ኢትዮጵያዊ ስያሜ ያለውና ከመነሻውም በኢትዮጵያ መገኘቱ የሚታመነው ጎመን ዘር፣ በሳይሳዊ አጠራሩ ብራሲካ ካሪናታ፣ አቢሲኒያን ሬፕ፣ አቢሲኒያን ሙስታርድ አለያም ኢትዮጵያም ሙስታርድ እንደሚባል መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ከኢትዮጵያ ባሻገር በበርካታ አገሮች የሚበቅለው ይህ ተክል፣ ለምግብ ዘይትነት በፋብሪካዎች ተጨምቆ ለገበያ እየዋለ ይገኛል፡፡ በተክል ዝርያነት የሚፈረጀው የጎመን ዘር፣ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው መስክ የባዮፊውል ነዳጅ ሊመረትበት ምርምር ሲደረግበት ቆይቷል፡፡ ከአራት ዓመታት በፊትም የመጀመሪያው የሙከራ በረራ ከጎመን ዘር በተመረተ ነዳጅ መደረጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
እርግጥ እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ አቪዬሽን ኢንዱስትሪው ከዕፅዋትና አትክሎቶች ብስባሽ የሚሰናዳ ነዳጅ መጠቀም እንደጀመረ የሚጠቁሙ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል፡፡ ግሪን ፍላይት ኢንተርናሽናል፣ ቨርጂን አትላንቲክ፣ ኤር ኒውዚላንድ፣ ኮንቲኔንታል ኤርላይንስ፣ ጃፓን ኤርላይንስ እንዲሁም የአሜሪካ አየር ኃይልን ጨምሮ በርካታ አየር መንገዶች ከወዳደቁ ዕፅዋትና ብስባሾች፣ ከአልጌ፣ ከጉሎ፣ ከጃትሮፋና ከመሳሰሉት የሚመረተውን ነዳጅ መጠቀም መጀመራቸው ታውቋል፡፡ የጎመን ዘርም ለአውሮፕላን ነዳጅ እየዋሉ ካሉ ውጤቶች መካከል እየተቀላቀለ መጥቷል፡፡
የዚህ ሁሉ መነሻው ከሰሞኑ ይፋ የተደረገ የጥናት ውጤት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም ፋብሪካ ላለፉት ስምንት ዓመታት ምርምር ሲያደርግበት እንደቆየ የገለጸው ውጤት ይጠቀሳል፡፡ ከጎመን ዘር ተረፈ ምርት የሚያዘጋጃቸውን የእንስሳት መኖ እንዲሁም ሰብል ለመቆጣጠር የሚያስችል፣ ፀረ ተባይ ከጎመን ዘር ተረፈ ምርት በማምረት ወደ ገበያ ለማውጣት መዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅና የምርምር ቡድኑ መሪ አቶ ፈለቀ ስብኃቱ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ዘይት ተጨምቆበት ተረፈ ምርቱ ይደፋ የነበረው የጎመን ዘር አሁን ለእንስሳት መኖነትና ለፀረ ተባይ ርጭት የሚውል ምርት በፋብካው ተቀናብሮ ለገበያ የሚውልበት ምዕራፍ ላይ መደረሱንም የቡድኑ መሪ ተናግረዋል፡፡
ለምግብነት መዋል የማያስችለው የመርዛማነት ይዘቱ የተወገደለትና የቅባት ይዘቱ የወጣለት የጎመን ዘር መኖ (Detoxified and Defatted Ethiopian Mustard Mill) መዘጋጀቱ፣ በየዓመቱ እንደሚደፋ የሚገመተው ከ400 እስከ 500 ሺሕ ኩንታል ተረፈ ምርት መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርገዋል፡፡ በተለይ በዶሮ እርባታ መስክ እስከ 70 ከመቶ የሚደርሰውን የኢንቨስትመንት ወጪ የሚሸፍነውን የመኖ ፍጆታ ለመቀነስ እንደሚያስችል አቶ ፈለቀ ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ፈለቀ ማብራሪያ፣ እስካሁን ድረስ በመርዛማ ይዘቱ ለምግብነት እንዳይውል ያደረገው ተረፈ ምርት (ኤክስፔለር ኬር) እንዲሁ ሲደፋ ቢቆይም፣ 46 ከመቶ የፕሮቲን ንጥረ ነገር ይዘት እንዳለው በጥናት መረጋገጡን ጠቁመዋል፡፡ ይህ ደግሞ አኩሪ አተርን ጨምሮ በርካታ ግብዓቶችን ለመተካት የሚያስችል አቅም እንዳለው ማረጋገጫ መስጠቱን ያብራራሉ፡፡ የጎመን ዘር ተረፈ ምርት ከሥጋና የሥጋ ተረፈ ምርት ከሆኑ ምንጮች የሚገኘውን መኖ ለመተካት የሚያስችል የፕሮቲን ይዘት በመያዙ ተመራጭ እንደሚያደርገውም ተገልጿል፡፡
ይህንኑ የምርምር ውጤት ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅቱ መጠናቀቁን ሲገልጹም፣ በአሁኑ ወቅት በሙከራ ደረጃ በቀን 40 ቶን የእንስሳት መኖ ከጎመን ዘር ተረፈ ምርት የሚያመርቱ ሁለት ፋብሪካዎች ሥራ መጀመራቸውን፣ ዋናው ፋብሪካም በብዛት ለማምረት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አቶ ፈለቀ አብራርተዋል፡፡
የምርምር ውጤቱ ለዶሮ አርቢዎችና አምራቾች ማኅበር አባላት ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ በተደረገበት ወቅት፣ ከመኖ ባለሙያዎችና ከፋብሪካዎች የተነሳው ጥያቄ ጥራቱና የአቅርቦቱን አስተማማኝነት በሚመለከት ነበር፡፡ አዲሱ ምርት እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ የሚያበቃ ዝግጅት እንደተደረገበት፣ የጥራት ጥያቄውም ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡ በቅርቡ የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መብት ማረጋገጫ ዕውቅና እንደሚያገኝና ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የእንስሳት መድኃኒትና ምግብ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ምርቶቹን በማስመዝገብ ፈቃድ ለማግኘት እየተዘጋጀ እንደሚገኝ አቶ ፈለቀ ገልጸዋል፡፡
በአርሲና በባሌ አካባቢ በሚኖሩ ገበሬዎች ማሳዎች ውስጥ በተደረገ ጥናት፣ ስንዴና ገብስ በሚያመርቱበት ወቅት የጎመን ዘር በማሳዎቻቸው ዙሪያ እንደሚዘሩ፣ ይህም ተባዮችን ለመከላከል በማሰብ የሚያደርጉት እንደሆነ የተብራራ ሲሆን፣ ከሌሎች ለመኖነት ከሚውሉ ተክሎች ይልቅ የጎመን ዘር ለዚህ ተግባር የሚውለው ግሉሲኖኔት የተባለው መርዛማ ይዘት በውስጡ ስለሚገኝ ነው፡፡ ይህንን መርዛማ ይዘት በማውጣት ለፀረ ተባይ ማምረቻነት እንዲውል በማድረግ የኬሚካል ውጤቶችን ለመተካት እንደሚውል ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ቅመማ ቅመም ፋብሪካ ከ45 ዓመታት በፊት በአሜሪካውያን የተቋቋመ ሲሆን፣ በመንግሥት ተወርሶ ሲተዳደር ከቆየ በኋላ ከስምንት ዓመታት በፊት በአሁኑ የፋብሪካው ባለንብረት እጅ በአቶ አካሉ ገለታ ባለቤትነት እየተዳደረ ይገኛል፡፡ አቶ አካሉና ቤተሰቦቻቸው የሚመሯቸው ሌሎችም እህት ኩባንያዎች ይጠቀሳሉ፡፡
በሎጂስቲክስ መስክ በመርከብ አስተላላፊነት የሚታወቀው አካካስ ሎጂስቲክስ ኩባንያ፣ ጊፍቲ ቅመማ ቅመም፣ ጊፍቲ ዘይት፣ ጊፍቲ ዱቄት የተባሉ ምርቶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ጨምሮ በ420 ሔክታር መሬት ላይ አኩሪ አተርና በቆሎ የሚያመርትበት እርሻ በወለጋ ዞን እንዳለውም የፋብሪካው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በሁለት ሚሊዮን ብር ካፒታልና በ20 ሚሊዮን ብር ሀብት የሚንቀሳቀሰው ቅመማ ቅመም ፋብሪካው፣ የጨው ማጣሪያና ማምረቻ ፋብሪካን ጨምሮ በደቡብ ክልል፣ አረቃ ወረዳ ወላይታ ዞን ውስጥ የሚያስተዳድረው የፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ማቀነባበሪያም ከሚጠቀሱ እህት ኩባንዎቹ መካከል ይመደባሉ፡፡
