Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ከአዲስ አበባ ካርቱም የሚጓዙ አውቶቡሶች ሥራ ሊጀምሩ ነው

$
0
0

- ተጓዦች 60 ዶላር ይከፍላሉ 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኢትዮጵያን ክልል አልፎ፣ ድንበር ተሻግሮ የመጀመሪያዎቹን የበረራ መዳረሻዎቹ ካደረጋቸው የአፍሪካ አገሮች መካከል ግብፅ፣ ጂቡቲና ሱዳን ተጠቃሾች ናቸው፡፡

አየር መንገዱ ድንበር ተሻጋሪ አገልግሎት ለመስጠት ወደ ካርቱም ያደረገው የመጀመሪያ በረራ ከ60 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በየብስ ትራንስፖርት ዘርፍ፣ በባቡር ድንበር የተሻገረው አገልግሎት፣ በአፄ ምኒልክ ዘመን አዲስ አበባን ከጂቡቲ ለማገናኘት አስችሏል፡፡  

ከእኒህ ትራንስፖርት አገልግሎቶች ባሻገር፣ በቅርቡ በመኪና ድንበር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለስ አገልግሎትን በአዲስ አበባና በካርቱም ከተሞች መካከል ለማስጀመር የመጨረሻው ምዕራፍ ተጠናቋል፡፡ ከኢትዮጵያ ወገን የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ ኩባንያዎች ዝግጅታቸውን አጠናቀው መንገደኞችን ወደ ሁለቱ ከተሞች ማመላለስ የሚጀምሩበት ቀን ተቆርጧል፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደሚጀመርም ይጠበቃል፡፡ ከፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የመጀመርያው የአዲስ - ካርቱም የአውቶብስ ትራንስፖርት አገልግሎት መጋቢት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በይፋ ይጀመራል፡፡

በሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች የሚደረግ ድንበር ተሻጋሪ አገልግሎት የሆነው የአዲስ - ካርቱም ትራንስፖርት አሁን ለደረሰበት ደረጃ የበቃው ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ እንደሆነ የኢትዮ - ሱዳን የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ጥምር ኮሚቴ ሰብሳቢና የጎልደን ባስ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ወጋየሁ አራጋው ይገልጻሉ፡፡  

ሱዳንን ጨምሮ ሌሎች አጎራባች አገሮችን በየብስ ትራንስፖርት ለማስተሳሰር እንቅስቃሴ ከተጀመረ ከስምንት ዓመታት በላይ ተቆጥሯል፡፡ ይሁንና በተፈለገው ፍጥነት ዕቅዱን መተግበር ሳይቻል ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያ የየብስ ትራንስፖርት አቅራቢ ድርጅቶች ድንበር አቋራጭ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ሐሳቡን በማመንጨት የሚጠቀሰው ሰላም ባስ አክሲዮን ማኅበር ነው፡፡ የኩባንያው የቀድሞ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ ከበደ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ለዓመታት ቢዘገይም አገልግሎቱ ሊጀመር መቃረቡ ትልቅ ነገር ነው፡፡ አክሲዮን ማኅበሩ በአገር ውስጥ ከሚሰጠው አገልግሎት ባሻገር ድንበር ዘለል ትራንስፖርት የማቅረብ ውጥን ስለነበረው፣ ይህንኑ ዕቅዱን ለትራንስፖርት ባለሥልጣን አቅርቦ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡  

አገልግሎቱን ለመጀመር ከአጎራባች መንግሥታት ጋር ስምምነት ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ተደማምረው ስላዘገዩት እንጂ፣ አገልግሎቱ አሁን ከሚጀመርበት ጊዜ ቀድሞ ሊጀመር ይችል እንደነበር አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ሌሎች አጎራባች አገሮችንም ማካተት እንደሚቻል የሚገልጹት አቶ ብርሃኑ፣ ወደ ኬንያ፣ ሱማሌላንድና ጂቡቲ ለመጓዝ የሚያስችሉ ዕድሎች እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህ አገሮች ጋር ድርድሮች እየተካሄዱ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ድርጅቶች ወደ ሌሎች ጎረቤት አገሮች ለመጓዝ ዝግጁ መሆናቸው የሚገልጹት አቶ ወጋየሁ በበኩላቸው፣ የሚጠበቀው ከየአገሮቹ ጋር መፈረም ያለበት ስምምነት ነው ብለዋል፡፡

ለዓመታት ሲጠበቅ የነበረው ድንበር ዘለሉ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሲጀመር የመጀመሪያውን ጉዞ የሚያደርገው አገልግሎቱን እንዲያቀርቡ ፈቃድ ካገኙ አራት ልዩ የትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅቶች አንዱ በሆነው ዓባይ ባስ ነው፡፡

ከዓባይ ባስ በተጨማሪ ለድንበር አቋራጭ አገልግሎቱ ፈቃድ ያገኙት ጎልደን ባስ፣ ሰላም ባስና ኢትዮ ባስ የተባሉት ድርጅቶች መሆናቸውን የገለጹት ከጥምር ኮሚቴው የዓባይና የኢትዮ ባስ ተወካይ የሆኑት አቶ ካሳሁን አቡሐይ ናቸው፡፡

የመጀመሪያው ጉዞ በዓባይ አውቶብሶች እንዲካሄድ የተወሰነው አራቱ የትራንስፖርት ድርጅቶች ባካሔዱት የዕጣ ድልድል መሠረት እንደሆነ ታውቋል፡፡ ከዓባይ ባስ በመከተል ኢትዮ ባስ፣ ጎልደን ባስና ሰላም ባስ በየተራ እየተፈራረቁ ከአዲስ - ካርቱም የሕዝብ ማመላለስ አገልግሎቱን ለማቅረብ ተስማምተዋል፡፡ ለዚህም የጋራ ኮሚቴ አዋቅረው እየሠሩ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

1,490 ኪሎ ሜትር ርቀት ለሚሸፍነው የአዲስ - ካርቱም የጉዞ መስመር ታሪፉ ምን ያህል ይሁን? የሚለው ጥያቄ በሁለቱ አገሮች መካከል ውይይቶች ከተደረገበት በኋላ፣ ከዚህ ቀደም ለአንድ መስመር ጉዞ ብቻ 90 ዶላር እንዲከፈል ስምምነት ተደርጎ ነበር፡፡

ነገር ግን ከሁለት ሳምንት በፊት በሁለቱ አገሮች የትራንስፖርት ድርጅቶች መካከል በባህር ዳር ከተማ በተደረገ የጋራ ምክክር ቀድሞ የተተመነውንና በአንድ የሚከፈለውን የ90 ዶላር ታሪፍ ከልሰዋል፡፡ በመሆኑም ለጉዞ እንዲከፈል የተባለው 90 ዶላር ወደ 60 ዶላር ዝቅ እንዲል በመደረጉ፣ በዚህ ዋጋ መሠረት ተጓዦች ክፍያ ይፈጽማሉ ተብሏል፡፡ ክፍያው የቁርስ አገልግሎትን የሚያካትት ሲሆን፣ በተቀረው የጉዞ ወቅት የማደሪያና ሌሎች ወጨዎችን ተጓዦች በራሳቸው መሸፈን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ቀድሞ የነበረው ዋጋ ማስተካከያ የተደረገበትን ምክንያት በተመለከተ ያነጋርናቸው አቶ ወጋየሁ እንደሚገልጹት፣ ዋጋው እንዲቀነስ ማድረጉ አግባብ ነበር፡፡ ምንም እንኳ የመጀመሪያው ታሪፍ ከወጣ ረጅም ጊዜ ቢቆይም፣ አዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ ግን የወቅቱን የነዳጅ ዋጋ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ አቶ ወጋየሁ እንደሚሉት፣ የቀደመው ታሪፍ በወጣበት ወቅት ‹‹የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ስለነበር የጉዞው ዋጋ 90 ዶላር ይሁን ተብሎ እስካሁን ድረስ በዚሁ ዋጋ ቆይቷል፡፡ አሁን ደግሞ ነዳጅ በመቀነሱ እንደገና የአዋጪነት ጥናት ተሠርቶ በባህር ዳሩ ስብሰባ 60 ዶላር እንዲሆን ተወስኗል፡፡››

ድንበር አቋራጭ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቱ የሚሰጠው ቪዛ ላላቸው ተሳፋሪዎች ነው፡፡ እንደ አቶ ካሳ ገለጻ፣ ከአዲስ አበባ ካርቱም የሚደረገው ጉዞ ሁለት ቀናት ይፈጃል፡፡ በመሆኑም ከአዲስ አበባ የተነሳው አውቶቡስ ጎንደር ከተማ አድሮ በማግሥቱ ካርቱም ይገባል፡፡ የመጀመሪያው ጉዞ ግን ስለአገልግሎቱ መጀመር የሚያበስሩ ሥርዓቶች ተካተውበት ጉዞው ሦስት ቀናት ይወስዳል ተብሏል፡፡

በሁለቱ መንግሥታት ስምምነት መሠረት በሱዳን በኩል አገልግሎቱን የሚሰጡት፣ በሱዳን የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶችን በማዕከል በሚያስተባብረውና ቻምበር ትራንስፖርት በተሰኘው ተቋም አማካይት የሚሰማሩ አውቶብሶች ናቸው፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎቱ መጀመር የሁለቱን ጎረቤታም አገሮች ግንኙነት ለማጠናከር ጠቀሜታ እንዳለው የሚጠቅሱት አቶ ብርሃኑ፣ መንገደኞችም በአነስተኛ ዋጋ አገልግሎት እንዲያገኙ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

አቶ ወጋየሁ በበኩላቸው የኢትዮ - ሱዳን የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መጀመር በተለይ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ለሚመለሱ ዜጎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ መመለስ የሚፈልጉ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ይጠቀሙበት የነበረው ትራንስፖርት መደበኛ አይደለም፡፡ በአብዛኛው በጭነት ተሽከርካሪዎች የሚጓጓዙና ከፍተኛ ወጪ ከማውጣታቸው ባሻገር ለእንግልት ተዳርገው ሲጓጓዙ የነበሩትን የሚያግዝ አገልግሎት ነው፡፡ በየኬላዎቹ ተጨማሪ ክፍያ የሚጠየቁ በመሆናቸው ጭምር በርካታ መጉላላት ይገጥማቸው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ግን ኢትዮጵያውያን ሱዳን ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ተገቢውን መረጃ በመያዝ በቀላሉ ተሳፍረው መገልገል እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡ የዚህ አገልግሎት መጀመር ሌላው ጠቀሜታ ከአውሮፕላን በተጓዳኝ አመቺ የትራንስፖርት አማራጭ ማስገኘቱ ነው፡፡ ለአውሮፕላን የሚከፈለውን ወጪ የማይችሉ ተጓዦች፣ ከአውሮፕላን ዋጋ ባነሰ እንዲገለገሉ ማስቻሉ የትራንስፖርቱን አማራጭነት ጠቀሜታ እንደሚያሳይ አቶ ወጋየሁ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአውሮፕላን ካርቱም ደርሶ መልስ ለመጓዝ 13,700 ብር ይጠይቃል፡፡ ለአንድ ጉዞ ከ7,000 ብር በላይ እንደሚከፈል ያስታወሱት አቶ ወጋየሁ፣ በአውቶብስ ለመጓዝ ግን 60 ዶላር ወይም ከ1,500 ብር ያልበለጠ መሆኑ ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አቶ ካሳ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የትራንስፖርት አገልግሎት ብቃት እንዲኖረው ከማገዙም በላይ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው እንደሆም ጠቅሰዋል፡፡

ከሱዳን ባሻገር ወደ ሌሎች አጎራባች አገሮች ለሚደረገው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በአገሮቹ መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች ብቻም ሳይሆኑ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እስኪጎለብቱ መጠበቅ ግድ እየሆነ ነው፡፡  

የሪፖርተር ምንጮች እንደሚገልጹት፣ ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ ለሚዘረጋው ትራንስፖርት ሁለቱ አገሮች ከሚያደርጓቸው ስምምነቶች ባሻገር የተጀመረው የመንገድ ግንባታ መጠናቀቅ ይኖርበታል፡፡ ወደ ሱማሌላንዷ ሐርጌሳ ከተማ ለመዝቀለቅ የሚያበቃ ገበያ ቢኖርም፣ የመኪና መንገዱ ጉዳይ እልባት የሚፈልግ ነው፡፡ በአንዳንድ ወገኖች አስተያየት ወደ ሱዳን የሚረገው ጉዞ ቪዛ የሚጠይቅ መሆኑ አገልግሎቱን ለማቀላጠፍ እንቅፋት ሊሆን እንደሚችል ሥጋት ፈጥሯል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ይህንን የሚያስቀር ስምምነት ማድረግ እንደሚኖርበት ተነግሯል፡፡ ወደ ኬንያ የሚደረገው ጉዞ ቢጀመር ተጓዦች ቪዛ ስለማይጠየቁ ከቪዛ ጋር በተያያዘ ሊፈጠሩ የሚሉች መስተጓጉሎች አይኖሩም፡፡ ከሱዳንም ጋር ያለ ቪዛ ዜጎቻቸው እንዲጓጓዙ የሚያስችል ስምምነት ማድረግ እንደሚገባም እየተገለጸ ነው፡፡

አራቱ የትራንስፖርት ድርጅቶች በጠቅላላው 96 አውቶብሶች አሏቸው፡፡ ሰላም ባስ 61፣ ጎልደን ባስ 15፣ ኢትዮ ባስ 13 እንዲሁም ዓባይ ባስ ሰባት አውቶብሶችን ገዝተዋል፡፡ እያንዳንዱ አውቶብስ 51 ሰው የመጫን አቅም አለው፡፡ ከአዲስ አበባ ካርቱም በቀጥታ ከሚደረገው ጉዞ ባሻገር፣ አውቶብሶቹ ተሳፋሪዎችን ከጎንደር፣ ከባህር ዳርና ከሌሎች ከተሞችም መጫን ተፈቅዶላቸዋል፡፡ ከአቶ ወጋየሁ ገለጻ ለመረዳት እንደተቻለው፣ ከጎንደር ተነስቶ ካርቱም ለመግባት 40 ዶላር ይጠይቃል፡፡ ከባህር ዳር ካርቱም ለሚገቡም 47 ዶላር እንዲከፍሉ ታሪፍ መውጣቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡  

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles