-የአማራ ክልል ንግድ ምክር ቤት ዕግድ ወጥቶበታል
የአገሪቱን የንግድ ማኅብረሰብ የሚወክለው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሲያወዛግብ የቆየውን ጠቅላላ ጉባዔ ለማካሄድ የንግድ ሚኒስቴርን ውሳኔ እየተጠባበቀ እንደሚገኝ ገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ሰሎሞን አፈወርቅ ለወራት እየተስተጓጎለ ለዘለቀው የንግድ ጠቅላላ ጉባዔና የአመራር አባላት ምርጫ ጋር በተያያዘ ስለተፈጠረው ችግር ለመጀመርያ ጊዜ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡
አቶ ሰሎሞን መጋቢት 14 ቀን 2009 ዓ.ም. በሒልተን ሆቴል በሰጡት መግለጫ፣ ምክር ቤቱ የገጠመውን ችግር ለመፍታት የተለያዩ አማራጮችን ሲጠቀም ቆይቷል፡፡ በመጨረሻም ንግድ ሚኒስቴር ጣልቃ ገብቶ በመፈተሹ የተፈጠሩት ችግሮች በአጭር ጊዜ ውስጥ እልባት አግኝተው ጠቅላላ ጉባዔው በቅርቡ ይጠራል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ የሚኒስቴሩ ውሳኔ ከምርጫ ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ችግር እንዳለባቸው የተገለጹ የንግድና የዘርፍ ምክር ቤቶች፣ በሕጉ መሠረት ምርጫ ካካሄዱ በኋላ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡ ይህን ለማድረግ ግን የንግድ ሚኒስቴር ውሳኔ እየተጠበቀ እንደሚገኝ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ የዘገየውን ጠቅላላ ጉባኤና አዲስ የአመራር አባላት ምርጫ ሥነ ሥርዓትም ከሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሊካሄድ እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡
አሁን ያለው የንግድ ምክር ቤቱ አመራር የሥልጣን ዘመኑ መስከረም 2009 ዓ.ም. እንዳበቃ ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ ሁለት ጊዜ ጠቅላላ ጉባኤውን ለመጥራት በማሰብ ጥቅምት 9 እና ጥር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊደረጉ የነበሩ ፕሮግራሞች ተሰርዘዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባኤና ምርጫ ያልተካሄደባቸው ምክንያቶች ናቸው ብለው ከጠቀሷቸው መካከል አንዱ የንግድ ምክር ቤቱን መተዳደሪያ ደንብ የመጣስ ድርጊት መፈጸሙ ነው፡፡
የተወሰኑ ንግድ ምክር ቤቶች በአዋጁና በሕገ ደንቡ መሠረት ምርጫ ማካሄድ ሲገባቸው ይህንን በሕጉ መሠረት ባለማድረጋቸው ምንክያት፣ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባኤውን ማካሄድ ተስኖት ቆይቷል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮች ቀድሞም ሲያጋጥሙ እንደነበሩ ያስታወሱት አቶ ሰሎሞን፣ ይህንን ለማስተካከል ዕርምጃ ወደ መውሰድ ሲገባ የተፈጠረና ሲንከባለል የመጣ ችግር ያስከተለው ውጤት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አሁን ወደ ተፈጠረው ውስብስብ ችግር ውስጥ ከመገባቱ በፊት ንግድ ምክር ቤቱ የራሱን የማተካከያ ዕርምጃዎች መውሰድ ለምን አልቻለም? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሰሎሞን፣ በሕገ ደንቡ መሠረት ዕርምጃ መውሰድ ይቻል እንደነበር ይናገራሉ፡፡ የምክር ቤቱን ሕገ ደንብ ያላሟላ አካል አይሳተፍም ማለት እንደሚቻል የጠቀሱት አቶ ሰሎሞን፣ ሆኖም ‹‹በፌዴራል አደረጃጀት ሥርዓት የምንመራ እስከሆነ ድረስ አንዳንድ ግለሰቦች በፈጠሩት ችግር ምክንያት የሚወሰደው ዕርምጃ ብዙ አባላቶች ያሏቸውን ተቋማት ማግለል እንዳይሆን በማሰብ ዕርምጃውን አዘገይቷል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ጣልቃ የገባውም የተቀመጡ ሕጎች ባለመተግበራቸው እንደሆነ የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ የተፈጠሩት ችግሮች እስኪፈቱ ድረስ መንግሥት ጠቅላላ ጉባኤው እንዳይካሄድ የሚያግድ ዕርምጃ እንዲወስድ አስገድዶታል፡፡ የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት በማስመልከት ጨምረው በሰጡት ማብራሪያ፣ መንግሥት በአዋጅ እንዲቋቋም የሚያስችል የዕውቅና ሰርተፍኬት የሚሰጥ በመሆኑ ‹‹ሕገወጥነት ሲኖር፤ ተቋሙ ለወከለው አካል አገልግሎት ከመስጠት ውጪ የውዝግብና የራስ ፍላጎት ማስፈጸሚያ ሆኖ ሲገኝ ወይም አዋጁን ሲጥስ ጣልቃ የመግባት ሥልጣን አለው፤›› በማለት የሚኒስቴሩን ጣልቃ ገብነት ተገቢነት እንዳለው አብራርተዋል፡፡
‹‹አዋጁንና መተዳደሪያ ደንባችሁን ጥሳችኋል ብሎ ካመነም ጣልቃ ይገባል ወይም ያገባኛል ማለት ይችላል፤›› ያሉት አቶ ሰሎሞን፣ ይህ ማለት ግን በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ይገባል ማለት እንዳልሆነም አጽንዖት ሰጥተውበታል፡፡ አሁንም ጣልቃ የገባው በቀጥታ እሱን የሚመለከቱ ጉዳዮች በማጋጠማቸውና የመጨረሻው መፍትሔም ከእሱ እንዲመጣ በማስገደዳቸው ምክንያት ጣልቃ እንዲገባ ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡
ንግድ ምክር ቤቱ ባጋጠሙት ችግሮች ውስጥ በአብዛኛው የግለሰቦች ተፅዕኖ ጎልቶ መታየቱም ተገልጿል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱን መጠቀሚያ የሚያደርጉ ሰዎች ለችግሩ መባባስ ምክንያት ሆነዋል ተብሎ ለቀረበው ጥያቄም፣ ‹‹በየጊዜው ከሚታየው ነገር መገመት የሚቻለው በዚህ አመራር ቦታ የሚቀመጥ አካል ራሱን እንደ ባለሥልጣን የማየት ፍላጎት መኖሩን እንዲሁም ለራስ ጥቅም እናገኛለን በማለት አንዳንድ ግለሰቦች ችግሩ እንዲባባስ አድርገዋል፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ሌላው ለችግሩ መባባስ የተጠቀሰው የላላ የቁጥር አሠራር መኖሩ ነው፡፡ እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ አሁን ለችግሩ መንስኤ ነበሩ የተባሉት በርካታ አባላት የያዙ እንደ አማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ምክር ቤቶች ከምርጫ ጋር በተያያዘ በታየባቸው ክፍተት ምክንያት ከዚህ ቀደም ያካሔዷቸው ምርጫዎች እንዲደገሙ ተወስኗል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለጠቅላላ ጉባኤው የዚህን ያህል መዘግየት ምክንያት ከነበሩና ድጋሚ ምርጫ እንዲያካሂዱ ከተወሰነባቸው መካከል አንዱ የሆነው የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲደረግ የአማራ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ያስተላለፈው ውሳኔ አልተተገበረም፡፡
ቢሮው የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ሕግን የተከተለ ምርጫ ባለማካሄዱ፣ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. የተደረገውን ምርጫ በመሻር አዲስ ምርጫ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ዳግመኛ እንዲያካሂድ በደብዳቤ ያሳወቀው የካቲት 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ቀነ ገደብ ካለፈ አንድ ወር አስቆጥሯል፡፡ በአቶ ጌታቸው አየነው የሚመራው እና የተሻረው ቦርድ አባላት የቢሮውን ውሳኔ መቃወማቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ቢሮው ግን ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራና ምርጫ እንዲደረግ ያስተላለፈው ውሳኔ በማን አስፈጻሚነት እንደሚከናወን አለመገለጹ ክፍተት እንደሆነም ሲገለጽ ነበር፡፡ ዳግመኛ ይካሄድ የተባለው ምርጫ ቀነ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት የተሻረው ቦርድ በአቶ ጌታቸው ስም ደብዳቤ በጻፈው መሠረት የክልሉ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መጋቢት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ ለአባላቱ ጥሪ አስተላልፎ ነበር፡፡
ይህ ቦርድ ጠቅላላ ጉባኤ ለመጥራት ሥልጣን የለውም እየተባለ እንዴ ሊጠራ ቻለ? የሚለው ጥያቄ አነጋገሪ ቢሆንም፣ ይህንን የስብሰባ ጥሪ ግን የክልሉ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ መጋቢት 16 ቀን 2009 ሊካሄድ ታስቦ የተላለፈውን የጉባኤ ጥሪ ያውቅ እንደነበር ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ ሆኖም ከዕውቅና ውጭ የተሰራጨ ጥሪ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች ሲወጡ ግን መጋቢት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ሊደረግ የነበረው ጉባኤ መካሄድ እንዳይችል ተደርጓል ተብሏል፡፡
ከዚህ ባሻገር የንግድ ቢሮው የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የምዝገባ ሰርተፍኬት እንዲታገድ መወሰኑም ታውቋል፡፡ የዕውቅና ሰርተፍኬቱ እንዲሰረዝ ከሚለው ውሳኔ ባሻገር፣ ጠቅላላ ጉባኤው ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙን ቢሮው ይፋ አድርጓል፡፡
በተመሳሳይም የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምርጫ እንዲደገም ንግድ ሚኒስቴር ቢወስንም፣ እስካሁን ግን ምርጫውን ለመድገም የሚያስችል ጥሪ ለአባላት አልተላለፈም፡፡
