Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ብዙ መሻሻሎችን የጠቆመው የሶሺዮ ኢኮኖሚክ የዳሰሳ ጥናት

$
0
0

ከዓለም ባንክና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጋር በመተባበር የተሰናዳው የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤንጀሲ ሪፖርት፣ በግብርና የሚተዳደረውን ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ለመለካት ባለፈው ዓመት የተደረጉ ጥናቶችን አጠቃሎ ያቀረበ ሲሆን፣ የጥናቱ ውጤቶችም በቅርቡ ይፋ ተደርገው ነበር፡፡

በዓለም ባንክ የኑሮ ደረጃ መለኪያ ጥናት መሠረት፣ ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ የተደረገው የሶሺዮ ኢኮኖሚክ የዳሰሳ ጥናት፣ ከአምስት ሺሕ ያላነሱ ቤተሰቦችን በናሙናነት በማካተት ከቤተሰብ አባላት ብዛት እስከ ባንክ ቁጠባ፣ ብድርን አካቶ እስከ መድን ዋስትና ተጠቃሚነት ድረስ ያሉትን ልዩ ልዩ መለኪያዎች አካቷል፡፡

በዚሁ መሠረትም አማካይ የቤተሰብ አባላት ብዛት በገጠራማው የአገሪቱ ክፍሎች ከአምስት በላይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በአነስተኛ ከተሞች ከአራት በላይ ሲሆን፣ በትልልቅ ከተሞችም ከሦስት በላይ የቤሰተብ አባላት በአንድ ላይ እንደሚኖሩ ጥናቱ ይጠቁማል፡፡

በጥናቱ መሠረት የአገሪቱ የቤተሰብ ጥገኛ አባላት አማካይ ብዛት 88 በመቶ እንደሆነ ሲያመላክት፣ በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል የጥገኛ አባላቱ ብዛት መቶ በመቶ እንደሚደርስ ያሳያል፡፡ በከተሞች ከሚኖሩ ቤተሰቦች ውስጥ የጥገኛ አባላት ብዛት 48 በመቶ እንደሚገመት ታይቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር በትምህርት መስክ ጥናቱ ከአምስት ዓመታቸው ጀምሮ ያሉና ወደ ትምህርት ገበታ የተቃረቡትን ሰዎችን ያካተተ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት በየትኛውም የአገሪቱ ቋንቋ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ ወንዶች ብዛት 64 በመቶ መድረሱ ሲጠቀስ፣ የሴቶች ቁጥር ግን 48 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ያሳያል፡፡ ይህ የትምህርት ደረጃ ማንበብና መጻፍን መሠረት ያድርግ እንጂ በጥናቱ መሠረት ዕድሜያቸው ከሰባት እስከ 18 ዓመት የሆናቸው 30 በመቶ ወንዶችና ሴቶች በትምህርት ገበታ ላይ እንደሚገኙ ተመልክቷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ግን 64 በመቶው በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ከስድስት በመቶ በታች ያነሱትን ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙ መሆናቸውም ታውቋል፡፡ ጥናቱ በአገሪቱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ምን ያህል አነስተኛ ሽፋን እንዳለው አመላካች ውጤት አቅርቧል፡፡

ከጤና አኳያ አገሪቱ ሶሺዮ አኮኖሚያዊ ጥናት እንደሚያሳየው፣ በጠቅላላው የጤና አጠባበቅ ተጠቃሚነት ሽፋን፣ በተለይም ቅድመ ክትትልና ምርመራን መሠረት በማድረግ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መሠረት የወንዶች ቁጥር ስምንት በመቶ ሲሆን፣ የሴቶች 11 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡ ይህም ቅድመ ክትትልና ምርመራ የማድረግ ልማድ በአገሪቱ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስለመገኘቱ ፍንጭ የሚሰጥ ውጤት ሆኖ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል በሕፃናት ሕክምና መስክ እንደታየው ከሆነ፣ አብዛኞቹ በገጠር የሚኖሩ ሕፃናት በከተማ ከሚኖሩት ይልቅ ለተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጋለጡ ሆነው መገኘታቸው በጥናቱ ውጤቱ ከተጠቀሱት መካከል አንዱ ሲሆን፣ በተለይ በጠቅላላ በአገሪቱ የታየው የሕፃናት መቀንጨር፣ አነስተኛ ክብደት መጠንና የመሳሰሉትን መሠረት በማድረግ በተደረገው ጥናት መሠረት 42 በመቶው የአገሪቱ ሕፃናት ለመቀንጨር ችግር ተዳርገዋል፡፡ ክብደታቸው ከተገቢው በታች የሆኑ ሕፃናት ብዛትም ከጠቅላላው አገሪቱ ሕፃናት ቁጥር አኳያ 24 በመቶውን ይዘዋል፡፡

በአገሪቱ ከሚኖሩ ቤተሰቦች ውስጥ 80 በመቶው በገዛ ራሳቸው ቤቶች ውስጥ እንደሚኖሩ አመላካች ጥናቱ ሲያሳይ፣ የተቀሩት ግን በኪራይና በሌሎች አማራጮች በቀረቡላቸው ቤቶች ውስጥ እንደሚኖሩ ይጠቁማል፡፡ ይህም ሆኖ አብዛኞቹ ቤቶች ለመኖሪያነት በማይመቹ አካባቢዎች የተቸመቸሙ፣ ወለልና ክዳናቸው፣ ግድግዳና ማገራቸው ለኑሮ ተስማሚ ባልሆኑ አሠራሮች የተዋቀሩ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

በግብርና አኳያም የሶሺዮ ኢኮኖሚክ የዳሰሳ ጥናቱ እንደሚያሳየው የሰብልና የከብት እርባታ ሥራዎች በአብዛኛው በገጠሩ ክፍል የሚዘወተሩ የመተዳደሪያ ሥራዎች ናቸው፡፡ 98 በመቶው ሕዝብ በእነዚህ ሥራዎች ተሰማርቷል፡፡ በአነስተኛ ከተሞች ከሚኖረው ሕዝብ ውስጥ 64 በመቶው በሰብል ምርትና በከብት እርባታ ይተዳደራል፡፡ ይሁንና በአማካይ አንድ አባወራ የሚተዳደርበት የግብርና መሬት ከ1.4 ሔክታር ያነሰ ስፋት እንዳለውም ታውቋል፡፡

በፍጆታ፣ በልዩ ልዩ ወጪዎች፣ በምግብ ዋስትና እንዲሁም በአደጋ ክስተትና መልሶ መቋቋም በመቻል ረገድ ያሉትን ክንውኖች በተመለከተ ጥናቱ እንዳሳየው፣ በተለይ ጥራጥሬ 90 በመቶ የሚሆነውን የቤተሰብ የምግብ ፍጆታ ይሸፍናል፡፡ ለአልባሳትና ለመጫሚያ የሚወጣው ወጪም ከሌሎች ምግብ ነክ ካልሆኑ ወጪዎች ይልቅ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ በጥናቱ ተመልክቷል፡፡ በአብዛኛው የገጠሩ ክፍል ለሳሙና፣ ለላምባ፣ ለማገዶ እንጨት፣ ለከሰል፣ ለትራንስፖርት ታክስ፣ ለመሬት ግብርና ለሌሎችም የሚያወጣቸው ወጪዎች ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ ይህም ሆኖ በከተማ የሚኖረው ሕዝብ ከገጠሩ ይልቅ አብዛኞቹን ወጪዎች በማውጣት፣ ለፍጆታዎችም ትልቁን ድርሻ በመያዝ ተመድቧል፡፡

የምግብ አቅርቦት ወቅታዊነት እንደሚታይበት ያመላከተው ይህ ጥናት፣ በተለይ ከመጋቢት እስከ ጥቅምት ያለው ጊዜ የምግብ እጥረት የሚታይበት የእህል መዝሪያ ወቅት ሲሆን፣ በተለይ የገጠሩ ክፍል ለምግብ እጥረት ከሚጋለጥባቸው ወቅቶች ውስጥ እነዚህ ወራት እንደሚያመዝኑ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ ባሻገር በቤተሰብ ላይ የሚደርሰው አደጋ ወይም ጉዳት የሚባባሰው በቤተሰብ አባላት ላይ ሕመም ሲከሰት፣ ድርቅ ሲመታቸው፣ አለያም የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ሲንር እንደሆነ ጥናቱ ጠቅሶ፣ እንዲህ ያሉ ነገሮች የቤተሰብ ጥሪትን በማሟጠጥ ለችግር የሚያጋልጡ፣ ከብቶቻቸውን እንዲሸጡ የሚያስገድዱ ችግሮች ሆነዋል፡፡

በፋይናንስ ረገድ በተለይ በባንክ አገልግሎት እንዲሁም በመድን ሽፋን አኳያ በተደረገው ጥናት መሠረት በአገሪቱ መደበኛ የፋይናንስ ተቋማት ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ብዛት 22 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ የመንግሥት ባንኮችና አነስተኛ የገንዘብ አቅርቦት የሚሰጡ ድርጅቶች ከፍተኛውን የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጡ ሆነው ሲገኙ፣ ለቁጠባም ትልቁን ድርሻ የሚይዙት እነዚሁ ድርጅቶች ሆነዋል፡፡ 32 በመቶ ግለሰቦችና 48 በመቶ ቤተሰቦች እንደየአቅማቸው የቁጠባ ልማድ እንዳላቸው ተመዝግቧል፡፡ ይሁንና በአገር አቀፍ ደረጃ 600 ብር ለመቆጠብ አቅም ያላቸው ሰዎች ብዛት ከ30 በመቶ ያልበለጠ ሆኗል፡፡

በጠቅላላው በአብዛኛው የጥናቱ መለኪያዎች መሠረት አገሪቱ የምትገኝበት የሶሺዮ ኢኮኖሚክ የዳሰሳ ጥናት፣ ብዙ ክፍቶች እንደሚታዩ አመላካች ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ጥናቱ ባለፈው ዓመት ውስጥ የነበሩትን ክንውኖች ያስቃኘ ሲሆን፣ ከጥናቱ ውጤት የታየው አፈጻጸም ዝቅተኛም ቢሆን መላ አገሪቱን የሚወክል ነው ለማለት በጥናቱ ለናሙና የተጠቀሱት ሰዎች ብዛት አብዛኛውን ሥዕል ሊያሳይ እንደማይችል በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles