Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

የቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ ወደ ግል ከተዛወረ በኋላ

$
0
0

ወደ ግል ከተዛወሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነውና ፀሐይ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር የገዛው ቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ ቀድሞም በመንግሥት ሲተዳደር በነበረ ጊዜ በአትራፊነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ የፋብሪካው ባለንብረትነት መብት ወደ ግል ከተዛወረ በኋላም ይበልጥ አትራፊ ሆኖ መዝለቁን የፀሐይ ኢንዱስትሪ ኃላፊዎች ይገልጻሉ፡፡

ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በጨረታዎችና በድርድር ሒደት ወደ ግል ይዞታ ከተላለፉ በመቶዎች ከሚቆጠሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል ፀሐይ ኢንዱዲስትሪ፣ ቃሊቲ ብረታ ብረትን ሲገዛው የራሱን አሻራ ያሳረፈበት ክስተት የፈጸመበት መሆኑም የሚጠቀስ ነው፡፡

ፋብሪካው ከ550 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ዋጋ ወደ ግል ይዞታነት ሲተላለፍ፣ የአክሲዮን ማኅበሩ ባለቤቶች ለቃሊቲ ብረታ ብረት ፋብሪካ ሠራተኞች የሰጡት ዕድል በሌሎች ያልተሞከረ ተግባር እንደሆነም ይነገራል፡፡ ይኸውም የፋብሪካው ሠራተኞች እንደአቅማቸው በድርጅቱ የአክሲዮን ባለድርሻ እንዲሆኑ የተመቻቸው ዕድል ሲሆን፣ ይህ ክስተት በፕራይቬታይዜሽን ሒደት ያልተለመደ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ለሠራተኞች ክፍት የተደረገውን የአክሲዮን ድርሻ በግል መግዛት የቻሉ እንዳቅማቸው መጠን እንዲገዙና ባለድርሻ እንዲሆኑ ከመደረጉ ባሻገር ይህንን ማድረግ ላልቻሉትም ሁሉንም የፋብሪካውን ሠራተኞች አባል በሚያደርገው በብድርና ቁጠባ ማኅበር በኩል አክሲዮን በመግዛት ሠራተኞቹ ባለድርሻ የሆኑበትን ዕድል ፈጥሯል፡፡ የአክሲዮን ኩባንያው የቦርድ ኃላፊዎች እንደሚገልጹት፣ በወቅቱ ይህንን ያደረጉበት ዋነኛ ምክንያት ሠራተኛው የእኔነት ስሜት ተሰምቶት በባለቤትነት ተግቶ እንዲሠራ፣ ከሥራውም ተጠቃሚ እንዲሆን በማሰብ ነው፡፡

ይህ ከተደረገ ሦስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ድርጅቱ ወደ ግል ከተዛወረ በኋላም በአትራፊነት መቀጠል መቻሉ ብቻም ሳይሆን አወቃቀሩን ለውጧል፡፡ የፋብሪካው የሥራ አድማስ እየሰፋ በመምጣቱ፣ ከአራት ዓመታት በፊት ሲያስመዘግብ የነበረው ዓመታዊ ሽያጭም በአሁኑ ወቅት ከእጥፍ በላይ ለማድረስ አስችሎታል፡፡

የፋብሪካው ዓመታዊ የሽያጭና የትርፍ መጠን ይበልጥ እያደገ ስለመምጣቱ የተገለጸው፣ ቅዳሜ ጥር 20 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው የድርጅቱ ዓመታዊ የሠራተኞች በዓል ወቅት ነበር፡፡ የፀሐይ ኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ማቴዎስ አሰሌ እንደገለጹት፣ በ2008 በጀት ዓመት 31,399 ቶን ልዩ ልዩ የብረታ ብረት ውጤቶችን ለማምረት አቅዶ 23,799 ቶን ማምረት ችሏል፡፡ ይህም የዕቅዱን 77 በመቶ ማከናወን እንደቻለ የሚያሳይ ነው፡፡ ዓምና የተመረተው ምርት በ2007 ዓ.ም. ከተመረተው ጋር በንፅፅር ሲታይ፣ የ24 በመቶ ወይም ከ4,611 ቶን በላይ ብልጫ እንዳሳየ ተመልክቷል፡፡ በዚሁ ጊዜ ውስጥ 573 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ያከናወነ ሲሆን፣ ከ2007 ዓ.ም. ከነበረው የሽያጭ መጠን ጋር ሲነጻጸርም የ18 በመቶ ብልጫ እንዳለው አቶ ማቴዎስ ጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ አፈጻጸም በበጀት ዓመቱ ሊመረት ከታቀደውና ከሽያጭ ይገኛል ተብሎ ካቀደው ገቢ ያነሰ ነው፡፡ እንደ ፋብሪካው ውጥን ቢሆን ኑሮ በበጀት ዓመቱ ለማምረት ካቀደው 31,399 ቶን ውስጥ የሽያጭ ገቢው 850 ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ ይጠበቅ ነበር፡፡

የዕቅዱን ያህል ባሆንም እንኳ በአሁን ወቅት የሚታየው የፋብሪካው አፈጻጸም በፋብሪካው ታሪክ ከፍተኛውና ከምንጊዜውም ይልቅ ብልጫ እንደያዘ አቶ ማቴዎስ ገልጸዋል፡፡ በዕቅዱና በክንውኑ መካከል የተፈጠረው ክፍተት የተከሰተው ወሳኝ በሆኑ ምክንያቶች እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ክንውኑ የዕቅዱን ያህል ላለመሆኑ አሳማኝ ምክንያቶች ናቸው ብለው አቶ ማቴዎስ ከጠቀሷቸው ውስጥ ቀዳሚው የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ነው፡፡ ፋብሪካው በውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ሳቢያ ለአሥር ወራት መደበኛ የቤት ቆርቆሮ ማምረት አለመቻሉን በአስረጅነት አቅርበዋል፡፡

በዓመታዊው የሠራተኞች በዓል ላይ የተገኙት የአክሲዮን ማኅበሩ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ተስፋዬ ፈንቴ ባለፉት ዓመታት ፋብሪካው ዕድገት እያሳየ ቢመጣም፣ ዕድገቱ በቂ የሚባል አይደለም ብለዋል፡፡ የፋብሪካውን ማኅበረሰብ የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሁኔታዎች መበራከትና መመቻቸት አለባቸው በማለት አክለዋል፡፡ በዚህ ረገድ የፋብሪካውን አቅም ለማሻሻል ይቻል ዘንድ የተሻለ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እንዲኖር ጥረት የተደረገ ቢሆንም፣ ከውጭ የሚገቡት ጥሬ ዕቃዎችን በውጭ ምንዛሪ ዕጥረት የተፈለገውን ያህል ማግኘት አለመቻል ለፋብሪካው እንቅስቃሴ ፈታኝ ችግር ሆኖ እንደቆየም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ሆኖም የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር ቀስ በቀስ እየተቀረፈ እንደሚመጣና መንግሥትም ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ቅድሚያ እንደሚሰጥ በማስታወቁ፣ የጥሬ ዕቃ አቅርቦቱ ይሻሻል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ ማቴዎስ ገልጸዋል፡፡

ፋብሪካው ከሚታወቅባቸው ምርቶች አንዱ የሆነው የቤት ክዳን ቆርቆሮ ለማምረት የሚያስችለውን ጥሬ ዕቃ በውጭ ምንዛሪ ዕጥረት ምክንያት እንደልብ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ያለመቻሉ ከፈጠረበት ችግር ባሻገር፣ ዕቅዱን ሙሉ ለሙሉ እንዳያሳካ ያደረገው ሌላው ምክንያት በበጀት ዓመቱ ይጀመራሉ የተባሉ አዳዲስ ምርቶችን ለማምረት የሚያስችሉ መሣሪያዎችን ለማስገባትና ለማምረት አለመቻሉ ነው፡፡

ምርት ይጀምራሉ ተብለው ይጠበቁ የነበሩት ባለቀለምና ባለጌጥ የጣሪያ ልባስ እንዲሁም የፈርኒቸር ቱቦ ማምረቻ መሣሪያዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህን ምርቶች ለማምረት የሚያስችሉትን መሣሪያዎች የሚያቀርብ ባለመገኘቱ መሣሪያዎቹ ሊገዙ አልቻሉም፡፡ በዚህ ምክንያትም ፋብሪካው ዓምና በያዘው ዕቅድ መሠረት ምርቶቹን በፈለገው መጠን ማምረት ሳይችል ቀርቷል፡፡ ይህም በዓመታዊ የምርትና የሽያጭ ዕቅዱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮበታል ተብሏል፡፡ በገበያው ውስጥ ተፈላጊነት ያላቸው ምርቶች በጥሬ ዕቃ ዕጥረትና በማምረቻ መሣሪያዎች ጉድለት ምክንያት ፋብሪካው የበለጠ ዕድገት ለማስመዝገብ የተነሳበት ዕቅድ ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠርበት ማድረጋቸው ተብራርቷል፡፡

አቶ ማቴዎስ እንደገለጹት፣ እንዲህ ያሉ ችግሮች ባያጋጥሙ ኑሮ የፋብሪካውን አፈጻጸም በከፍተኛ ደረጃ ማሻሻል ይቻል ነበር፡፡ በ2009 በጀት ዓመት ግን የተለያዩ ዕርምጃዎችን በመውሰድ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ መቻሉን ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡ በተለይ ከሥራ ውጭ የነበሩ መሣሪያዎች በፈጠራ  ተሻሽለው እንዲሠሩ በማድረግና በማንቀሳቀስ አዳዲስ ምርቶችን ለማምረት አስችለውታል፡፡ እንዲህ ያሉት ተግባራት ተደማምረው በ2009 የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ወቅት፣ የምርት አፈጻጸሙ ወደ 86 በመቶ እንዲደርስ አስችለውታል፡፡ በግማሽ ዓመቱ አክሲን ማኅበሩ አገኘዋለሁ ብሎ ካቀደው የሽያጭ ገቢ 76 በመቶ ማከናወን መቻሉን አቶ ማቴዎስ ጠቅሰዋል፡፡ ለሠራተኞችም የሁለት ወራት የደመወዝ ቦነስና የአንድ ዕርከን ዕድገት እንዳደረገ አስታውቀዋል፡፡ ፋብሪካው ወደ ፀሐይ ኢንዱስትሪ ከተሸጋገረ በኋላ የተለያዩ አዳዲስ ምርቶችን ያካተተ ሲሆን፣ በተለይ የከባድ ተሽከርካሪ አካላትና ተሳቢዎችን ማምረት መጀመሩ አንዱ ነው፡፡

በ2009 በጀት ዓመት ባለቀለም የጣሪያ ልባሶችን ማምረት እንደሚጀምርና ለዚህ የሚሆነውን የማሽነሪ ግዥ ፈጽሞ መሣሪያው ወደብ መድረሱ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የብረት መዋቅር ማምረቻ ፋብሪካ ግንባታ ለማካሄድ የሚያስችለውን ጥናት እንዳጠናቀቀም ተገልጿል፡፡

የብረት መዋቅር ማምረቻ ፋብሪካው የሚያመርታቸው ምርቶች በብረት መዋቅር አማካይነት የሚሠሩ ትላልቅ ግንባታዎች የሚከናወኑባቸው ሲሆን፣ ይህንን ማምረቻ በደብረ ብርሃን ከተማ ለመትከል የቦታ ጥያቄ መቅረቡም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፋብሪካው በመደበኛነት ከሚያመርታቸው ምርቶች በተጨማሪ የጭነት ተሳቢ ተሽከርካሪ አካላትን የማምረት ሒደቱን የሚያሳድጉ ተጨማሪ ሦስት የማምረቻ ሕንፃዎች ግንባታን እያካሄደ ሲሆን፣ የፈሳሽ ጭነት ተሳቢ አካላትን ማምረትም በበጀት ዓመቱ ለመጀመር እንዳቀደ ከኩባንያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles