Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ለቡና አቅራቢዎች የተራዘመው ብድር መክፈያ ጊዜና የባንኮች ሥጋት

$
0
0

በዳዊት ታዬ

በአንዳንድ ቡና አብቃይ አካባቢዎች የሚገኙ ቡና አቅራቢዎች፣ ከቡና ዋጋ ማሽቆልቆልና ከቡና ምርት እጥረት ጋር በተገናኘ ባሰቡት መጠን ልክ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የሚፈተኑባቸው የምርት ዘመኖች አሉ፡፡ ከጥቂት ዓመታት በፊት በተለይ በሲዳማ ቡና አብቃይ አካባቢዎች የተከሰተው ችግር ለአብነት ሊጠቀስ ይችላል፡፡

በ2008 የምርት ዘመንም በርካታ ቡና አቅራቢዎች አትራፊ መሆን የሚያስችላቸውን ውጤት አላገኙም፡፡ ባሰቡት ልክ ያልሆነላቸው ቡና አብቃዮች የገጠማቸውን ችግር ለመቅረፍ ዘንድሮም የመንግሥትን ዕርዳታ ለመጠየቅ ተገደዋል፡፡

በተለይ በሲዳማ አካባቢ ያሉ ቡና አብቃዮች ባለፉት ሁለት ዓመታት የጠበቁትን ያህል ማግኘት ባለመቻላቸው ከተለያዩ ባንኮች የወሰዱትን ብድር ለመመለስ ስለተቸገሩ  የመንግሥትን እገዛ እንደሚሹ አስታውቀዋል፡፡

የብድር መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉም ባንኮች ለእነዚህ ቡና አቅራቢዎች ሰጥተዋል፡፡ ቡና አቅራቢ ተበዳሪዎቹ ከባንኮች ብድሩን ለመውሰድ ከቡና መፈልፈያ ድርጅቶቻቸው ጀምሮ መኖሪያ ቤት፣ ሕንፃዎችንና ተሽከርካሪዎችን በማስያዝ ለብድር ዋስትና አውለዋል፡፡

ብድሩን ለመመለስ ባለመቻላቸውም ያስያዙት ንብረት በሐራጅ ሊሸጥባቸው በመሆኑ መንግሥትን ድረስልን በማለት ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡ ብድር የመመለስ አቅም ማጣት በመበራከቱ የበርካታ አቅራቢዎች ንብረት ለብድር አመላለስ ይረዳ ዘንድ በባንኮች ተሸጧል፡፡ ቡና አምራቾቹ ግን ከዚህ በኋላ የምናሲዘው ንብረት አጥተናል እያሉ ነው፡፡

ባንኮች በበኩላቸው የቡና ዋጋ ሲወድቅ እነሱም የፈተናው ተጋሪዎች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ አንዳንዴ ለብድር ማስከበሪያነት የሚያዘው ንብረት የቡና መፈልፈያ ሲሆን፣ የቡና ዋጋ በወደቀበት ዘመን ንብረቱን ይሸጥ ሲባል ገዥ የሚጠፋበት ጊዜ እንደሚፈጠር ባንኮቹ ይገልጻሉ፡፡ ምክንያቱም መፈልፈያው የሚፈለገው በቡና አቅራቢው ነውና፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሩት የንግዱ ኅብረተሰብና የመንግሥት የጋራ የምክክር መድረክ ላይ ከሲዳማ አካባቢ የመጡ ቡና አቅራቢዎች የቡና ሥራ ባስከተለባቸው ኪሳራ ምክንያት የባንክ ብድር ለመክፈል መቸገራቸውን አስታውቀው ነበር፡፡

ያሏቸውን ንብረቶች በማስያዝ ብድር መውሰዳቸውን የገለጹ ቡና አቅራቢዎች፣ ለባንኮች የሚከፍሉት ገንዘብ ባለማግኘታቸው ባንኮች ንብረቶቻቸውን ሊሸጡባቸው መሆኑን፣ የአንዳንዶቹም መሸጡን በመጠቆም መንግሥት ችግራቸውን እንዲያይላቸው አቤት ብለው ነበር፡፡

ቡና አንድ ጊዜ ጥሩ ውጤት የሚሰጥ ሌላ ጊዜ የሚለግም በመሆኑ (በዓለም ደረጃ የቡና ገበያ ‹‹ቮላታይል›› ወይም ዋዣቂ እየተባለ ይገለጻል)፣ በቀጣይ የምርት ዘመኖች ከሚገኝ ገቢ የባንክ ብድራቸውን እንዲከፍሉ ካልተመቻቸላቸው በቀር በርካታ ቡና አቅራቢዎች ከጨዋታ ውጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመሩት  መድረክ ላይ ተንፀባርቆ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ የወጣ ሰርኩላር እንደሚያሳየውም እንዲህ ያለው ጥያቄ ዘንድሮም መቅረቡን ነው፡፡ ይኼንን ጥያቄ ለመመለስ ይመስላል የባንክ ብድር ለመክፈል አቃተን ላሉ አንዳንድ ቡና አቅራቢዎች የተበደሩት ገንዘብ የመክፈያ ጊዜ እንዲዘገይ ሰርኩላሩ ያሳስባል፡፡

ባንኮች ብድር ከሰጡ በኋላ ብድሩ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ካልተመለሰ ለብድሩ ዋስትና የተያዘውን ንብረት በሐራጅ ጨረታ በመሸጥ ገንዘቡን ገቢ ማድረግ አሠራራቸው ነው፡፡ በዚሁ መሠረት የተበዳሪ ቡና አቅራቢዎች ንብረቶችን በጨረታ ለመሸጥ ባንኮች  እየንቀሳቀሱ በነበረበት ወቅት ግን ሰርኩላሩ ብቅ ብሏል፡፡

ከብሔራዊ ባንክ ለባንኮች የተሰራጨው ሰርኩላር፣ የቡና አቅራቢዎችን የብድር ዕዳ  ጉዳይ መንግሥት በተለየ የያዘው በመሆኑ ላልተወሰነ ጊዜ የቡና አቅራቢዎቹ ንብረቶች በጨረታ እንዳይሸጡ የሚገደብ ነው፡፡ ንብረታቸው ለሽያጭ እዳይቀርብ የተባሉት ቡና አቅራቢዎችም ስም ዝርዝር ከሰርኩላሩ ጋር ተያይዞ ለባንኮች ተላልፏል፡፡

ከአንዳንድ ባንኮች ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ በብሔራዊ ባንክ ሰርኩላር መሠረት በጨረታ ሊሸጡ የነበሩና ለጨረታው ሒደት ሲነገሩ የነበሩ የጨረታ ማስታወቂያዎች እንዲቆሙ ተደርገዋል፡፡

ሆኖም ይህ ዕርምጃ ባንኮች የሰጡትን ብድር ከማስመለስ እንዲዘገዩ መገደዳቸውን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

አሁን ባንኮቹን እያሳሰበ ያለው ጉዳይ ደግሞ በስም ዝርዝር ጭምር የተጠቀሱት ቡና አቅራቢዎች ብድራቸውን ካልከፈሉ ንብረታቸውን ሸጠው ገንዘባቸውን ማስመለስ የሚሉችሉት መቼ እንደሆነ ባለመታወቁ ነው፡፡ የተላለፈላቸው ሰርኩላር ቀነ ገደብ አላስቀመጠም፡፡

የመንግሥት እርምጃ ግን ለቡና አብቃዮቹ እፎይታ የሰጣቸውን አትርፏል፡፡  ይሁን እንጂ አሁንም የቡና ገበያው ካልተስተካከለ ብድሩን ሙሉ ለሙሉ ለመክፈል  ሊችገሩ ይችላሉ የሚለው ሥጋት ግን ብዙዎች የሚጋሩት ነው፡፡  

የብድር መክፈያ ጊዜያቸው መራዘሙና ያስያዙት ንብረት ሳይሸጥ መቆየቱ በሌላ በኩል አሁንም ጫናውን በቡና አቅራቢዎቹ ላይ ማድረጉ እየተነገረ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የብድር መክፈያው በተራዘመ ቁጥር ሊከፈል የሚገባው ወለድ የማያስቀረው በመሆኑ ነው፡፡

የብሔራዊ ባንክ ሰርኩላር ያልተለመደ ቢሆንም፣ ባንኮች እነዚህን አቅራቢዎች ለመደገፍ ጥረት አድርገው እንደነበር ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ የሚያሻቸውን መደገፍ በባንክ ዘርፍ የተለመደ እንደሆነ የገለጹ አንድ የባንክ ኃላፊ፣ አሁን ባንኮችን የቸራቸው ግን ብድር መክፈል የሚችሉትም በዝርዝሩ ውስጥ መካተት አለመካተታቸውን ለይቶ ማወቅ አለመቻሉ ነው፡፡

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles