Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ኢትዮጵያ ያልተጠቀመችበት የማር ምርት

$
0
0

በኢትዮጵያ ከሚመረተው የማር ምርት ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ለጠጅ መጣያነት አለያም ለቤት ውስጥ ፍጆታ ብቻ እንደሚውል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህም ውስጥ አብዛኛው ማር ማስገኘት የሚጠበቅበትን ያህል ጥቅምና ውጤት ሳያስገኝ እንደሚገባክን ሲነገር ቆይቷል፡፡

አገሪቱ በየዓመቱ የምታገኘው የማር ምርት በውጭ ገበያዎች ተወዳዳሪ እንድትሆን የሚያስችላት ቢሆንም፣ አብዛኛው ለጠጅ መጣያነት እኩሌታውም እንዲሁ ለቤት ውስጥ ፍጆታ እየዋለ እንደሚገኝ ያስታወቁት፣ የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ የሥጋ፣ የማር እንዲሁም የመኖ አቅርቦት አስተባባሪው ዶክተር ተቀባ እሸቴ ናቸው፡፡

ዶ/ር ተቀባ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ በየዓመቱ እስከ 500 ሺሕ ቶን የማር ምርት የምታመርት ሲሆን፣ በአገሪቱ አብዛኛው አካባቢዎችም ማር በቀላሉ ማምረት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በትግራይና በአማራ ክልሎች ነጭ ማር በብዛት ማምረት የሚቻልባቸው አመቺ ተፈጥሯዊ ይዘቶች አሉ፡፡

በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች በተለይ ቡና በሚበቅልባቸው አካባቢዎች ማር እንደልብ የሚገኝ ሲሆን፣ በተለይ በማር አምራችነት ቀለበት ውስጥ እንደሚካተቱ ከሚነገርላቸው የወለጋ-ኤሊባቡር፣ የጅማ-ቦንጋ መዳረሻዎች ውስጥ ማር በብዛት ማግኘት እንደሚቻል ዶ/ር ተቀባ አብራርተዋል፡፡ እነዚህ አካባቢያዎች ሁሌም እርጥበታማ በመሆናቸውና ዕፅዋቶችንም ከዓመት ዓመት ስለሚያበቅሉ፣ ንቦች እንደልብ መቅሰም የሚችሉበት ዕድል አላቸው፡፡ ንቦቹ በእነዚህ አካባቢዎች ከሚያገኙት የተክል አበባ ንፁህ የተፈጥሮ ማር ስለሚያመርቱ፣ የኢትዮጵያን ማር ከሌላው ዓለም ልዩ እንደሚያደርገው ዶ/ር ተቀባ ይናገራሉ፡፡

 ማሩ ብቻም ሳይሆን ሰምን ጨምሮ ከውስጡ የሚወጡ ስድስት ዓይነት ለልዩ ልዩ አገልግሎቶች የሚውሉና ዋጋቸውም ከማር ይልቅ እጥፍ ዋጋ የሚያወጡ ምርቶች እንደሚመረቱ ያብራሩት ዶ/ር ተቀባ፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተመረተ ያለው ማር በብዛት በኋላ ቀር ቀፎች ውስጥ በመሆኑ ከምርቱ መባከን ባሻገር የሚመረተውም ያለ አግባብ ጥቅም ላይ እየዋለ በመሆኑ የማር ምርት በአግባቡ ተይዟል ለማለት እንደሚያስቸግር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ለምሳሌ ደኅንነቱ ያልተጠበቀ ማር በአዝዋሪዎች እጅ እየገባ፣ ከባዕድ ነገሮች ጋር እየተቀላቀለ በየመንገዱ ሲሸጥ ማየት የተለመደ ነው፤›› በማለት ዶ/ር ተቀባ አደገኛ የንግድ እንቅስቃሴዎችም የሚስተዋሉበት ምርት ስለመሆኑም አብራርተዋል፡፡

ከልማዳዊው የማር ማነብ ሥራ ባሻገር፣ በአሁኑ ወቅት 20 ድርጅቶች ንፁህ ማር አጣርተው ወደ ውጭ የሚልኩ ሲሆን፣ ሌሎች 11 ያህል ኩባንያዎች ደግሞ የማር ተረፈ ምርት የሆነውን ሰም የሚልኩ ስለመሆናቸው ታውቋል፡፡ ይህ ግን ዓባይን በጭልፋ የመቅዳት ያህል እንደሆነ ይታያል፡፡ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩና ልዩ ልዩ ጣዕም ያላቸው የማር ዓይነቶች የሚመረቱ ሲሆን፣ እነዚህን በማጥናት የትኛው ለምን አገልግሎት እንደሚውል፣ እንዴት መሸጥ እንዳለበት፣ ደረጃውስ ምን መሆን ይገባዋል የሚለውን ጉዳይ የሚደነግግ ሕግ ባለመኖሩ ዘርፉ በተገቢው መንገድ እንዳያድግ እንቅፋት መሆኑን ዶ/ር ተቀባ አብራርተዋል፡፡ ‹‹ሕግ ባለመኖሩ ግብይቱን ሥርዓት አልባ አድርጎታል፤ ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ ሆኗል፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ይህን ለማስተካከል የሚያግዝ የሕግ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ሊቀርብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ማር በቀላሉ ማምረት የሚቻልባቸው በርካታ ዕድሎች እንዳሉ ሲገለጽ፣ ወደ ኢንዱስትሪዎች በማምጣት ፕሮሰስ አድርጎ ገበያ ላይ ለማዋል በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ግን ከፍተኛ ክፍተት ይታያል፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱና በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ገብተው ለመሥራት የጥራትና የብቃት ማረጋገጫ አግኝተው እየሠሩ የሚገኙ ኩባንያዎች ሦስት ብቻ መሆናቸው ይነገራል፡፡

ማርን ወደ ውጭ ከመላክ የሚያግድ ምንም ዓይነት የገበያ ችግር እንደሌለ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ፣ በቅርቡም የቻይና ገበያዎች በዋቢነት ይጠቀሳሉ፡፡ ይሁንና አገሮች የሚያስቀምጡት የጥራትና የደረጃ ማረጋገጫ ጥያቄዎች የማር ዘርፉን ውጤታማነት ይፈታተናሉ፡፡ የማር ጥራትና ደኅንነቱን ለማስፈተሽ እስከ 60 ሺሕ ዶላር ለላቦራቶሪዎች ወጭ ማድረግ የሚጠይቅ መሆኑም ፈታኝ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአገሪቱ ከሚታየው አሠራር አኳያ ባህላዊ ቀፎዎች አብዛኛውን ድርሻ ይዘው መገኘታቸውም ለጥራቱ መጓደል ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡

ከእነዚህ ቀፎዎች በአንድ የምርት ዘመን ከአራት እስከ አምስት ኪሎ ግራም ማር የሚገኝ ሲሆን፣ በአንፃሩ ከዘመናዊው የንብ ቀፎ በአማካይ ከ25 እስከ 30 ኪሎ ግራም ማር ማግኘት እንደሚቻል ዶ/ር ተቀባ ያብራራሉ፡፡ በአንድ የንብ ቀፎ አማካይነት   ከ500 ሺሕ ኪሎ ግራም በላይ ማምረት ቢቻልም፣ እስካሁን የሚመረተው መጠን ግን አሥር በመቶው ብቻ ነው፡፡ ‹‹ይህ መሆኑ ደግሞ በዓለም አቀፍ ገበያ ያለን ድርሻ ያሳንሰዋል፤›› ብለዋል፡፡

በዓለም ገበያ አንድ ኪሎ ግራም ማር ከሦስት እስከ አራት ዶላር የሚሸጥ ሲሆን፣ ሰም ግን አሥር ዶላር ያወጣል፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ማርና የማር ተረፈ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ያገኘችው ገቢ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከሆለታ የማር ምርምር ማዕከል የተገኙ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ አብዛኛው ማር አናቢ አነስተኛው ገበሬ ነው፡፡ ማር በአብዛኛው በልማዳዊ አመራረት ዘዴ ተመርቶም ቢሆን ለገበያ የሚውል ምርት መሆኑን የሚያብራራው የሆለታ ምርምር ማዕከል፣ ከሚመረተው ማር ውስጥ 90 ከመቶው ለገበያ የሚውል ነው፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2008 ጀምሮ በአውሮፓ ኅብረት ማረጋገጫ የተሰጠው አገሪቱ የሰም ምርት ለወጪ ገበያ እንዲበቃ ማስቻሉም በጥሩ ጅምሩ ይጠቀሳል፡፡

በኢትዮጵያ ከ10 ሚሊዮን በላይ የንብ ዝርያዎች እንዳሉ ይታመናል፡፡ ከእዚህ ውስጥ 7.5 ሚሊዮኖቹ በንብ አናቢዎች እጅ እንደሚገኙ ሲገመት የተቀሩት ግን እንዲሁ በየጫካው የሚኖሩ እንደሆኑ የምርምር ማዕከሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles