በስዊዘርላንድ ሆቴል በማስተዳደር አገልግሎት ከሚታወቁ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ሞቨንፒክ ሆቴልና ሪዞርት በኢትዮጵያ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚፈጀውን ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ለማስተዳደር ከዮቤክ ኢንተርፕራይዝ ጋር ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎችን በማስተዳደር የሚታወቀው ሞቨንፒክ ሆቴልና ሪዞርት ኩባንያ፣ በኢትዮጵያ የሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ ተሳታፊ የሚያደርገውን ይህንን ስምምነት ከዮቤክ ኢንተርፕራይዝ ጋር ሐሙስ የካቲት 29 ቀን 2009 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ተፈራርሟል፡፡
አዲሱ ስቴዲየም እየተገነባ በሚገኝበት ገርጂ አካባቢ በዮቤክ እየተገነባ ያለውን ባለ 14 ፎቅ ሆቴል ለማስተዳደር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ስምንት ኩባንያዎች ሲያወዳደሩ ቆይተው፣ ሞቨንፒክን ሊመርጥ እንደቻለ ሁለቱን ኩባንያዎች በማደራደር ወደ ስምምነት ያመጣው የኦዚ ቢዝነስ ኤንድ ሆስፒታሊቲ ግሩፕ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል ገልጸዋል፡፡
ሞቨንፒክ ሆቴል ዋና መቀመጫውን በስዊዘርላንድ በማድረግ በተለያዩ የዓለም ከተሞች የሚገኙ ሆቴሎችን በጋራ የማስተዳደር ስምምነት መሠረት እንደሚያንቀሳቅስ የሚታወቅ በመሆኑ እንደተመረጠ ተገልጿል፡፡ ሞቨንፒክ በዓለም አቀፉ የሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ በተለይም ባለአምስት ኮከብ ደረጃ ባላቸውና ለላይኛው ወይም ውድ በሚባለው የሆቴል ደረጃ መሠረት አገልግሎቶችን በማቅረብ ትልቅ ስም ካተረፉ የሆቴል ብራንዶች መካከል አንዱ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
የዮቤክ ኢንተርፕራይዝ መሥራችና ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኔ ግደይ እንደገለጹት፣ ኩባንያቸው ሞቨንፒክን የመረጠው መልካም ስምና ዝናው ከመመልከት ባሻገር በሆቴል አስተዳደር ሥራ መስክ ያላቸውን መርኅ እንዲሁም ዝርዝር የሥራ አመራር ልምዶችን የሚገልጹ መረጃዎችን በማጥናት ነው፡፡ በተለያዩ ከተሞች የሚገኙ የሞቨንፒክ ሆቴሎችን በአካል በመጎብኘት ጭምር ምዘና ማድረጋቸውን የገለጹት አቶ ብርሃኔ፣ የሞቨንፒክ ብራንድ ለሆቴላቸው ተመራጭ ሆኖ እንዳገኙት ገልጸዋል፡፡
ሆቴሉ 252 የተለያዩ ደረጃ ያላቸው የእንግዳ ክፍሎች የሚኖሩት ሲሆን፣ ከፕሬዚደንሻል እስከ ስታንዳርድ ክፍሎችን ያካተተ ዘመናዊ ሆቴል እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ከመንታ ክፍሎች ባሻገር ሦስት የምግብ አዳራሾች፣ አንድ የሙሉ ጊዜ ምግብ ቤትንም ያካትታል፡፡ ሁለት የጣልያንና የእስያ ምግብ ቤቶች፣ ሦስት የመጠጥ አገልግሎት መስጫ ባሮች፣ 1,600 ሰው መያዝ የሚችል የስብሰባ አዳራሽና ስድስት የተለያዩ ስፋት ያላቸው የስብሰባ አዳራሾች እንደሚያካትትም ተጠቅሷል፡፡ 1,350 ካሬ ሜትር ስፋት ያለውና በወር እስከ 300 ተገልጋዮችን ማስተናገድ የሚችል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማካሄጃ ጂም በሆቴሉ ግንባታ ውስጥ ተካቷል፡፡
ከ140 በላይ መኪኖችን የሚያስተናግድ ማቆሚያ የያዘ ስለመሆኑም አቶ ብርሃኔ ተናግረዋል፡፡ የሆቴሉ ሕንፃ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 60 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ቀሪውን የፊኒሺንግና አጠቃላይ የመገልገያ መሣሪያዎች የገጠማ ሥራ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ተሟልተው ሆቴሉ በ2011 ዓ.ም. አገልግሎት እንደሚጀምር ገልጸዋል፡፡ ሆቴሉ ለ700 ቋሚና 450 ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ይጠበቃል፡፡
ዩቤክ በአዲስ አበባ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይሠራል ተብሎ ከተጠበቀው ሆቴል በተጨማሪ በመቐለ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ ባለአራት ኮከብ ሆቴል ግንባታ በማጠናቀቅ ላይ ነው፡፡ ዮቤክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለው የፒፒ ከረጢት፣ ኮንድዊት፣ ፒቪሲ ቧንቧና የኤሌክትሪክ ኬብሎች ማምረቻና ልዩ ልዩ የኤሌክትሪክ ዕቃዎች አስመጪና አከፋፋይ መሆኑን የኩባንያው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በ1999 ዓ.ም. የተመሠረተው ዮቤክ፣ በ2004 ዓ.ም. ወደ ሪል ስቴት ልማት በመግባት በአዲስ አበባ ከተማ ለተለያዩ የንግድና የቢሮ አገልግሎት የሚውሉ ባለ 14 ፎቅ መንትያ ሕንፃዎችን በሰንጋተራ አካባቢ አስገንብቶ፣ ለአገልግሎት ማብቃቱም ይታወሳል፡፡
ሞቨንፒክ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት አላን ኦዲዬ ስምምነቱን በፈረሙበት ወቅት እንደገለጹት፣ የሞቨንፒክን ብራንድ ሆቴል በኢትዮጵያ ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን ስምምነት የፈረሙት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ባሻገር በሞሮኮ፣ በቱኒዝያ፣ በኬንያ፣ በናይጄሪያ እንዲሁም በኮትዲቯር ከዚህ ቀደም የሞቨንፒክ ብራንዶች መከፈታቸውን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስታውቀዋል፡፡
በዓለም 35 አዳዲስ ሆቴሎችን በመክፈት ለማስተዳደር የሚጠባበቀው ሞቨንፒክ፣ በዓለም ላይ የሚያስተዳድራቸው ሆቴሎች ብዛት 83 እንደሆኑ ሲገልጽ፣ በመጪዎቹ ሦስት ዓመታት ውስጥም ከ100 በላይ እንደሚያደርሳቸው ይጠበቃል ተብሏል፡፡
