በአዲስ አበባ የሜትር ታክሲዎችን ከቀረጥ ነፃ በማስገባት ለሚንቀሳቀሱ ባለንብረቶች የሽያጭ አገልግሎት የሰጠው የቻይናው ሊፋን ሞተርስ ኩባንያ፣ እስካሁን ለሸጣቸው 825 ሊፋን ሥሪት ሜትር አገልግሎት ድኅረ ሽያጭ የጥገና አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል ይፋ አድጓል፡፡
በያንግፋ ኩባንያ ሥር የሚተዳደረው ሊፋን ሞተርስ ሊፋን ሥሪት ሜትር ታክሲዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ከአንድ ዓመት በፊት ለሽያጭ ያዋለ ሲሆን፣ ለሊፋን ሜትር ታክሲዎች ብቻ አገልግሎት የሚሰጥ የጥገና ማዕከል ይፋ ያደረገው ትናንት ግንቦት 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ወቅት ነበር፡፡
በአንድ ጊዜ እስከ 50 ተሽከርካሪዎች ያስተናግዳል የተባለው አዲሱ የጥገና ማዕከል ሲመረቅ እንደተገለጸው፣ የሜትር ታክሲዎች ከዚህ ቀደም ሲያረቀቡት የነበረውን የጥገና አገልግሎት ዕጦት ቅሬታ ሊፈታላቸው እንደሚያስችል ታምኖበታል፡፡
አዲሱ የጥገና አገልግሎት መስጫ ማዕከል ለሚቀርቡለት የአገልግሎት ጥያቄዎች ተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚጠይቅም የኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች በምረቃ ፕሮግራሙ ላይ ተናግረዋል፡፡
በምረቃ ሥርዓቱ ወቅት ከ18ቱ የሜትር ታክሲ ማኅበራት የተውጣጡ ተወካዮች የተገኙ ሲሆን፣ የጥገና አገልግሎቱን በማስመልከት ከዚህ ቀደም ያጋጠማቸውን ችግር እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ከሜትር ታክሲዎች ማኅበራት ጋር በመነጋገር ሲፈጠሩ የነበሩ ክፍቶችን ለመሙላት ሲሠሩ እንደቆዩም በዕለቱ ከተደረገው ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የኩባንያው ኃላፊዎችም ከጥገና አገልግሎት ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮች እንደማይደገሙ ቃል ገብተው፣ በአዲሱ ማዕከል ስለሚሰጧቸው አገልግሎቶችም በዝርዝር አቅርበዋል፡፡
ከሜትር ታክሲዎች ባለንብረቶች በቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ ለሜትር ታክሲዎች አገልግሎት ብቻ የሚውል የጥገና ማዕከል የተከፈተው ታክሲዎቹ ለጥገና ሲመጡ መዘግየት እንዳይፈጠርና በፍጥነት ለማስተናገድና የሚፈለገውን አገልግሎት ሰጥቶ በአፈጣኝ ወደ ሥምሪት እንዲመለሱ ለማስቻል ጭምር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ይህ የጥገና ማዕከል ከ825 የሊፋን ሜትር ታክሲዎች በተጨማሪ በቅርቡ ርክክብ የሚፈጸምባቸውን 40 የሜትር ታክሲዎችም የጥገና አገልግሎት እንዲያገኙ በማሰብ የተደራጀ ነው፡፡ የሊፋን ሞተርስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ማርክ ቹ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪው ውስጥ ሊፋን የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እየጎላ መጥቷል፡፡ እስካሁን ለገበያ ሲያቀርባቸው ከቆዩ አገልግሎቶች በተጨማሪ ለሜትር ታክሲዎቹ እንዲውል ያስገነባው ማዕከልም ለሚያደርገው እንቅስቀሴ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ከመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት አኳያ ለቀረበው ጥያቄ፣ ኩባንያው በቂ መለዋወጫዎችን እንዳቀረበና የአቅርቦቱን ሥራ ሌሎች ተቋማትም እንዲሳተፉበት ጥረት እየተደረገ ነው ተብሏል፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጡ የመለዋወጫ ዕቃ አቅራቢዎች ወደ ገበያ እስኪገቡ ድረስ ግን ያንግፋ ማቅረቡ እያቀረበ ይቀጥላል፡፡
እንደ ኩባንያው የሥራ ኃላፊዎች ገለጻ ሊፋን ሞተርስ ለጥገና አገልግሎት የሚጠቀምበትን ቦታ ከግለሰቦች በመከራየት የመሠረተው ነው፡፡ ሆኖም አገልግሎቱን የበለጠ ለማድረግ ዋና መሥሪያ ቤቱን ጨምሮ የጥገና፣ የማሳያ ማዕከል እንዲሁም የሽያጭ ሥራዎችን አንድ አጠቃልሎ የሚይዝ ሕንፃ ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ ሲሆን፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዕውን እንደሚያደርግም ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት 11 የተለያዩ ሞዴል ያላቸው የሊፋን መኪኖች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ የገቡ ሲሆን፣ ኩባንያው በሺዎች የሚቆጠሩ መኪኖችን በአገር ውስጥ በመገጣጠም ላይ ይገኛል፡፡ በዱከም ከሚገኘው የኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን የመገጣጠሚያ ፋብሪካውን በመመሥረት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው ሊፋን ሞተርስ፣ ወደ ውጭ ገበያ የመግባት ፍላጎት እንዳለውና ኢትዮጵያ ውስጥ የገጣጠማቸውን መኪኖች ለጎረቤት አገሮች የማቅረብ ውጥን እንዳለው መግለጹ ይታወሳል፡፡
በአገር ውስጥ በገጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ያሰበውን ያህል መሥራት እንዳልቻለ ደጋግሞ ሲገልጽ የቆየው ኩባንያው፣ ባገለገሉ መኪኖች የተያዘው ገበያም አሳሳቢ እንደሆነበት መጥቀሱ አይዘነጋም፡፡ በኢትዮጵያም ሆነ በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በኬንያ በብዛት የሚነዱት ያገለገሉ መኪኖች መሆናቸው እንደ ሊፋን ላሉ አምራቾች የገበያ ድርሻን እየተሻሙ ማሽቸገራቸው ቅሬታ ሲቀርብበት ይደመጣል፡፡
በአንጻሩ በአገር ውስጥ የሚገጣጥሙ ኩባንያዎች ከውጭ ሙሉ በሙሉ ተገዝቶ ከሚገባው አዲስ መኪና አኳያ ብዙም የዋጋ ልዩነት አለማሳየታቸው እያስተቻቸው ይገኛል፡፡ አብዛኞቹም መጠነኛ የታክስ ማበረታቻን ጨምሮ ልዩ ልዩ ድጋፎች ቢደረጉላቸውም የሚፈለገውን ያህል የዋጋም ሆነ የገበያ ልዩነት ማሳየት አለመቻላቸው፣ ተፈላጊነታቸው ላይ ተፅዕኖ እንዳሳደረ ይታመናል፡፡
