በዓለም አቀፍ ደረጃ በመልከዓ ምድራዊ አመላካች ምድብ ውስጥ ከሚካተቱና የንግድ ምክልት ተሰጥቷቸው ባለቤት አገሮችን ተጠቃሚ ከሚያደርጉ ምርቶች አንዱ ቡና ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ በንግድ ስያሜና ምልክት ያስመዘገበቻቸውን ቡናዎች እንደሚገባት አላስተዋወቀችም ሲሉ አሜሪካዊ የሕግ ምሁር ተቹ፡፡
ፕሮፌሰር ጀስቲን ሒውጅስ በአዕምሯዊ ንብረት መብት ጥበቃ ረገድ የበርካታ ዓመታት ተሞክሯቸውን መሠረት በማድረግ እንደገለጹት፣ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በቡና ረገድ ልትጠቀምበት የምትችልበት ዕቅም አቅም ቢኖራትም ተገቢውን ኢንቨስትመንት በማድረግ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻለች ገልጸዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደረጉት ፕሮፌሰሩ፣ በብሔራዊ ቤተ መጻሕፈትና ቤተ መዛግብት ውስጥ በሚገኘው የአሜሪካ ማዕከል ገለፃ ሰጥተው ነበር፡፡ በዚሁ ገለጻቸው ወቅት ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፣ የመልከዓ ምድራዊ አመላካች መብት የሚከበርላቸው ምርቶች በዓለም ደረጃ ተቀባይነት አግኝተው ተጠቃሚ እንዲያውቃቸው ለማድረግ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ወጪ ማውጣትን ይጠይቃል፡፡
ይህ ባይቻል እንኳ አቅም ያላቸው አጋር ድርጅቶችን በማፈላለግ አብሮ መሥራት ያስፈልጋል ያሉት ፕሮፌሰር ሒውጅስ፣ ኢትዮጵያ አቅም በማጣት ወይም ደግሞ ወጭ ለማድረግ ባለመፈለግ ምክንያት ዕውቅና የተቸራቸውን የቡና ዓይነቶችን ለማስተዋወቅ ያደረገችው እንቅስቃሴ እዚህ ግባ እንደማይባል ጠቅሰዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ እንደሚጠቅሱት፣ እ.ኤ.አ. በ2005 የኢትዮጵያ መንግሥት በተከተለው ፖሊሲ አማካይነት ለኢትዮጵያ ቡናዎች አሜሪካ ዕውቅና እንድትሰጥ ግፊት የሚያደርግ ፖሊሲ ተከትሏል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያን ቡና በብዛት የሚገዛው የአሜካው ስታርባክስ ኩባንያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመጋጨቱ ምክንያት የኢትዮጵያ ንግድ ምልክት የታተመባቸውን ቡናዎችን ከመሸጥ ለመቆጠብ መገደዱን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ግን ኩባንያው ከኢትዮጵያ ቡና መግዛቱን እንዳላቋረጠ፣ የገዛውንም ቡና ከሌሎች ቡናዎች ጋር በማደባለቅ ሲሠራ እንደቆየ አስታውሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግሥትና በስታርባክስ መካከል የተነሳው ግጭት ካባራ በኋላ የይርጋጨፌ፣ የሐረርና የሲዳማ ቡናዎች በዓለም ደረጃ ዕውቅና ተሰጥቷቸው፣ የንግድ ምልክት ሆነው በመሸጥ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ይሁንና መንግሥት ለእነዚህ ቡናዎች ዕውቅና እንዲሰጥ ያደረገውን ያህል ግፊት ግን ቡናዎቹ በተጠቃሚው ዘንድ ተፈላጊነት አግኝተው እንዲሸጡና የገበያ ድርሻ እንዲኖራቸው ለማድረግ ያደረገው እንቅስቃሴም ሆነ ያፈሰሰው ኢንቨስትመንት አለ ለማለት እንደማያስደፍር ጠቅሰዋል፡፡
እንዲህ ያለው የማስተዋወቂያ ኢንቨስትመንት ተጠቃሚ ካደረጋቸው አገሮች መካከል በተለይ ኮሎምቢያን ዋቢ ያደረጉት ፕሮፌሰሩ፣ እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ አንድ አሜሪካዊ ኮሎምቢያ ቡና አምራች ስለመሆኗ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ በጥናት ተረጋግጦ እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡
ይሁንና በአሜሪካ ገበያዎች ዘንድ ለቡና ተጠቃሚዎች በተደረገ የማስተዋወቅ ቅስቀሳና ዘመቻ መሠረት በአሁኑ ወቅት ሁሉም አሜሪካ ኮሎምቢያ ቡና አምራች አገር መሆኗን እንደሚያውቅ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ አኳያ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር መሆኗን የሚጠቅሱ ስትገለጽ ብትታይም፣ የአዕምሯዊ ንብረት ባለመብት በሆነችባቸው ቡናዎች ረገድ እንዲሁም ቡናዎቹ በሚሸጡባቸው የገበያ መዳረሻ አገሮች ውስጥ ያደረገቻቸው የማስተዋወቅ ሥራ እጅግ ደካማ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ የይርጋጨፌ፣ የሲዳማም ሆነ የሐረር ቡና የሚባሉትን የንግድ ስያሜዎችና ምልክቶች አብዛኞቹ አሜሪካውያን እንደማውቋቸውም ለፕሬፌሰሩ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
መንግሥት በቁጥጥር ሥራዎች ላይ ገንዘብና ጊዜውን ከሚያጠፋ ይልቅ ገበሬው ከሚሸጠው ቡና ገንዘብ ማግኘት የሚችልበትን፣ እንደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለው ተቋም አማካይነት በማዕከላዊ ገበያ የሚደረገው ግብይት ላይ ጫና ከማሳደር ይልቅ ሻጭና ገዥ በቀላሉ መገበያየትና ተጠቃሚ መሆን የሚችሉባቸውን አሠራሮች በመከተል የቡናን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ማሳደግ ላይ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
እንዲህ ባሉት የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃዎች፣ በተለይም በንግድ ምልክት በቅጅና ተዛማጅ መብቶች፣ በፓተንትና በመሳሰሉት ዙሪያ በተለያዩ መድረኮች ተዘዋውረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ለመስጠት በአሜሪካ መንግሥት ጋባዥነት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት፣ ፕሮፌሰር ሒውጅስ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሯዊ መብት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሒደዋል፡፡ የኦሮሚያ የቡና ኅብረት ሥራ ዩኒየን አባላትን፣ ጨምሮ በአማራ ክልል የሚገኙ የጤና አገልግሎት መስጫዎችን የጎበኙት ፕሮፌሰሩ ከሳምንት ቆይታ በኋላ ወደ አሜሪካ መመለሳቸው ታውቋል፡፡
ከቡና ባሻገር በካካዎና በናይጄሪያው የኖሊውድ የፊልም ኢንዱስትሪ ላይ ሰፊ ጥናት በማድረግ የአገሮቹን የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሕጎች፣ አሠራሮችና መሰል ይዘቶችን ለዓመታት እንዳጠኑ ያስታወቁት ፕሮፌሰሩ፣ በተለይ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ የአዕምሯዊ ንብረት መብቶችን የሚመለከቱ አንቀጾች በግልጽ እንዳልሰፈሩ ጠቅሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመላው ዓለም ችግር መሆኑ የሚነገርለት የቅጅና ተዛማጅ መብቶች አለመከበር ችግር ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሆኖ ይታያል፡፡ ፕሮፌሰሩ እንደሚጠቅሱት የሕግ ማስከበር ክፍተቶች ለእንዲህ ያሉት መብቶች መጣስ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡ በአሜሪካ ባለፈው ዓመት ብቻ ከ980 ሚሊዮን ዶላር በላይ የፊልምና የቴሌቪዥን ሥርጭቶች በሕገ ወጥ መንገድ ተባዝተው እንደተሰራጩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የአሜሪካ የፊልምና የቴሌቪዥን ኢንዱስትሪ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል የፈጠረና ለዘርፉ የተለያዩ አገልግሎቶችን በመስጠት የሚንቀሳቀሱ የንግድ ተቋማት በዓመት ከ43 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚያገኙበት ቢሆንም፣ ከሕገወጥ ቅጅ ተግባራት የራቀ አልሆነም፡፡ በኢትዮጵያም በርካታ የኪነ ጥበብ ሥራዎች ከባለመብቶቹ ዕውቅናና ፈቃድ ውጭ በሕገወጥ መንገድ እየተባዙና እየተሰራጩ ለጉዳት ሲዳርጓቸው ይታያል፡፡
