- በቅርቡ በ22 የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ አገሮች የሚካሄድ የኢንቨስትመንትና የባህል ትርዒት እንደሚዘጋጅ አስታውቋል
አይጂ ኢንተርቴይንመንትና ኤቨንትስ የተባለው አገር በቀል ኩባንያ የሚያስተባብራቸውና የኢትዮጵያ ኩባንያዎች የሚሳተፉባቸው የንግድ ትርዒቶች በጀርመን ስቱትጋርት ከተማ እንዲሁም በካናዳ ሊካሄዱ መዘጋጀታቸውን አስታውቋል፡፡
የአይጂ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ይስሃቅ ጌቱ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ በጀርመን ስቱትጋርት በመጪው ግንቦት ከ20 እስከ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የኢትዮጵያ ጀርመን የኢኮኖሚ ፎረም ጎንዮች ላይ የንግድ ትርዒቱ ይካሄካዳል፡፡ በዚህ ንግድ ትርዒት ላይ የሚያመርቷቸውን ሸቀጦችና የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች የሚቀርቡ 20 ያህል ኩባንያዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ያሉት አቶ ይስሃቅ፣ በካናዳም በቡና፣ በቅመማ ቅመም፣ በጥራ ጥሬና በቅባት እህሎች ላኪነት የሚንቀሳቀሱ 40 ኩባንያዎች የሚታደሙበት ዓውደ ርዕይ እንደሚካሄድም ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር በበርካታ አፍሪካ አገሮች ተሳትፎ እንደሚደረግበት የሚታሰብ፣ በ22 የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ አገሮች የሚሰናዱ የኢንቨስትመንትና የባህል ትርዒቶችን ለማዘጋጀት ቅድመ ሁኔታዎች እየተሟሉ እንደሚገኙ ያስታወቁት አቶ ይስሃቅ፣ ይህንኑ በማስመልከት ለኤምባሲዎች፣ ለአፍሪካ ኅብረት፣ ለአውሮፓ ኅብረትና ለሌሎችም ተቋማት ዝግጅቶቹን የሚገልጹ ዕቅዶች እየቀረቡ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡
በ1970ዎቹ መጀመሪያ ከኢትዮጵያ በመሰደድ ወደ አውሮፓ እንዳቀኑ የሚገልጹት አቶ ይስሃቅ፣ ለበርካታ ዓመታት በኖሩበት ኔዘርላንድስ ውስጥ ሁለት ትልልቅ ሬስቶራንቶችን ያስተዳድሩ ነበር፡፡ ከሬስቶራንት ንግድ ሥራቸው ባሻገር ግን ‹‹የሙዚቃ ፕሮሞተር ነኝ›› የሚሉት አቶ ይስሃቅ፣ ‹‹ኒው ላይት›› እንዲሁም ‹‹ላይት ኦፍ አፍሪካ›› ይባሉ የነበሩትን ሁለቱን ሬስቶራንቶች ሸጠው 12 ሚሊዮን ብር ያህል ገንዘብ በመያዝ ወደ ኢትዮጵያ ስለመጡበት ሁኔታም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ጠቅልለው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ 14 ዓመታት ያቆጠሩት አቶ ይስሃቅ፣ ከሆላንድ ለመምጣት ምክንያት ከሆኗቸው ነገሮች መካከል ኢትዮጵያውን ሙዚቀኞችና ሙዚቃዎቻቸው በነጮቹ ዘንድ የነበራቸው ዝቅተኛ ተቀባይነት እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ሌሎቹ የአፍሪካ ሙዚቀኞች አውሮፓ በሄዱ ቁጥር በየስታዲየሙ የሚንጋጋው ሕዝብ፣ ኢትዮጵያውን ሲሄዱ ግን አይመጣም ነበር፤›› ያሉት አቶ ይስሃቅ፣ ይህ አኳኋን እንዲቀር ያስችላሉ ካሏቸው ሐሳቦች አንዱ የመድረክ ዳንስና የሙዚቃ ትዕይንቶችን ያዋሃደ የተሰጥኦ ውድድር በቋሚነት እንዲካሄድ በማድረግ መንቀሳቀስ አንዱ መፍትሔ በመሆኑ ‹‹ኢትዮጵያን አይዶል›› የተባለውን ውድድር አመጣሁ ይላሉ፡፡ አይጂ ኢንተርቴይንመንት በመባል የሚጠራ ኩባንያ በመመሥረት ወደ ሥራው እንደገቡ ይናገራሉ፡፡
አሜሪካን አይዶል ከሚለው የሙዚቃ ተሰጥኦ ውድድር የተቀዳው ኢትዮጵያን አይዶል ጥቂት ዓመታትን በስኬት ቢያሳልፍም የይገባኛል ጥያቄን ጨምሮ፣ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የወጣው ጨረታ ‹‹ባለቤትነቱ የእኔው በሆነው ፕሮግራም ላይ እንዴት ለጨረታ ታወጣላችሁ፤›› የሚል ጥያቄ በማንሳት አግባብ አይደለም ብለው እንደተከራከሩ ይጠቅሳሉ፡፡ ይኸው ጉዳይ ከአራት ዓመታት በፊት ትልቅ ጭቅጭቅ አስነስቶ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ባላገሩ አይዶል በሚል ርዕስ ጨረታውን አሸንፎ መሥራት የጀመረው አርቲስት አብርሃም ወልዴ ቀድሞውንም ሐሳቡ የእኔ ነው በማለት ሲከራከር እንደነበርም ይታወሳል፡፡ አቶ ይስሃቅ በዚህ ማዘናቸውን ተናግረው፣ በወቅቱ የኮርፖሬሽኑ ኃላፊዎች የወሰዱት ዕርምጃ ተገቢ ባይሆንም ‹‹ኮካኮላ ሱፐር ስታር›› በሚል ርዕስ ሌላ የውድድር ፕሮግራም ይዘው በመምጣት መንቀሳቀስ ችለው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
ከአንጋፋ አርቲስቶች ጋር በመላው አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ተዘዋውረው እንደሠሩ የገለጹት አቶ ይስሃቅ፣ አሁንም የተለያዩ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶችና ዝግጅቶች በሚካሄዱባቸው አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያውያን ኩባንያዎችን በማሳተፍ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ባለፈው ዓመትም ተመሳሳይ ዝግጅቶችን ውብሸት አስመጪና ላኪ ከተባለው ኩባንያ ጋር በመሆን ሀንጋሪ፣ አውስትራሊያ፣ ስዊዘርላንድ እንዲሁም ጀርመን ውስጥ በተዘጋጁ የንግድ ዓውደ ርዕዮች ላይ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ስለመሳተፋቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
