- ከውጭ የሚገባውን 90 ሺሕ ቶን የገበታ ጨው ያስቀራል ተብሏል
በአፋር ክልል አፍዴራ ወረዳ በ500 ሚሊዮን ብር ወጪ የጨው ፋብሪካ ሊቋቋም ነው፡፡ ለፋብሪካው ግንባታ ሐሙስ ታኅሳስ 21ቀን 2009ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ተጥሏል፡፡
የአፋር ጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ የሚባል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ ፋብሪካ፣ በካዳባ ጨው አቅራቢዎች አክሲዮን ማኅበርና በሰኢድ ያሲን ቢዝነስ ግሩፕ ባለቤትነት የተቋቋመ ነው፡፡ 49 በመቶ የፋብሪካው የባለቤትነት ድርሻ በካዳባ የተያዘ ሲሆን፣ 51 በመቶው ደግሞ የሰኢድ ያሲን ኩባንያ ድርሻ መሆኑ ታውቋል፡፡
በአካባቢው የሚመረተውን ጨው የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከኢዮዲን ንጥረ ነገር ጋር የመቀላቀል ሥራ ቀደም ብሎም ሊሠራበት እንደነበር፣ አሠራሩ ግን አጥጋቢ ስላልነበር አዮዲን የመቀቀላቀሉን ሥራ በፋብሪካ ደረጃ የማሳደግ ሐሳብ የተጠነሰሰው ከሁለት ዓመታት በፊት መሆኑን የሚናገሩት፣ የካዳባ ጨው አቅራቢዎች አክሲዮን ማኅበር የሥራ አመራር ቦርድ አባልና የቢዝነስ አማካሪ አቶ ሰይፉ ኪዳኔ ናቸው፡፡ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ በንግድ ሚኒስቴር፣ በምግብ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ ቁጥጥርና አስተዳደር ባለሥልጣን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በሌሎችም ባለድርሻ አካላት የበላይ ጠባቂነት የአዋጭነት ጥናት ተደርጎበት ፋብሪካውን የማቋቋም እንቅስቃሴ እንደተጀመረ አቶ ሰይፉ ተናግረዋል፡፡
በ200,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚገነባው ፋብሪካ፣ በወር አንድ ሚሊዮን ኩንታል ጨው የማምረት አቅም እንዳለው ታውቋል፡፡ እንደ አቶ ሰይፉ ገለጻ፣ የአፍዴራ ጨው ያልተበከለ የባህር ጨው በመሆኑ ተፈላጊነቱ ከፍተኛ ነው፡፡ በተጨማሪም የጨው ይዘቱ ከፍተኛ ነው፡፡ ከቀይ ባህር የሚመረተው ጨው የሶዲየም ክሎራይድ ይዘቱ 66 በመቶ ሲሆን፣ የአፍዴራ ግን 97.99 በመቶ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የጨው ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ ቢቻል ለአገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት ይቻላል ብለዋል፡፡
አዲስ የሚቋቋመው ፋብሪካም ይህንን ታሳቢ ያደረገና የአውሮፓን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚዋቀር ነው፡፡ ጥራት ያለው ጨው በማምረት እንደ ደቡብ ሱዳን፣ ብሩንዲ፣ እንዲሁም እንደ ሩዋንዳ ላሉ አገሮች ለመላክ መታሰቡም ተገልጿል፡፡ ለአውሮፓና ለአሜሪካ ገበያዎች ለማቅረብም ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ አገሪቱ በየዓመቱ ከውጭ የምታስገባውን 90,000 ቶን የገበታ ጨው በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት ታቅዷል፡፡ ለእንስሳት መኖነት የሚውለውን አሞሌ ጨው በዘመናዊ መንገድ በማምረት በአሁኑ ወቅት ከሚሸጥበት ዋጋ በግማሽ ቀንሶ ሊሰጥ እንደሚችልም ዋጋ ተገልጿል፡፡ ለኢንደስትሪ ግብዓትነት የሚውሉ የተለያዩ ኬሚካሎችንም አዲስ በሚገነባው ፋብሪካ ውስጥ ለማምረት መታሰቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሁለቱ ድርጅቶች ጥምረት የተቋቋመው አፋር ጨው ማቀነባበሪያና ማምረቻ፣ ኢዛና ጨው የተባለውን ማቀነባበሪያ ተቋም ለስድስት ወር በሊዝ በመከራየት ጨው እያቀነባበረ ይገኛል፡፡ የፋብሪካ የማምረት አቅም በወር 300,000 ኩንታል ነው፡፡ የአገሪቱ ወርሀዊ የገበታ ጨው ፍላጎት ከ380,000 በላይ ሲሆን፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ከሚያስፈልገው ጋር ተደምሮ በወር ከ450,000 እስከ 500,000 ኩንታል ይፈለጋል፡፡ ይህ በመሆኑም የፋብሪካውን የማምረት አቅም በወር 400,000 ለማድረስ ታቅዷል፡፡ ይህ ምርት ግን የአዲሱ ፋብሪካ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ለስድስት ወራት ያህል የሚቆይ ነው ተብሏል፡፡
በካዳባ አክሲዮን ማኅበር የሥራ አመራር ቦርድ አባል የሆኑት አቶ ሳዲቅ መሐመድ፣ ‹‹በአፍዴራ ሐይቅ ዙሪያ በጨው ምርት ሥራ የተሰማሩ አምራቾች ድርጅቱን እንዲቀላቀሉ እንፈልጋለን፤›› በማለት ማኅበሩ የአባላቱን ቁጥር የማብዛት ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ የፋብሪካው ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ በተጣለ ማግሥት ግንባታው እንደሚጀመርና በስድስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምርም አስታውቀዋል፡፡
ከካዳባ ጋር በባለቤትነት ፋብሪካውን እያቋቋመ የሚገኘው ሰኢድ ያሲን ቢዝነስ ግሩፕ፣ ካዳባ ከመፈጠሩ በፊት ከአፍዴራ አምራቾች ጨው እየገዛ ለአገሪቱ ያቀርብ የነበረ ድርጅት ነው፡፡ በ2006 ዓ.ም. ካዳባ ሲቋቋም የማከፋፈሉን ሥራ ተቀብሎት መሥራት ጀምሮ ነበር፡፡
የአፍዴራ ጨው በባለሙያ ክትትል ተደርጎለት ቢመረት ከሌሎች አካባቢዎች (ከዶቢና ከአፍቄር) ከሚመረተውም ሆነ ከውጭ ከሚገባው ጭምር በጥራቱ የተሻለ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ የአፍዴራ ጨው ሐይቅ ከብክለት የፀዳ፣ ባዕድ ነገሮች ያልተቀላቀሉበት ንፁህ የጨው ክምችት የሚገኝበት እንደሆነ በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ይሁን እንጂ ለአምራቾች ዘንድ ለጥራት ትኩረት ስለማይሰጥ ከማምረቻ ኩሬው መሬ እየወጣ መሬት ላይ ይከመራል፡፡ ለብዙ ጊዜም መሬት ላይ ስለመሚቀመጥ አቧራና ሌሎች ባዕዳን ነገሮች እየበከሉት፤ በምርት ሒደት ወቅትም በባለሙያ የታገዘ ክትትል ስለማይደግበት፣ ሽያጩም በኮታ ስለሚደለደልና የጥራት ውድድር ስለሌለ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የጨው ጥራት ችግር ተንሰራፍቶ ይኛል፡፡
