Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

አንበሳ ኢንሹራንስ ከዓምናው ያነሰ ትርፍ አስመዘገበ

$
0
0

- በ2009 ትርፉን ከሁለት እጅ በላይ ለማድረስ ማቀዱን አስታውቋል

በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ካሉ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው አንበሳ ኢንሹራንስ በ2008 በጀት ዓመት ያስመዘገበው የትርፍ መጠን በበጀት ዓመቱ በዕቅድ ከያዘውም ሆነ ከቀዳሚው ዓመት የትርፍ መጠን ያነሰ ሆኗል፡፡

ታኅሳስ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ ይፋ ባደረገው ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት፣ ዓምና ኩባንያው ከታክስ በፊት ያስመዘገበው ትርፍ 16.9 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ግን ከካቻምናው አኳያ የ23 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ለዘመኑ ከተያዘው ዕቅድ ጋር ሲነፃፀርም በ27 በመቶ ያነሰ ነበር፡፡

የትርፍ መጠኑ ማነስም ለአንድ አክሲዮን በአማካይ የሚከፈለውን የትርፍ ድርሻ እንዲቀንስ አስገድዷል፡፡ እንደ ኩባንያው መረጃ በ2007 ዓ.ም. 28 በመቶ የነበረው የአንድ አክሲዮን የትርፍ ድርሻ በ2008 ወደ 20 በመቶ ሊቀንስ ችሏል፡፡ ለቅናሽ ምክንያት ከተደረጉ መካከለም የካሳ ክፍያ መጨመር፣ አጠቃላይ ወጪ መጨመርና ለኢንሹራንስ የሽያጭ ወኪሎችና ደላሎች የኮሚሽን ክፍያ መጨመራቸው እንደሆነ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

ኩባንያው በበጀት ዓመቱ ከውል ሥራ የመነጨ 29.4 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘት ቢችልም፣ ከታቀደው አኳያ የ21 በመቶ፣ ካለፈው ተመሳሳይ ዓመት ውጤት ጋር ሲነጻጸርም የ17 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

በ2008 በጀት ዓመት የካሳ ክፍያ አፈጻጸምን የተመለከተው የኩባንያው ሪፖርት እንደሚያሳየው በአጠቃላይ የተከፈለው ካሳ 135.9 ሚሊዮን ብር እንደነበር ነው፡፡ በእንጥልጥል ላይ ያለ 77.9 ሚሊዮን ብር የካሳ ጥያቄም ወደ 2009 በጀት ዓመት መተላለፉን ያሳያል፡፡ 20.9 ሚሊዮን ብር ደግሞ ላልተመዘገቡ የካሳ ክፍያዎች መጠባበቂያ የተያዘ በጀት ነው ተብሏል፡፡

ለካሳ ክፍያ ጥያቄዎች መናር ምክንያት የነበሩት የሥራ አድማስ መስፋትና የተለያዩ የቦንድ ካሳ ክፍያዎች ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸሩ ከፍተኛ መሆናቸው፣ በተሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰው አደጋ በብዛትና በመጠን ማሻቀቡና የመለዋወጫ ዕቃዎችና የጉልበት ዋጋ መጨመር ተጠቃሾች ናቸው፡፡

የትርፍ መጠኑ ቢቀንስም የተሻለ ሥራ ስለመሠራቱ የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ የኦፕሬሽን ዕቅድ አፈጻጸም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 282.1 ሚሊዮን ብር የአረቦን ገቢ ያስመዘገበ ሲሆን፣ ይህም በ2007 ዓ.ም. ከተመዘገበው ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ከተያዘው ዕቅድ ጋር ሲነጻጸር በ13 በመቶ ማለትም 31.7 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንደነበረው ጠቅሷል፡፡

በበጀት ዓመቱ ለሞተር ከሚሰጥ የመድን ሽፋን 62.5 በመቶ አረቦን ገቢ ለመሰብሰብና ቀሪውን 37.5 በመቶ ደግሞ ሞተር ነክ ካልሆኑት ለማሟላት አቅዶ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ቢያስታውቅም፣ በዕቅዱ መሠረት ግን ሊከናወን አልቻለም፡፡ ለዚህም የቀረበው ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ ያለው የገበያ አማራጭና ውድድር ነው፡፡ በመሆኑም 70.4 በመቶውን ድርሻ ከሞተር ሲሰበስብ ቀሪውን 29.6 በመቶ ደግሞ ሞተር ነክ ካልሆኑ መስኮች መሰብሰቡ ለአብነት ተጠቅሷል፡፡ የገንዘብ ነክ የዋስትና ዓይነት 11.2 በመቶ ሲይዝ የባህር ላይ ጉዞ 4.5 በመቶ፣ የእሳትና መብረቅ 3.9 በመቶ፣ ኢንጂነሪንግ 3.5 በመቶ እንዲሁም ለኃላፊነት የሚሰጠው የመድን ሽፋን 3.4 በመቶ ድርሻ ይዘዋል፡፡ ከገንዘብ ነክ የዋስትና ዓይነት በስተቀር ሌሎቹ ሞተር ነክ ያልሆኑት የዋስትና ዓይነቶች ከዕቅድ በታች አፈጻጸም አሳይተዋል፡፡

በሌላ በኩል የኩባንው ዕዳ በ2008 ዓ.ም. የነበረው አፈጻጸም ከ2007 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ61.7 ሚሊዮን ብር ወይም የ34 በመቶ ብልጫ በማሳየት ወደ 245 ሚሊዮን ብር ሊያድግ ችሏል፡፡ ለዚህም ውጤት የኩባንያው የአረቦን መጠባበቂያ መጠን መጨመር በዋናነት ተጠቃሽ ሆኗል፡፡

አጠቃላይ የአረቦን ገቢው (እ.ኤ.አ. ከ2007/08 እስከ 2015/16 በነበረው ጊዜ ውስጥ) በአማካይ 20.5 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ያስታወሰው ሪፖርቱ፣ በ2008 በጀት ዓመት በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ6.1 ቢሊዮን ብር በላይ አረቦን ከመድን ሽፋን እንደተሰበሰበ መረጃው ይጠቁማል፡፡ ከዚህ አጠቃላይ አረቦን ውስጥ የአንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ ድርሻ 4.6 በመቶ ወይም 282.1 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ የግል የመድን ኩባንያዎች ከሰበሰቡት 3.9 ቢሊዮን ብር አረቦን አንፃር ሲታይ የኩባንያው የገበያ ድርሻ 7.2 በመቶ መሆኑንም የአንበሳ ኢንሹራንስ ሪፖርት አመልክቷል፡፡

በ2008 ዓ.ም. በሁሉም የሥራ ክንውኖች በተወሰነ መልኩ የተሻለ አፈጻጸም ያሳየበት እንቅስቃሴ ቢኖርም፣ በትርፍና በተከፋይ የትርፍ ድረሻዎች ላይ መቀነስ ታይቷል የሚለው የአንበሳ ኢንሹራንሽ ሪፖርት፣ ወደፊት እደርስበታለሁ ያለውን ግብም አስቀምጧል፡፡

እንደ ኩባንያው ሪፖርት በዚህ በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ እንደሚንቀሳቀስና በሦስት እጅ ጭማሪ የሚያሳይ ትርፍ እንደሚያስመዝግብ ይጠበቃል፡፡ ለዚህም በ2009 ዓ.ም. የሚሰበሰበው ጠቅላላ የውል ሥራ ገቢ በ2008 በጀት ዓመት ከተሰበሰበው በ31 መቶ ብልጫ በማሳደግ 350 ሚሊዮን ብር ለማድረስ ማቀዱ አንዱ ነው፡፡ ከውል ሥራ 55.4 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ከጥቅል ትርፍ 27.5 ሚሊዮን ብር ለማግኘት ማቀዱን አስታውቋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የተገኘው የኩባንያው ትርፍ ከግብር በኋላ 15 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ የኩባንያው የዲሬክተሮች ቦርድ 13.1 ሚሊዮን ብር ሙሉ በሙሉ ለባለአክሲዮኖች እንዲከፋፈል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

እንደ ኩባንያው ሪፖርት ከበጀት ዓመቱ ዓበይት ተግባራት ውስጥ አንዱና ግንባር ቀደም አድርጎ ያስቀመጠው ለዋና መሥሪያ ቤትና ለሁለገብ አገልግሎት የሚውል ባለ ሕንፃ ግንባታን ነው፡፡ የግንባታ ሥራው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃው ሕንፃ ሥራ ጀምሯል፡፡

የአንበሳ ኢንሹራንስ አጠቃላይ ሀብት 335 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት አኳያ የ24 በመቶ ወይም 64.4 ሚሊዮን ብር ዕድገት አስመዝግቧል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉ 66.4 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles