Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

የደቡብ ግሎባል ባንክ ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ድርሻቸውን በእጥፍ ለማሳደግ ወሰኑ

$
0
0

የተከፈለ ካፒታሉ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. 500 ሚሊዮን ብር ማድረስ የሚጠበቅበት የደቡብ ግሎባል ባንክ ባለአክሲዮኖች የአክሲዮን ድርሻቸውን በእጥፍ ለማሳደግና ዓመታዊ ትርፋቸውን ለካፒታል ማሳደጊያነት ለማዋል ውሳኔ አሳለፉ፡፡

የባንኩ ባለአክሲዮኖች ባለፈው ቅዳሜ ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ ባሳለፉት ውሳኔያቸው መሠረት፣ በርካታ የባንኩ ባለአክሲዮኖች እስካሁን ያላቸውን የአክሲዮን ድርሻ በእጥፍ ለማሳደግ የተስማሙበትን ቅጽ በዕለቱ እስከመሙላት ደርሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ባንኩ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ የተከፈለ ካፒታሉን 500 ሚሊዮን ብር ማድረስ የሚገባው በመሆኑ፣ ባለአክሲዮኖቹ ትርፋቸውን ለካፒታል ማሳደጊያ ከማዋል ባሻገር የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት ካፒታሉን ለመሙላት የሚያስችሉ ሌሎች ተግባራትን ለመከወን ተስማምተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የጊዜ ገደብ በፊት የተከፈለ ካፒታሉን መሙላት የሞት ሽረት ጉዳይ ስለሆነ፣ ባለአክሲዮኖች ከባንኩ ጋር ተባብረው በመሥራት የባንኩን ዕድገት ማስቀጠል የግድ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ሌሎች አዳዲስ አክሲዮን ገዥዎችን በማምጣት ጭምር ባንካቸውን ለማገዝ እንደሚጥሩም ባለአክሲዮኖቹ የገለጹ ሲሆን፣ ገንዘባቸውን በባንኩ ከማስቀመጥ ጀምሮ ሌሎች ሥራዎቻቸውን ከባንኩ ጋር በማስተሳሰር ከተቻለ የሚፈለገውን ውጤት በአጭር ጊዜ ማምጣት ይቻላል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ባንኩ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ካፒታሉ 322.1 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የገለጹት የባንኩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኑረዲን አወል፣ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ከነበረው በ103.2 ሚሊዮን ብር ወይም በ47 በመቶ ጭማሪ የታየበት ነው፡፡

የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ በ322 ሚሊዮን ብር የደረሰ ቢሆንም፣ ባንኩ የተከፈለ ካፒታሉን 500 ሚሊዮን ብር ለማድረስ ከ175 ሚሊዮን ብር በላይ ማሰባሰብ ይጠበቅበታል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ በበኩላቸው ባንኩ በተያዘው በጀት ዓመት ዋነኛ ክንዋኔ ካፒታሉን ማሳደግ በመሆኑ፣ ለዚህ የሚያግዙ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉን ሞልቶ በቀጣዩ ዓመት የተሻለ ትርፍና ዕድገት ይኖራል የሚል እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡

በቅዳሜው ጠቅላላ ጉባዔ የባንኩ የ2008 በጀት ዓመት ሪፖርት በባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኑረዲን የቀረበ ሲሆን፣ የ2008 በጀት ዓመት ትርፉን በሁለት እጅ በማሳደግ 68 ሚሊዮን ብር መድረሱን ለባለአክሲዮኖቹ አሳውቀዋል፡፡  

ከዚህም ሌላ ዓመታዊ ገቢ 74.5 በመቶ እንዳደገና በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ 194.1 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል፡፡

በ2008 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 871.8 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ የአስቀማጮች ቁጥር ደግሞ ከ25,351 ወደ 36,615 ወይም የ44 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ አቶ ኑረዲን ገልጸዋል፡፡

እንደ ባንኩ ሪፖርት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሰጠው ብድር በ76.8 በመቶ አድጎ 599.3 ሚሊዮን ብር ሲደርስ፣ የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱን ደግሞ በ142 በመቶ በማሳደግ 939 ሚሊዮን ብር መድረሱ ተመልክቷል፡፡

የደቡብ ግሎባል ባንክ አሴት 1.3 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ የሚያመለክተው የባንኩ ሪፖርት፣ በ2009 ዓ.ም. ሌሎች አዳዲስ ዘመናዊ የባንክ አሠራሮችን በመተግበር ተወዳዳሪ ባንክ ሆኖ ለመውጣት ይሠራል ተብሏል፡፡ ባንኩ ከ7,000 በላይ ባለአክሲዮኖች አሉት፡፡

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles