Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

መፍትሔ ያጡ በካይ ወንዞችና አትክልቶች

$
0
0

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት ትልቅ ሃይማኖታዊ መሠረት ካላቸው አንዱ የዓቢይ ፆም ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ፆመ እኩሌታው ተጋምሶ ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ በሚገኘው በዚህ የፆም ወቅት፣ ምዕመናን ነፍሳቸውንና ሥጋቸውን በመጎሰም ለንስሐና ለመልካም ዋጋ የሚተጉበት ጊዜ ነው፡፡ ስለ ፆሙ መተንተን ሳይሆን በፆሙ ወቅት ስለሚበሉ ምግቦችና በምግቦቹ ምክንያት ስለተጋረጠው የጤና አደጋ መዘገብ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነው፡፡

በሁዳዴ ፆም የጡልላት (እንደ ሥጋ፣ ወተት፣ እንቁላል ወዘተ. ያሉ) ምግቦች ከገበታ የሚርቁበት በአንፃሩ እንደ አትክልት፣ ፍራፍሬና ጥራጥሬ ያሉት ምግቦች የሚዘወተሩበት ጊዜ በዚሁ ለ55 ቀናት በሚፆመው ትልቁ ፆም ወቅት ነው፡፡

ከወዲህ ደግሞ ሌላም ክስተት እየተስፋፋ በመምጣት ላይ ይገኛል፡፡ የአትክልት ተመጋቢነት ልማድ ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ዕምነት ባሻገር ያሉትንም የሚያካትት የአመጋገብ ዘይቤ ሥርዓት እየሆነ መጥቷል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከጊዜ በኋላ ለበሽታ ጠንቅ እየሆኑ የሚገኙ ምግቦችን ከምርጫ ዝርዝራቸው ገሸሽ ለማድረግ እየሞከሩ ነው፡፡ የኮሌስትሮል፣ የደም መርጋት፣ የደም ግፊትና ሌሎችም ከአመጋገብ ሥርዓት ጋር ግንኙነት ያላቸው የበሽታ ዓይነቶች መበራከት ወደ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያዘነብሉ እያስገደዷቸው መጥተዋል፡፡ ከክብደት መጨመርና ከሌሎችም መሰል ሥጋቶች ለመራቅ ምርጫቸውን  ወደ አትክልት ተራ ያደረጉ በርካቶች ናቸው፡፡

አደገኞቹ ወንዞችና አደገኞቹ ምርቶች

ይህ እየሆነ ባለበት ወቅት በከተማው ስለ አትክልቶች የሚባለውና የሚታየው ለየቅል እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ ቀበና፣ ባንተ ይቀጡ፣ ቁርጡሜ፣ መከተያ፣ ቀጨኔ፣ ግንፍሌ፣ ቡልቡላ፣ ጆሞ፣ አቃቂ ወዘተ. የተባሉ ወንዞችን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከሚገኙ አምስት ዋና ዋና ወንዞችና እስከ 76 ከሚገመቱ ገባሮቻቸው እንዲሁም አቃቂ ትንሹና ትልቁ እየተባሉ ከሚታወቁ የመዳረሻ ወይም የመካተቻ ወንዞች ዳርቻ የተመተሙ የአትክትል ማሳያዎች ጉዳይ አሳሳቢ ከሆነ ሰነባቷል፡፡ የአዲስ አበባ ወንዞች ለምንም ዓይነት አገልግሎት እንዳይወሉ የሚከለክል ማሳሰቢያ ከወጣ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የወንዞቹን ዳርቻዎች ተከትለው አትክትልክት፣ የግቢ ማስዋቢያ ዓጸዶችንና ልዩ ልዩ ችግኞችን በማምረት የሚተዳደሩ ከአሥር ሺሕ በላይ አባወራዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በአንድ አባወራ ቤት በአማካይ ከአምስት እስከ ስድስት የቤተሰብ አባላት ይኖራሉ በሚል ስሌት ይህንን አኃዝ ብናበዛው፣ ከ50 እስከ 60 ሺሕ የሚገመቱ ሰዎች ኑሯቸው የተመሠረተው በዚሁ የጓሮ አትክልት በማልማትና በመሸጥ ሥራ ላይ ሆኖ እንናገኘዋለን ማለት ነው፡፡  

ይሁንና የወንዞቹ የብክለት ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት በመምጣቱ በወንዞቹ ውኃ አማካነት የሚመረተው አትክልትም፣ ለልዩ ልዩ ብክለት መጋለጡ እየጨመረ መምጣቱ የማይታበል ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር በመተባበር ባካሄዱት ጥናት መሠረት የአዲስ አበባ ወንዞች ከቤት ውስጥ በሚወጣ በካይ ፍሳሽ ብቻም ሳይሆን በኢንዱስትሪ ዝቃጭ መበከላቸው ታይቷል፡፡ ከኢንዱስትሪ የሚለቀቁት ዝቃጮችም ለጤና ጠንቅ የሆኑ እንደ አርሴኒክ፣ ኮባላልት፣ ካድሚየም፣ክሮሚየም፣ ኮፐር ወይም መዳብ፣ ሜርኩሪ፣ ኒኬል፣ ዚንክና የመሳሳሉት የብረት ይዘት ያላቸው ሲውል ሲያድር በጤና ላይ ከባድ ችግር የሚያስከትሉ ኬሚካሎች ወደ ወንዞች ይለቀቃሉ፡፡

እንደውም በአንድ ወቅት ፍስሐ ኢታና የተባሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባዮሎጂ ትምህርት ክፍል ባልደረባ ‹‹ሜታልስ ኢን ሊፊ ቬጂቴብልስ ግሮውን ኢን አዲስ አበባ ኤንድ ቶኢኮሎጂካል ኢምፕሊኬሽስን፤›› በሚል ርዕስ ባካሔዱት ጥናት መሠረት እነዚህ ከባድ የብረት ይዘት ያላቸው ኬሚካሎች ወደ ወንዝ እየተለቀቁ ልዩ ልዩ አትክልቶች በመመረታቸውና ለተመጋቢም በመቅረባቸው ካንሰር፣ የተዛባ አፈጣጠር እንዲከሰትና ፅንስ እስከማጨናገፍ ወይም ማስወረድ ያሉ በሽታዎች እንዲከሰቱ እንደሚያደርጉ አሳይተዋል፡፡ በተለይ በቄራና በአቃቂ ወንዞች ላይ በተደረገ ጥናት አርሴኒክ፣ ክሮሚየም፣ አይረን የተባሉ ብረት ያለባቸው ኬሚካሎች እንደሚገኙባቸው፣ በእነዚህ ወንዞች የተመረቱ አትክለቶችም አስከፊ የጤና ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ በጥናታቸው አስጠንቅቀው ነበር፡፡

የአዲስ አበባ ወንዞች የሚደፋባቸው የፋብሪካ ዝቃጭ ቆሻሻ መጠን ከ4.8 ሚሊዮን ሜትር ኩብ በላይ ብዛት ያለው መሆኑን የሚያመላክቱ ጥናታዊ መረጃዎች አሉ፡፡ በተለይ ፋብሪካዎች ለልዩ ልዩ የምርት አገልግሎት የተጠቀሙበት ውኃ ሲወጣ ከ80 በመቶ በላይ ተበክሎ እንደሚወጣ የሚገልጹት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወንዞች፣ የወንዝ ዳርቻዎች ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ ናቸው፡፡ እንደ አቶ ደሳለኝ ማብራሪያ፣ ይህን ያህል ድርሻ ያለው የፋብሪካ ቆሻሻ ወደ ወንዞች ቢለቀቅም ከሚለቀቀው በካይ ቆሻሻ ውስጥ ከየመኖሪያ ቤቱ የሚወጣው፣ ከወንዞች ጋር በቱቦና በሌሎች መስመሮች አማካይነት የሚደፋው ቆሻሻ ግን አሁንም ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይህም ቢባል ግን በአዲስ አበባ ወንዞች ውስጥ የፋብሪካ ዝቃጭ በመልቀቅ ትልቅ ድርሻ ካላቸው ውስጥ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች፣ የምግብና የመጠጥ ኢንዱስትሪዎች፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች አምራቾች በተለይ ጫማ ፋብሪካዎች፣ ቆማ ፋብሪካዎች፣ ብረታ ብረት አምራቾች በአበይትነት ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይም ጨርቃ ጨርቅ፣ ምግብና መጠጥ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ከ4.8 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ዝቃጭ ቆሻሻ ውስጥ 96 በመቶውን ያመነጫሉ፡፡ ከፋብሪካዎቹ በተጨማሪ የሆቴሎች፣ የሆስታሎች፣ የማተሚያ ቤቶችና የመሳሰሉት ሲታከልበት የበካይ ንጥረ ነገሮች ልቀት መጠን ከፍተኛ እየሆነ እንዲሄድ፣ በአደገኛነቱም ይበልጡን እየጎላ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡

ይህ በመሆኑም ሳቢያ በከተማው ተፈጥሯዊ ይዞታዎች ላይ በሰዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ አማካይነት እየደረሰ ያለው የብክለት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ተመራማሪዎች በየጊዜው የሚያስተጋቡት እውነታ ቢሆንም፣ የሚታየው ለውጥና የሚወሰደው ዕርምጃ ግን አዝጋሚ ይመስላል፡፡ በከተማው የውኃ አካላት ላይ የተደረጉት ጥናቶች የባዮሎጂካል፣ የኬሚካል እንዲሁም የአካላዊ ለውጦችን መለኪያ ዘዴዎች በመጠቀም ምርምር አድርገው ያገኟቸው ውጤቶች የሚያመላክቱት፣ በወንዝ ውኃ የሚመረቱ ልዩ ልዩ የምግብ ምንጮች ለረጅም ጊዜ በምግብነት በሚወስዱ ሰዎች ጤና ላይ የሚደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ስለመሆኑም በጥናት ሲያመላክቱ ቆይተዋል፡፡

በአንፃሩ የከተማይቱን የአካባቢ ብክለት በመከታተል በሰው ጤናና ሕይወት ላይ ጠንቅነት ያላቸውን ዝቃጮች ወደ ከባቢ አየር እንዳይለቀቁ እንዲቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው የአዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ለዓመታት ያልሠመረለትን ሙከራ ሲያከወናውን ቆይቷል፡፡ በጥቂቱ ለስምንት ዓመታት ያህል በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ እሮሮ ሲቀርብባቸው የኖሩትን በካይ ፋብሪካዎች በተለይም የቆዳ ፋብሪካዎች አደብ ለማስገዛት ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ፣ የፍሳሽ ማጣሪያ ሥርዓት እንዲዘረጉ ቀነ ገደብ ሲያስቀምጥ ሰንብቷል፡፡ ከ33 ያላነሱ የቆዳ ፋብሪካዎች ይገኛሉ፡፡

አብዛኞቹም በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የሚገኙ ናቸው፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች በጋራ የሚጠቀሙበትን የፍሳሽ ማጣሪያ እንደሚገነቡ ሲያስተጋቡ ዓመታት አልፈዋቸዋል፡፡ አንዳቸውም ተግባራዊ አላደረጉም፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ከፍተኛ ኢንቨስትመንትን የሚጠይቅ ሆኖ በመገኘቱ ነው የሚል ነው፡፡ ይህ እውን እስኪሆን ግን የየራሳቸውን የመጀመሪያ ደረጃ የፍሳሽ ማጣሪያ ገንብተው፣ ከተጠቀሙበት በኋላ በልዩ ልዩ በካይ ዝቃጮች የተሞላውን ፍሳሻቸውን አጣርተው እንዲለቁ የሚያስገድድ መመርያ ከወጣ ሰነባብቷል፡፡ በጥቂቱ ሁሉም ፋብሪካዎች የመጀመሪያ ደረጃ ማጣሪያ በግዳጅ እንዲገነቡ፣ ይህን በማደርጉት ላይ የመዝጋት ዕርምጃ ይወሰዳል የሚለው ማስጠንቀቂያና ቀነ ገደብ ካለፈ እንኳ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን ድጋፍ ከጀርባቸው ያደረጉት እነዚህ ፋብሪካዎች አብዛኞቹ ይህንን ማስጠንቀቂያ ችላ ብለውታል፡፡ በህዳር ወር ገደማ አዲስ አበባ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ይፋ ባደረገው መሠረት ደጋግሞ ማስጠንቀቂያ የሰጣቸው ፋብሪካዎች ማስጠንቀቂያውን ወደጎን ብለውት ነበር፡፡ የባለሥልጣኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ገብረማርያም ይፋ እንዳደረጉት፣ ከ20 ጊዜ በላይ የጻፏቸው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤዎች ምንም ሊፈይዱ አልቻሉም፡፡ ይህንን ዝቅተኛውን የማጣሪያ ደረጃ እንዲገነቡ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ካለፈም ወደ አራተኛ ዓመቱ እየተጠጋ ይገኛል፡፡

በአንፃሩ ከ10 ሺሕ በላይ የሚገመቱት አባወራዎች በፋብሪካዎቹም ሆኑ ከየቤቱ በሚለቀቀው በካይ ፍሳሽ በተጋለጡት ወንዞች አማካይነት የዕለት ኑሯቸውን ያሸንፋሉ፡፡ እንደ አቶ ዋለልኝ ማብራሪያ ከሆነ፣ እነዚህ አባወራዎች ከ4000 ሔክታር በላይ በወንዞች ዳርቻ የሚገኝ መሬት በአትክልት በማልማት ይተዳደራሉ፡፡ አዲስ አበባ የከተማ ግብርና የሥራ ሒደት የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ከ3,000 በላይ አልሚዎች በ340 ሔክታር መሬት ላይ ከ2,400 ቶን በላይ ልዩ ልዩ የጓሮ ለምግብነት የሚውሉ አትክልቶችን አልምተዋል፡፡

‹‹ብክለቱ መጣብን እንጂ አልመጣንበትም››

አቶ ዋለልኝም ሆኑ አምራቾቹ እንደሚገልጹት፣ በአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻዎች አትክልትና ሌሎች ችግኞችን ማልማት የተጀመረው በጣልያን የአምስቱ ዓመት ቆይታ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ ወንዞች ለብክለት ብዙም ያልተጋለጡ ከመሆናቸው ባሻገር፣ አብዛኞቹም ለመጠጥነት ይውሉ እንደነበር  ይታመናል፡፡ የጣልያኖችን መውጣት ተከትሎ አብረዋቸው ይሠሩ የነበሩ የአገር ሰዎች በእግራቸው ተተክተው በወንዝ ዳርቻ የተጀመሩትን የአትክልት ልማት ሥራዎች አስፋፍተው ቀጥለዋል፡፡ በአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻዎችን በመንተራስ ከሚያለሙ ማኅበራት መካከል ቀደምት እንደሆነ የሚነገርለት የመካኒሳ፣ የጎፋና የሳሪስ አካባቢ የአትክልት አምራቾች የገበያ አገልግሎት ኅብረት ሥራ ማኅበር ነው፡፡ የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ኃይሉ ወልደ ኢየሱስ እንደሚገልጹት፣ የማኅበሩ ይዞታ በሆኑ አካባቢዎች የአትክልት ልማት ሥራ የተጀመረው ከ90 ዓመታት ቀድሞ ነው፡፡ ከግሪኮችና ከጣልያኖች በውርስ ቅድመ አያቶቻቸው የአትክልት እርሻዎችን በማልማት ለገበያ ሲያቀርቡ ኖረዋል፡፡ ዋናው መተዳደሪያቸው በመሆን ወንዞቹ ዛሬም ድረስ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ይሁንና ሕጋዊ ዕውቅና ያለው ማኅበር በመሆን በኢትዮጵያ መንቀሳቀስ የጀመረው ከ41 ዓመታት በፊት እንደሆነ፣ ይህም መሬት በማኅበር እንጂ በግል መያዝ አይቻልም የሚል አዋጅ በመውጣቱ ማኅበራት ማደራጀት ሲጀመር በዚሁ አግባብ ተደራጅተው በአትክልት አልሚነት እንደቀጠሉ አቶ ኃይሉ ይገልጻሉ፡፡ ከዚህም በሻገር በአዲስ አበባ ከተማ፣ በቀድሞው ክልል 14 ግብርና ቢሮ በኩል በማኅበር በመደራጀት ሕጋዊ ሠርቲፊኬት የተሰጠው ቀደምት ማኅበር፣ ይኸው አቶ ኃይሉ የሚመሩት የመካኒሳ፣ ጎፋና ሳሪት አካባቢ ማኅበር እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ማኅበሩ ሲመሠረት በ210 ወንዶችና፣ በ34 ሴቶች በጠቅላላው በ244 አባላት ተመሥርቶ በአሁኑ ወቅት የመሥራቾቹ ተተኪዎች እያስተዳደሩት የሚገኘው ይህ ማኅበር፣ በነፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ፣ ወረዳ ሦስት፣ አራት፣ አምስት፣ ስድስት፣ 11 እና 12 ውስጥ በ54.3 ሔክታር መሬት ላይ አትክልቶችን በማልማት የአዲስ አበባን 75 በመቶ የአትክልት ፍላጎት በማሟላት እንደሚገኝ አቶ ኃይሉ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና የመሬት ይዞታቸው በግል ኩባንያዎች እየተቀነሰባቸው፣ በርካታ በካይ ሥራዎችን የሚሠሩና ብክለትን ወደ ወንዞች የሚለቁ ድርጅቶች እያስፋፉ መምጣታቸው ለህልውና ሥጋት እንዳስከተለባቸው አቶ ኃይሉና የማኅበሩ አመራሮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ለአትክልት ልማት የሚጠቀሙባቸው ወንዞች ንፁህ እንደነበሩ፣ አልፎ ተርፎም የአካባቢው ነዋሪዎች ለልብሳቸውና ለገላቸው መታጠቢያነት የሚገለገሉባቸው እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ ኃይሉ፣ ብክለቱ የመጣው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሆነ ይልቁንም በአካባቢው የሚገኘው ቆዳ ፋብሪካ ትልቁን ድርሻ በመያዝ ወንዞችን እየበከለ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡ ሌሎችም እንደ አረቄ ፋብሪካ፣ ጥጥ ፋብሪካ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ተደራጁ ሳሙና አምራቾች፣ ጋራዦች፣ መኪና የሚጥቡ ሰዎች፣ እንጨት መሰንጠቂያ ድርጅት ወደ ወንዝ በሚለቁት ባካይ ቆሻሻ ምክንያት ለዘመናት የሚተዳደሩት የአትክልት ምርት እየተመናመነ መምጣቱን አቶ ኃይሉ በቁጭት ይገልጹታል፡፡

‹‹የአትክልቱ ምርት በከፍተኛ መጠን ቀንሶ የህልውና ችግር ፈጥሯል፡፡ አካባቢ ጥበቃ ብዙ ጊዜ ጥያቄ ቀርቦለት አንድም መፍትሔ አላመጣም፤›› ያሉት አቶ ኃይሉ፣ የማኅበሩ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ትዕግሥቱ ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው ‹‹በልማት ሰበብ መሬት እየተወሰደብን ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹በከተማው ግብርና ቢሮ የተመዘገበ 54.3 ሔክታር ነበረን፡፡ አሁን ግን በተለያየ ምክንያት ገበሬዎች ምትክ ቦታ እንኳ ሳይሰጣቸው እየተወሰደባቸው ነው፡፡ ይህ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ለከተማ ግብርና ሥራ ምንም ዓይነት ትኩረት አይሰጡም፤›› በማለት ማኅበራቸው የሚደርሱበትን ጫናዎች አብራርተዋል፡፡

የማኅበሩ አመራሮች በአትክልት አምራችነት ወደፊት መዝለቅ ፈታኝ እየሆነ መምጣቱን አጽንዖት ሰጥተው ይገልጹታል፡፡ ‹‹ለውጥ እንፈልጋለን፡፡ በዶሮና በከብት ርቢ እንዲሁም የገበያ ማዕከል በመገንባትና ሌሎች ምርቶችን ለማምረት የሚረዱ ሼዶችን በመሥራት የገበሬውን ሕይወት መለወጥ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን ለመሥራት ስንነሳ ፈቃድ የማግኘት ችግር አጋጥሞናል፤›› በማለት ሌሎች ያገኙትን ዕድል ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡

ይልቁንም በማኅበሩ አባላት ይዞታ ሥር የሚገኝ መሬት ላይ አንድ አረቄ ፋብሪካ የገበሬውን ማሳ በመግፋት የማስፋፈፊያ ግንባታ በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ሲገልጹ፣ ዋቢ ያደረጉት ‹‹እኛን ለአረንጓዴ ቦታ ማስፋፊያነት እያሉ ይዞታችንን ሲቀንሱ በጎን በኩል ግን ፋብሪካዎች ወንዝ ላይ እንዲገነቡ ይፈቅዱላቸዋል፡፡ ጥቃቅንና አነስተኛዎችን እያደራጁና ቦታ እየሰጡ ሲያሠሩ እኛ ግን ባለን ይዞታ ላይ እንኳ መሥራት እንዳንችል ያደርጉናል፤›› በማለት የፍትሕና የርትዓዊነት ጥያቄ በመንግሥት ላይ አቅርበዋል፡፡

ይህን ቢሉም ግን በወንዞች ላይ የሚካሔደው ብክለትና አትክልቶችም መመረታቸውን ሳያቋርጡ እንደቀጠሉ ይገኛሉ፡፡ ይብሱንም ይኸው ማኅበር የሚከተለው የአመራረት ዘዴ በራሱ ለወንዞች ብክለት አስተዋጽኦ እንዳለው ለመመልከት ተችሏል፡፡ አብዛኞቹ አትክልት አምራቾች ከማኅበሩ የኬሚካል ማዳበሪያ በመውሰድ ችግኞች አፍልተው የሚያለሙ መሆናቸውን ለመታዘብ ተችሏል፡፡ ማዳበሪያው ወደ ወንዙ በቀላሉ እንደሚቀላል ለማረጋገጥም ሳይሳዊ አመክንዎ ሳይጠይቅ በጉልህ የሚታይ  ነው፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደርም ሆነ የፌደራል መንግሥት ስለ አካባቢ ክብካቤና ስለ ብክለት መጠን በሚገልጹት ልክ እንደማይሠሩ የሚያሳብቁት የአዲስ አበባ ወንዞች ናቸው፡፡ ይሁንና ባለፈው ዓመት ተቋቁሞ ወደ ሥራ የገባው የወንዞች፣ የወንዝ ዳርቻዎች ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ የተበከሉ ወንዞች እንዲያገግሙ፣ እንዲፀዱ፣ አዳዲስ ፓርኮች ተገንብተው አረንጓዴነት እንዲስፋፋ የማድረግ ሥራዎችን ማካሄድ ጀምሬያለሁ ብሏል፡፡

ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ዋለልኝ እንደገለጹትም በአሁኑ ወቅት 65 ሚሊዮን ብር ወጭ ተደርጎባቸው ግንባታቸው እየተጠናቀቀ የሚገኙ ሰባት ፓርኮችን በቀበና ወንዝ፣ በጀሞ፣ በጉለሌ ሸክላ አፈር ማውጫ አካባቢ፣ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን አካባቢ፣ እንጦጦ አካባቢ እንዲሁም ሻንቅላ ወንዝ ተብለው የሚጠሩ የውኃ አካላትን መሠረት ያደረጉት ፓርኮች ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ግንባታቸው እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ወንዞችና ዳርቻዎችን የማፅዳት ዘመቻ በወጣቶች አማካይነት እየተካሄደ እንደሚገኝ፣ ይህም 5000 ኪሎ ሜትር ርቀትን የሚያዳርስ ሥራ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ በዚህ አኳኋን የከተማውን ብክለት ለመቀነስ የሚረዱ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ፣ 54 ሔክታር መሬት በማስመለስ ከብክለት ነፃ ለማድረግ ከመንቀሳቀስ ባሻገር፣ ለጎርፍና ለናዳ የተጋለጡ፣ ለሕዝቡም ለመሠረተ ልማቶችም ሥጋት የሆኑ የወንዝ ዳርቻዎችን በመለየት የመጠበቅ ሥራ እየሠራ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡

ይህ ሥራ ግን አምራቾቹ እንደሚገልጹት፣ አቶ ዋለልኝም እንደሚናገሩት ቀላል እንደማይሆን እየታየ ነው፡፡ በተለይ ሰዎችን ከወንዞች ዳርቻዎች የማንሳት፣ የእርሻ ቦታዎችን የመለወጥ እንዲሁም ለልዩ ልዩ ምርት ሥራ የሚውሉ እንደ ሸክላ አፈር ማውጫ ያሉ አካባቢዎችን ወደ ጥብቅ ቦታነት የመቀየር ዕርምጃ ቅሬታና ተቃውሞ እያስከተለ የሚገኝ መሆኑ ከዚህ ቀደም እንደታየ አቶ ዋለልኝ ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህም ተባለ በዚያ የአዲስ አበባ ወንዞች ብክለትን የሚገታ ነገር ሊመጣ አልቻለም፡፡ አትክልቶችም መመረታቸው አልቀረም፡፡ ሕዝቡም መመገቡን አልተወም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ለዚህ ዘገባ ሶፎኒያስ ታደሰ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

 

 

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles