ከ14 አገሮች የተውጣጡ ባለሀብቶች የተሳተፉበትና ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው ‹‹አግሮ ፉድ ፕላስትፓክ›› የተሰኘው ዓለም አቀፍ የንግድ ዓውደ ርዕይ፣ ዓርብ ጥር 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ለጎብኚዎች ክፍት ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከጀርመን፣ ከፈርንሳይ፣ ከእንግሊዝ፣ ከኔዘርላንድስ፣ ከኦስትሪያ፣ ከአሜሪካ፣ ከህንድ፣ ከኬንያ፣ ከታይዋን፣ ከዩክሬን፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች፣ ከቶጎ የተውጣጡ የንግድ ዓውደ ርዕይ ተሳታፊዎች የታደሙበት ይህ ዝግጅት፣ በአገር በቀሉ ፕራና ፕሮሞሽንና በጀርመኑ ፌርትሬድ ኩባንያ አማካይነት በሚሊኒየም አዳራሽ ሲካሄድ ቆይቶ እሑድ፣ ጥር 28 ቀን ይጠናቀቃል፡፡ በየዓመቱ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው ይህ ዓውደ ርዕይ በአብዛኛው በግብርና ምርቶች፣ በግብርና ግብዓቶችና በግብርና ማቀነባበሪያ መስኮች ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡ ከየአገሮቹ የተውጣጡ ልዩ ልዩ የማምረቻ፣ የምርት መጠቅለያና ማሸጊያ ማሽነሪዎችና መሣሪያዎችን ለዕይታ ያቀረቡ ሲሆን፣ በመክፈቻው ዕለትም በኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር መብራህቱ መለስና በዲፕሎማቶች ተከፍቶ ለሕዝብ ዕይታ ይፋ ሆኖ ቆይቷል፡፡
Standard (Image)
