የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት የመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የፋይናንስ ተቋማት በሚያዘጋጇቸው ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች ላይ እምብዛም ሲታደሙ አይታዩም፡፡ ለዓመታት የፋይናንስ ተቋማት በተናጠልም ሆነ በጋራ ሲያዘጋጇቸው በቆዩት መድረኮች ላይ የመገኘት ልምድም የላቸውም፡፡
እንዲህ ባሉት ዝግጅቶች ወቅት ብሔራዊ ባንክን ወክለው በመገኘት የሚታወቁት ከሦስት ሳምንታት በፊት የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሰየሙት የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ጌታሁን ናና ናቸው፡፡
የግል ባንኮች ከሥራቸው ጋር በተገናኘ ችግር ሲገጥማቸው አቤት ማለት የሚያዘወትሩትና ስለጉዳያቸው ቀድመው የሚያመለከቱት ለምክትል ገዥው ለአቶ ጌታሁን ናና ነበር፡፡ ሐሙስ ታኅሳስ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. ማምሻውን የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ባዘጋጀው መድረክ ላይ የሁሉንም ባንኮች ኃላፊዎች ጨምሮ የብሔራዊ ባንክ አመራሮችን በአንድ ያሰባሰበው ፕሮግራም ላይ ያለወትሯቸው አቶ ተክለወልድ ከተፍ ብለዋል፡፡ የሰውየው መገኘት ለአብዛኛዎቹ የባንክ ሰዎች እንግዳ ነገር እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡
በባንክ ኢንዱስትሪው ጉምቱ ከሚባሉት ጥቂት ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት የቀድሞው የብሔራዊ ባንክ ገዥ፣ የቀድሞው የንግድ ባንክ ሥራ አስኪያጅና የቀድሞው የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ለይኩን ብርሃኑ ዘግየት ብለው ወደ ዝግጅቱ አዳራሽ ሲደርሱ፣ ከአንደበታቸው ያወጡት ቃል የአባባሉን እውነታነት ያረጋግጣል፡፡ አቶ ተክለወልድ መኖራቸውን ሲያውቁም ‹‹የማይታመን ነው፡፡ በጣም ደስ ይላል፤›› ነበር ያሉት፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥው ምክትሎቻቸውን አስከትለው በተገኙበት የሐሙስ ምሽቱ ፕሮግራም፣ ከቀድሞ የባንክ መሪዎች መካከል እንደ አቶ ጥላሁን ዓባይ ያሉትን ጨምሮ የቀድሞ የባንኮች ማኅበርና የሕብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ጌታነህንና ሌሎችንም ያሰባሰበ መድረክ ነበር፡፡ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ባልተለመደ ሁኔታ ተሰባስበው በነፃነት ያወጉበት ጊዜ እንዳልነበር በመግለጽ የዕለቱ ስብስባ እንዳስደመማቸው የገለጹም ነበሩ፡፡
የገዥው ባንክ ቁንጮ ባለሥልጣናት ተሰባስበው የታደሙበትና ሁሉንም የባንኮች መሪዎች በአንድ ቦታ ያገናኘው መድረክ፣ በአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት እንቅስቃሴ ዙሪያ ስላለ ብርቱ ጉዳይ ለመምከር የተጠራ አስቸኳይ ስብሰባ አስመስሎታል፡፡ በአራቱም አቅጣጫ የአገሪቱን የገንዘብ እንቅስቃሴ የሚመሩ ባንኮች ኃላፊዎችና ባንኮችን የሚቆጣጠረው የብሔራዊ ባንክ መሪዎች በአንድ ላይ የተሰባሰቡበት የተለየ አጀንዳ ነበረው፡፡ ብሔራዊ ባንክ እስከዛሬ ካወጣቸው መመርያዎቹ በተጨማሪ አዲስ መመርያ ስለማውጣቱ የሚመክር ስብሰባ አልነበረም፡፡ የግል ባንኮች ከሚሰጡት እያንዳንዱ ብድር ላይ 27 በመቶ ለቦንድ ግዥ የሚለውን መመርያ ብሔራዊ ባንክ እንዲያነሳ የሚጠይቅም አይደለም፡፡ ዜግነታቸውን የቀየሩ ባለአክሲዮኖች ጉዳይ ከአቅማችን በላይ ስለሆነ ብሔራዊ ባንክ በዚህ ጉዳይ ያወጣውን መመርያ ያንሳልን ለማለት የተገናኙበትም አልነበረም፡፡ ይልቁንም ለአንድ ባለሟል ዕውቅና ለመስጠት ታስቦ የተጠራ እንጂ፡፡
በቅርቡ ከብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥነታቸው በመልቀቅ፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክን እንዲመሩ የተሾሙትንና የባንኮች ማኅበር አባል መሆን ግድ የሚላቸውን አቶ ጌታሁን ናናን ለማመስገን፣ ለኢንዱስትሪው ዕድገት ላበረከቷቸው ሥራዎች ዕውቅና ለመስጠት የተሰናዳ ምሽት ነበር፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ ስለ ሥራው በዚህ ደረጃ ዕውቅና የተሰጠው ሰው ከዚህ ቀደም አለመኖሩ የዕለቱን ዝግጅት ለየት አድርጎታል፡፡ እንዲህ ላለው ዓላማ ሁሉም የዘርፉ ተወናይ መሰባሰቡና በፕሮግራሙ ላይ በግልጽ ሲደረጉ የነበሩ ምክክሮች በራሳቸው ላለፉት 20 ዓመታት ያልታዩ በተቆጣጣሪውና በባንኮች መካከል ከዚህ ቀደም ከነበረው ይልቅ ጥሩ ግንኙነት እንዲፈጠር መንገድ የጠረገ ምሽት ስለመሆኑ በምሽቱ ከተሰጡ አስተያየቶች ለመገንዘብ ተችሏል፡፡
ለዓመታት በገዥ ሕጎችና በተገዥ ሕግ ተቀባይነት መካከል ሲታዩ ከነበሩ ክርክሮችና ሙግቶች ይልቅ ሲጓዙበት የነበረውን የቀደመ መንገድ በምልሰት እያዩ በነፃነት ሐሳብ ሲለዋወጡ መታየታቸውም አዲስ ነገር ተብሏል፡፡ በተቆጣጣሪውና በሚቆጣጠራቸው ባንኮች መካከል የነበረው ፍትጊያ ሁልጊዜም ጠጣር ቢሆንም፣ የአቶ ጌታሁን ናና ስንብት ግን በዝምታ አይታለፍም በማለት አክብሮት ዕውቅና መሰጠቱ በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ክሰተት ተብሏል፡፡
የዕለቱን ፕሮግራም ማዘጋጀት ያስፈለገበትን ምክንያት ለታዳሚዎቹ ያስተዋወቁት የኢትዮጵያ ባንኮች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ ሃባ፣ ከባንኮች ጋር የቅርብ ትስስር የነበራቸው አቶ ጌታሁንን ልናመሰግን ይገባል በማለት ከተለየዩ ባንኮች የቀረቡትን ሐሳቦች መነሻ በማድረግ ማኅበሩ የዕለቱን ፕሮግራም እንዳዘጋጀ ጠቅሰዋል፡፡ አቶ ጌታሁን ለአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ዕድገት ቦታ ያላቸው ሰው ስለመሆናቸው የተለያዩ አስረጂዎችን በማቅረብ አቶ አዲሱ መስክረዋል፡፡ ባንኮች አሁን ላሉበት ደረጃ መድረስ የአቶ ጌታሁን አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ያስረዱት አቶ አዲሱ፣ ዕውቅና እንስጣቸው የሚለው ሐሳብ የመነጨው ከሁሉም ባንኮች መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡
የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ተክለወለድ አጥናፉም ‹‹የባንኮች ኃላፊዎች አቶ ጌታሁንን ለማመስገን እንዲህ ያለ ደመቅ ያለ ነገር በማዘጋጀታችሁ አመሰግናለሁ፤›› በማለት ስለ አቶ ጌታሁን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ከአቶ ጌታሁን ጋር ለ27 ዓመታት አብረው እንደሠሩ፣ እንደ ሥራ ባልደረባና እንደ ጓደኛም በደንብ እንደሚተዋወቁ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አቶ ጌታሁን በቅንነትና በታማኝነት የፋይናንስ ዘርፉና የአገር ኢኮኖሚ እንዲያድግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደረገ ትልቅ ሰው ነው፤›› በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡ ‹‹በእኔ ዕምነት ከዚህ የበለጠ የሚገባው ሰው ነው፤›› ሲሉም ባንኮች ሲቋቋሙ የሚገዙበትን ሕግ ከማርቀቅ ጀምሮ የሠሩ፣ ከዚያም ባሻገር የፋይናንስ ኢንዱስትሪው አሁን ለደረሰበት ደረጃ እንዲበቃ የተጫወቱትን ሚና አስረድተዋል፡፡ በብሔራዊ ባንክ ቆይታቸው የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲፈጠር ጭምር በማድረግ አቶ ጌታሁን የተሳካ ሥራ መሥራታቸውን ገዥው አቶ ተክለወልድ ተናግረዋል፡፡
በማሳረጊያቸውም ‹‹ከአቶ ጌታሁን ጋር ተባብራችሁ እንደሠራችሁት ሁሉ ከአዲሱ ምክትል ገዥ ጋርም የበለጠ ተባብራችሁ እንደምትሠሩ ዕምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡ የተሰጣቸው ዕውቅና የሚገባቸው መሆኑን በመግለጽም አወድሰዋቸዋል፡፡ የባንኮች መሪዎች አስተያየትም ተመሳሳይ ሲሆን፣ የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ አሻራቸውን ያሳረፉ ሲሏቸው፣ አቶ ብርሃኑ ጌታነህ በበኩላቸው ዘርፉን ለማሳደግ የደከሙ በማለት ለመመካከርና ለመነጋገር ሁሌም በራቸው ክፍት እንደነበር ጠቅሰውላቸዋል፡፡
በሁሉም ዘንድ እንዲህ ያሉ ሰው ናቸው ለተባሉት አቶ ጌታሁን፣ ዕውቅና አሰጣጡ እናመሰግናለን በሚሉ ቃላት ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ የጣት ቀለበትና የገንዘብ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡ ይሁንና የባንኮች ማኅበር ለአቶ ጌታሁን የሰጠውን የገንዘብ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ለመግለጽ አልፈቀደም፡፡
አቶ ጌታሁን በዕውቅና አሰጣጡ ወቅት ንግግራቸውን የጀመሩት ‹‹እጅግ በጣም ከተደሰትኩባቸው ቀኖች አንዱ ነው ብል ማጋነን አይሆንም፡፡ እጅግ በጣም ነው የተደሰትኩት፡፡ ለዚህም የባንኩን ማኅበረሰብ በሙሉ በጣም አመሰግናለሁ፤›› በማለት ነበር፡፡
የግል ባንኮች ሲቋቋሙና የመንግሥት ባንኮች እንደ አዲስ ሲዋቀሩ፣ ከሱፐርቪዥን ጀምሮ በልዩ ልዩ ሥራዎች ተሳትፎ እንደነበራቸው በማስታወስ ‹‹የግል ባንኮች ተቋቁመው ድክ ድክ ከማለት አልፈው እያደጉ ለዛሬ መድረሳቸው የተለየ ስሜት ይፈጥራል፡፡ ዕድገታቸው ሲያስደስተኝ አንዳንዴ የሚፈጠረው ፍትጊያ ሲያመኝ ነበር፡፡ አንዳንድ ጊዜም በፍትጊያው መካከል እንዳይጎዱብኝ አቅፌ ለመከላከል እየሞከርኩ ቆይቻለሁ፤›› በማለት ለባንኮች የነበራቸውን ድጋፍ አውስተዋል፡፡
‹‹በ20 ዓመት ጊዜ ውስጥ ምንም ዓይነት የባንክ ውድቀት ወይም ችግር አለማጋጠሙ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ይህ ለብሔራዊ ባንክ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በተለያዩ አገሮች ባንኮች ይወድቃሉ፣ ይነሳሉ፡፡ በእኛ አገር ውስጥ ግን ይህ አለመከሰቱ እጅግ አስደሳች ነው፤›› ነው በማለት የገለጹት አቶ ጌታሁን፣ ወደፊትም የአገሪቱ ባንኮች ዕድገት ቀጣይነት ላይ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡
ቀጣዩ ውጥን
የዕለቱ ፕሮግራም በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጉልህ ሚና አላቸው ለተባሉት ሰው ዕውቅና ከመስጠት ባሻገር ለዘርፉ ዕድገት አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎች የሚታወሱበትና ዕውቅና መሰጠት ይኖርበታል የሚል ሐሳብ እንዲፈልቅ ያስቻለ ነበር፡፡
ከዚህ ቀደም በተለያዩ ምክንቶች ለዘርፉ ይደክሙ ለነበሩ ባለሙያዎች ምስጋና ለማቅረብ ያልተቻለ ቢሆንም የሐሙስ ምሽቱ ፕሮግራም ግን ይህ ዕድል እንዲፈጠር፣ ይህንንም ለማመቻቸት ኃላፊነቱን የባንኮች ማኅበር እንዲወስድ የቤት ሥራ የወሰደበት ሆኖ አልፏል፡፡
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ አዲሱ በቀረበው ሐሳብ መሠረት የሚመሩት ቦርድ በሐሳቡ መክሮ በጥንቃቄ ለመተግበር ምን ማድረግ እንዳለበት ወደፊት ምላሽ እንሰጥበታለን ብለዋል፡፡ የብሔራዊ ባንክ አመራሮችም እንዲህ ያለው የተፍታታና የተዝናና ፕሮግራም በቋሚነት እንዲኖር የበኩላቸውን ለማበርከት ቃል ገብተዋል፡፡
