ ታዲያ?› ነበር ያሉት››፡፡
ስለዚህ ባለሀብቱ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲገባ በቂ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ አልተሠራም የሚለው ምክንያት የሚያስኬድ በመሆኑ፣ ንግድ ምክር ቤቶችም ድርሻቸውን ለመወጣት፣ ‹‹ለኢንዱስትሪ ልማት እንሩጥ!›› በሚል ርዕሥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰናዳ የቢዝነስ ሩጫ የግንዛቤ ውድድር መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በመጪው እሑድ፣ ግንቦት 27 ቀን 2009 የሚካሄደው ይህ ሩጫ፣ በየዓመቱ በቋሚነት ለማካሄድ የታሰበ ሲሆን፣ ሩጫው 3,000 ተሳታፊዎች እንደሚታደሙበት ይጠበቃል፡፡ እስካሁንም ከ2,000 በላይ መመዝገባቸው ታውቋል፡፡
አቶ ሰለሞን ስለሩጫው እንደገለጹት፣ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ሚና የሚጫወተው የኢንዱስትሪ በተለይም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቱ ተሳታፊ እንዲሆን መንደርደሪያ ሊሆን እንደሚችል ታስቦ የተሰናዳ ነው፡፡
እስካሁን በነበረው አካሄድ በተለያዩ ስብሰባዎች የምክክር መድረኮችና በተመሳሳይ መንገዶች የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ኢንዱስትሪ በመግባት ኢንቨስት እንዲደርጉ መረጃው ቢተላለፍም፣ በታሰበው ልክ ባለሀብቱ ተሳታፊ ሊሆን አይችልም፡፡
በኢንዲስትሪው ዘርፍ የውጭ ኢንቨስተሮች አብላጨውን ድርሻ ሲይዙ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ግን ወደ ዘርፉ ለመግባት ያላቸው ተነሳሽነት ዝቅተኛ በመሆኑ ይህ እንዲለወጥ የሚረዳ ግንዛቤ ለመፍጠር የተሰናዳ የሩጫ ውድድር ነው፡፡ ዘርፉን ለማገዝ በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሳይቀር የውጭ ባለሀብቶች ብልጫውን እየወሰዱ ነው ያሉት አቶ ሰሎሞን፣ ይህ አካሄድ ሥጋት እንደሚያሳድር ይናገራሉ፡፡ አገራዊውን ባለሀብት በኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚኖረውን ተሳትፎ በማቀጨጭ አደጋ ላይ ሊጥል ስለሚችል ባለሀብቱ ዓይኑን ወደ ኢንዱስትሪው እንዲጥል የተለየ ነገር እናድርግ በሚል ለኢንዱስትሪ እንሩጥ በማለት አዘጋጅተነዋል ብለዋል፡፡
ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር እንዲረዳ የግንዛቤ ማስጨበጫው የሩጫ ፕሮግራም በቂ አይደለም ያሉት ወ/ሮ ባግናወርቅ፣ ሌሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልቶችም ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡ መጪውን የቢዝነስ እንቅስቃሴ ያገናዘበ፣ አገራዊ ጠቀሜታ ያለውን ሥራ ለመሥራት ሌሎች ዘዴዎችን መጠቀም አለብን ይላሉ፡፡
አቶ ሰለሞን እንደሚጠቅሱት ዘርፉን ለመቀላቀል ችግር የሚያጋጥማቸው ከሆነም ችግሩን ለመፍታት የንግድ ምክር ቤቱም እገዛ ያደርጋል፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በተለያዩ የምክክር መድረኮች ችግሮችን በማሳየት መፍትሔ እንዲሰጥባቸው ለማድረግ ጥረታችን ይቀጥላል ያሉት አቶ ሰለሞን፣ የንግዱ ኅብረተሰብ በኢንዱስትሪ ውስጥ በመግባት ኢንቨስትመንቱን ማስፋፋት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
የንግድ ማኅበረሰቡን ጨምሮ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ አትሌቶች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎችም አካላት ይሳተፉበታል የተባለው የቢዝነስ ሩጫ አምስት ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ ከመስቀል አደባባይ ተነስቶ በጋንዲ ሆስፒታል በኩል በሜክሲኮ አደባባይ ዞሮ ቡናና ሻይ ሕንፃ ሲደርስ ይጠናቀቃል፡፡
