ከ23 ዓመታት በፊት የግል ባንኮችንና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን በማደራጀት ማቋቋም እንደሚቻል ሲፈቀድ፣ በወቅቱ የፋይናንስ ኩባንያ ለማቋቋም ያስፈልጋል ተብሎ የተደነገገው ዝቅተኛው የካፒታል መጠን ከአሥር ሚሊዮን ብር ያነሰ ነበር፡፡
ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው የተከፈለ ካፒታል መጠን አሥር ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያ ለመመሥረት የሚሰባሰቡ ግለሰቦች የሚጠበቅባቸው ሦስት ሚሊዮን ብር ብቻ ማሟላት ነበር፡፡ ይህ ገንዘብ ለዛሬዎቹ የፋይናንስ ተቋማት ምንም ማለት አይደለም፡፡ ምናልባትም በአንዳንድ ባንኮች ውስጥ አንድ ግለሰብ ደንበኛ ወይም ድርጅት በግሉ ሊኖረው የሚችል የአክሲዮን ድርሻ መጠን ሊሆን ይችላል፡፡
ከ23 ዓመት በፊት ግን ባንክም ሆነ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ለማቋቋም የተነሱ ግለሰቦች፣ ሦስትም አሥርም ሚሊዮን ብር አሟልተው ወደ ሥራ ለመግባት ሲቸገሩና ሲፈተኑ እንደነበር የሚያስታውሱ አሉ፡፡ በተለያዩ አክሲዮን ኩባንያዎች ውስጥ በተለይም የሕብረት ኢንሹራንስና የሕብረት ባንክ መሥራቶች ከሆኑት አንዱ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡
በደርግ ውድቀት ማግሥት የግሉ ዘርፍ በባንክና በኢንሹራንስ ሥራ መሰማርት እንደሚችል ቢፈቀድለትም፣ ለሥራው የሚያስፈልገውን አነስተኛ የካፒታል መጠን ለመሰብሰብ ግን እንዲህ ቀላል አልነበረም፡፡ በወቅቱ የግል የፋይናንስ ተቋማትን ለማቋቋም በአገር ውስጥና በውጭ አገር የኖሩ፣ የካበተ ልምዳቸውንና ዕውቀታቸውን በመጠቀም አክሲዮን ለማሻሻጥ ወዲህ ወዲያ ሲሉ የነበሩ የፋይናንስ ሰዎች የአንድ አክሲዮን የመሸጫ ዋጋቸውም ይህንኑ ያሳይ ነበር፡፡
በወቅቱ የአንድ የአክሲዮን ዋጋ ከ25 ብር እስከ 100 ብር ባለው መጠን ውስጥ እንዲዋልል ካደረጉበት ምክንያቶች አንዱ የአገሬው ሰው የመግዛት አቅም ነበር፡፡ በወቅቱ ግፋ ቢል አንድ ሰው አሥር አክሲዮኖችን ሊገዛ ቢችልም፣ ከዚህ በላይ መሔድ ግን ለብዙዎች ከባድ ነበር፡፡ ይህም ማለት ለአሥር አክሲዮን 1,000 ብር እንደማዋጣት ማለት ነው፡፡ ይህ ለብዙዎች የሚቻል ባለመሆኑ በአንድ ጊዜ አጠቃሎ መክፈልም ግዴታ አልነበረም፡፡ ስለዚህም ቀዳሚዎቹ ባንኮች አሥር ሚሊዮን ብር ለመሙላት ፈተና ይገጥማቸው ነበር፡፡
በዚያን ወቅት ለባንክ መመሥረቻ የሚፈለገውን ካፒታል በቶሎ ለመሙላት እጅግ ከባድ እንደነበር አቶ ኢየሱስ ወርቅ ያስታውሳሉ፡፡ በተለይ የካፒታል ገበያ ያልነበረበት፣ የሰውም አመለካከትም ገና ያልነቃበት ወቅት በመሆኑ፣ ለሽያጭ የቀረበውን አክሲዮን ዋጋ ብቻ እንዲገዙ ለማግባባት ትልቅ ፈተና እንደነበርም ይገልጻሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ የመጀመርያዎቹ ባንኮችና ኢንሹራንሶች ሲቋቋሙ እንደዛሬው በእያንዳንዱ አክሲዮን ዋጋ የሚጠየቀውን ፕሪምየም ክፈሉ እንደማይባሉም አቶ ኢየሱስ ወርቅ አስታውሰዋል፡፡
ይህ ሁሉ ግን ዛሬ ተለውጧል፡፡ ባንኮች አክሲዮናቸውን ሲሸጡ ፕሪሚየም ይጠይቃሉ፡፡ ያወጡትን ካፒታል ታሳቢ በማድረግም የኢንቨስትመንቱ ዋጋ ስለጨመረ ለአክሲዮን ሽያጩ የሚከፈል ተጨማሪ ገንዘብ ወይም ፕሪሚየም ይጠይቃሉ፡፡ የሚጠየቀው ፕሪሚየም ከአንዱ አክሲዮን ዋጋ እስከ 75 በመቶ ሊደርስ እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡ የፕሪሚየሙ ዋጋ እንደ ባንኩ ይለያይ እንጂ ፕሪሚየሙ መኖሩ ኩባንያዎቹ የደረሱበትን ደረጃ እንደሚያመላክት ይታሰባል፡፡
አጋጣሚ ሆኖ ግን ከኢትዮጵያ ውጭ ለዓመታት ቆይተው የተመለሱና ዜግነታቸውን ያልቀየሩ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ከነበሩት ሰዎች የተሻለ ገንዘብ ስለነበራቸው፣ የግል የፋይናንስ ድርጅቶቹ ለመፈጠራቸው አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ የተሰባሰበው ካፒታልም በየጊዜው እያደገ መጥቷል፡፡
ባንክ ለማቋቋም የሚጠየቀው የዱሮው የካፒታል መጠን አሥር ሚሊዮን ብር መሆኑ ቀረና 75 ሚሊዮን ብር ገባ፡፡ ቆይቶም ወደ 100 ሚሊዮን ብር አደገ፡፡ አሁንም ኢንቨስትመንቱ ስላልጠቀመው ወደ ግማሽ ቢሊዮን ብር ያደገ የተከፈለ ካፒታል ማሟላት ግዴታ ተደርጎ ቆየ፡፡ በአሁኑ ወቅት 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ማሰባሰብ ካልተቻለ ባንክ ማቋቋም አይቻልም፡፡ እንደውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የባንኮች የተከፈለ ካፒታል ሁለት ቢሊዮን ብር እንዲደርስ ለማድረግ ተዘጋጁ ተብለዋል፡፡ ይህ የብሔራዊ ባንክ ማሳሰቢያ በአብዛኛዎቹ ባንኮች ላይ ሥራ ማብዛቱ ባይቀርም፣ የባንክና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አትራፊ በመሆናቸው በቀላሉ አክሲዮን በመሸጥ ከኢኮኖሚው ገንዘብ ማሰባሰብ ይችላሉ በማለት የገዥውን ባንክ አቋም የሚቀበሉ አሉ፡፡ በኢንሹራንሱም ዘርፍ ቢሆን በሦስት ሚሊዮን ብር የተጀመረው የካፒታል መጠን ዛሬ ላይ ወደ 60 እና 75 ሚሊዮን ብር አሻቅቧል፡፡ 17ቱ የግል የመድን ድርጅቶችም ይህንን የካፒታል ጣራ አልፈው ሄደዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 34 የግል ባንኮችና የመድን ድርጅቶቸ ያሰባሰቧቸው ባለአክሲዮኖች ቁጥር ከ140 ሺሕ በላይ ደርሷል፡፡ የተመዘገበና የተከፈለ ካፒታላቸውም ከ46 ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን፣ ከ100 ሺሕ በላይ ሠራተኞችንም ማስተዳደር ችለዋል፡፡
የዜግነት ገደብ
የግል ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንዲቋቋሙ ከተፈቀደበት ጊዜ ጀምሮ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከተው አዋጅ፣ አዋጁንም ተከትለው በወጡ ማስፈጸሚያ ሕጎች ውስጥ በጉልህ ከተቀመጡ አንቀጾች አንዱ በፋይናንስ ኩባንያዎች ውስጥ ባለቤት መሆን የሚችሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ መሆናቸውን የሚገልጽ ነው፡፡ የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ሌሎች የውጭ ዜጎችና የውጭ ኩባንያዎች በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ ባለድርሻ መሆን እንደማይችሉ ተቀምጧል፡፡ ይህ ድንጋጌ አግባብ አይደለም የሚሉ በርካታ ሙግቶችን ሲያስነሳና ሲያነታርክ ቆይቷል፡፡ በተለይ የዓለም ገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ መንግሥት የፋይናንስ ዘርፉን ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እንዲያደርግ ሲወተውቱ ቆይተዋል፡፡ ዘርፉ ለሁሉም ክፍት እንዲደረግና በውድድር ብሎም በነፃ ገበያ የሚመራ መሆን እንደሚገባው የሚያምኑ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችም የውጭ ኩባንያዎች ዕድሉ እንዲሰጣቸው ቢደረግ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ደጋግመው ተንትነዋል፡፡
አሁንም ድረስ ይህንኑ አቋም የሚያራምዱ ምሁራን ጥቂት አይደሉም፡፡ መንግሥት ግን በውሳኔው እንደፀና ይገኛል፡፡ የመንግሥት አቋም በዚሁ ቢቀጥልም ዘርፉ ሌላው ቢቀር ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉበት መፈቀድ አለበት የሚለው ውትወታ ቀጥሏል፡፡ ዳያስፖራው ቢያንስ በሕግ ተገድቦ በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ እንዲሳተፍ ይፈቀድለት በማለት የሚከራከሩ አሉ፡፡
ይህንንም ቢሆን መንግሥት አልተቀበለውም፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ በቅርቡ ከሪፖርተር ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ ወቅት እንዳሉት፣ ወደፊት መንግሥት ዘርፉን ለውጭ ክፍት ማድረጉ ባይቀርም አሁን ግን ባለበት እንደሚቆይ አስታውቀው ነበር፡፡ ይህ እንደማይቀር ሲያጣቅሱም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመግባትም ሆነ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ በመሆኑ ዘርፉን መዝጋት እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ዘርፉን መክፈት ጉዳቱ እንደሚያመዝን ማስረጃዎችን አጣቅሰዋል፡፡ በመሆኑም ዳያስፖራው ማኅበረሰብ በቀጥታ ከፋይናንስ ሥራ ጋር በማይገናኙ ነገር ግን እንደ ሊዝ ፋይናንሲንግ ባሉት ኢንቨስትመንቶች ውስጥ በመሳተፍ እንዲንቀሳቀስ ይፈቀድለት ነበር ብለዋል፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ግን በተነወሰ ገደብ ዳያስፖራዎች ባለአክሲዮን ቢሆኑ ችግር እንደሌለው ይሞግታሉ፡፡
ዳያስፖራውና የፋይናንስ ተቋማት
ለውጭ ዜጎች ትውልደ ኢትዮጵያውያንም ቢሆኑ ኢንቨስት ከማድረግ የተከለከሉበት የፋይናንስ ዘርፍ ይፈቀድላቸው ከሚለው ጥያቄ ጎን ለጎን በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የዳያስፖራውን ስም የሚያስነሳ ጉዳይ ተከስቷል፡፡ ይህም በተለያዩ ባንኮችና ኢንሹራንስ ተቋማት ውስጥ የውጭ ዜግነት ያላቸውን ባለአክሲዮኖች ያቀፉ ባንኮች ተገኝተዋል የሚለው ጉዳይ አጀንዳ እየሆነ መጥቷል፡፡
ብሔራዊ ባንክ በሕግ ክልከላ የተደረገባቸው የውጭ ዜጎች በተለይም የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ባለአክሲዮን ሆነው ከተገኙ ባስቸኳይ እንዲያሳውቁት ባንኮችንና መድን ድርጅቶችን አዘዘ፡፡ ባለአክሲዮን ሆነው ከተገኙ በወንጀል የሚያስጠይቅ ድርጊት ነው እስከማለት ተደረሰ፡፡ የባንክ ኃላፊዎችም የውጭ ዜጋ የሆነ ባለአክሲዮኖችን አስወጡ የሚለውን የሰርኩላር ትዕዛዝ መተግበር ሥራቸውን ሲረብሸው ቆይቷል፡፡ የውጭ ዜግነት እያላቸው አክሲዮን የገዙ ስለመኖራቸው ማስረጃ ባይቀርብም፣ አክሲዮን ከገዙ በኋላ ዜግነታቸውን የቀየሩ ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ግን ግልጽ ነበርና እነዚህን ለይቶ ሪፖርት ለማድረግ እንዴት እንደሚቻል የብዙዎች ጥያቄ ነበር፡፡
ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሌላቸው ባለአክሲዮኖች ድርሻቸው እንዳይጠቀስ ይደረጋል የሚለው ጉዳይም ብዙዎች መንግሥት ገንዘባቸውን ሊወርሱ አስቦ ነው ወደሚለው አመለካከት እንዲያዘነብሉ አስገድዷቸዋል፡፡ ቆይቶ በተደረገ ድርድር የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለአክሲዮኖች ጥሪ እንዲደረግላቸው፣ ባንኮችም ይህንኑ አጣርተው እንዲያቀርቡ፣ ለዚህም 60 ቀናት እንዲሰጥ ጊዜ ገደብ እንዲሰጥ ተደረገ፡፡ በጥሪው መሠረት የቀረቡትም ያላቸው አክሲዮን ብዛትና ዋጋ ተሰልቶ የትርፍ ድርሻቸውን ይዘው እንዲወጡ ተደረገ፡፡ ይህ መደረጉም ጊዜያዊ ዕፎይታን ፈጠረ፡፡
ሰሞኑን እንደተገለጸው ግን በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ግን ደግሞ ባለአክሲዮን የሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስለመኖራቸው የሚያረጋግጡ መረጃዎች ቀረቡ፡፡ ከ700 በላይ የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በባንክና በኢንሹራንስ ውስጥ እስከ 400 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድርሻ ይዘው መገኘታቸው ይፋ ተደረገ፡፡ እነዚህ ባለአክሲዮኖች እንደ ሕጉ ቅጣት ቢጠብቃቸውም አክሲዮኖቻቸውንና የትርፍ ድርሻቸውን ይዘው እንዲወጡ ተደርጓል፡፡ ኩባንያዎቹም የእነዚህን አክሲዮኖች ድርሻ በጨረታ መሸጥ ጀምረዋል፡፡
ከተለያዩ ባንኮች የተገኘው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ የውጭ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኩባንያዎቹ ውስጥ ባለድርሻ ሆነው የተገኙባቸው የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ነው፡፡
አንዱና ዋናው ምክንያት በኩባንያዎቹ ውስጥ ባለድርሻ የሚያደርጋቸውን አክሲዮኖች በገዙበት ወቅት ኢትዮጵያዊ መሆናቸው ሲሆን፣ ቆይተው ግን ዜግነታቸውን መለወጣቸው ነው፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ ውርስ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ብዙ አከራክሮ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደ ብሔራዊ ባንኩ ገዥ ገለጻ፣ ለኢትዮጵያውያን ብቻ የተሰጠን መብት ኢትዮጵያዊነቱን ሲቀይር ያገኘው መብት መመለስ አለበት የሚል አቋም መንግሥት እያራመደ ይገኛል፡፡ ትልቁ ችግርም ይህ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ግን ይህም ከተባለ የባለአክሲዮኖች ድርሻ በባንኮች በጨረታ ከሚሸጥ ይልቅ ግለሰቦቹ በራሳቸው መንገድ ለባለአክሲዮኖች ቢሸጡ ይመረጥ ነበር ብለዋል፡፡ ‹‹በእርግጥ ያላቸውን አክሲዮን ይዘው መውጣታቸው መልካም ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ የተሻለ ቢደረግ ጥሩ ነበር፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡ ከአንዳንድ የባንክ ኃላፊዎች ያገኘነው መረጃ ደግሞ ይህ ጉዳይ አክሲዮኖችን በመሸጥ መቋጨቱ መልካም እንደሆነ የሚጠቁም ነው፡፡ ይህ ባይሆንና ጉዳዩ ወደ ሕግ ቢሔድ ኑሮ ገንዘባቸው መወረሱ አይቀሬ ነበር ይላሉ፡፡
የዳያስፖራ አክሲዮን ዋጋ
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት በውጭ ዜጎች ተይዘው የነበሩ አክሲዮኖችና የባለቤትነት ማረጋገጫቸውም እንዲመልሱ ተደርጓል፡፡
ባንኮች የውጭ ዜጋ መሆናቸው ተረጋግጦ በግንባር አለያም በወኪል ለቀረቡ ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ዋጋቸውንና ትርፋቸውን በመስጠት በምትኩ ሰርተፍኬታቸውን እንዲያስረክቡ አድርግዋል፡፡ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ያልቀረቡትም ድርሻቸው ተቀምጦ በቀሪው ጊዜ እንዲሰጣቸው ተወስኗል፡፡ ነገር ግን ይዘውት የነበረው አክሲዮን ኢትዮጵያዊ ለሆነ ሰው መተላለፍ ስላለበት አክሲዮኑን ለማስተላለፍ የተመረጠው ሒደት ጨረታ ሆኗል፡፡ ሁሉም ኩባንያዎች በውጭ ዜጎች የተያዙትን የአክሲዮን ድርሻዎች ለመሸጥ ጨረታዎችን ሲያወጡና ሲያስተዋውቁ ከርመዋል፡፡
በመመርያው መሠረት በውጭ ዜጎች ነበር የተባሉት አክሲዮኖች ለሁሉም ባለድርሻ ክፍት ይደረጋሉ፡፡ ዘወትር እንደሚደረገውም ቅድሚያ ተቋማቱ ባለአክሲዮኖች ይሰጥ የሚለውን አሠራርም ያስቀረ ሒደት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከሽያጩም የሚገኘው ትርፍ ለመንግሥት፣ ዋናው ገንዘብ ለባንክና ኢንሹራንሶች ገቢ ይደረጋል፡፡ እስካሁን በተከታታይ የአክሲዮን ሽያጭ ለማከናወን ይፋ ማስታወቂያ ካወጡት ውስጥ አዋሽ ባንክ ሰሞኑን ባደረገው ጨረታ የ1,000 ብር መነሻ ዋጋ ያለውን የአንድ አክሲዮን በ14 ሺሕ ብር እስከመሸጥ ደርሷል፡፡
ከምሥረታ ጀምሮ የነበሩ ባለአክሲዮኖች በተለይ በባንክ ውስጥ ያወጡትን ኢንቨስትመንት በስድስት ዓመት መመለስ እንደሚቻል ይጠቁማሉ፡፡ ኢንቨስትመንቱም አዋጭ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ቀዳሚ በሆኑ ባንኮች ውስጥ የነበሩ ባለአክሲዮኖች አብዛኛዎቹ በመጀመርያ የነበራቸውን አክሲዮን ከእጥፍ በላይ ማሳደጋቸውን የተናገሩም አሉ፡፡
በሁለት ባንኮች ውስጥ ባለአክሲዮን የሆኑት አንድ ባለአክሲዮን እንደገለጹት፣ ከ14 ዓመት በፊት በአንደኛው ባንክ በአሥር ሺሕ ብር የገዙት አሥር አክሲዮን በየዓመቱ እያደላቸው መጥቶ የገዙት አሁን 110 ሺሕ ብር ደርሶላቸዋል፡፡
ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሁን ከታወቁት ባለአክሲዮኖች ሌላ እስካሁን ያልታወቁ ባለአክሲዮኖች ሊኖሩ የሚችሉ መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አንዳንድ ባለአክሲዮኖች ኢትዮጵያዊ መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥት ግን በዚህ ጥሪ ያልቀረቡት እያወቁ ያላመለከቱ ካሉ ቀጣዩ ዕርምጃው ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው በእንጥልጥል ላይ ይገኛል፡፡
