Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

ንግድ ሚኒስቴር የንግድ ምክር ቤቶች የምርጫ ሕጋዊነት እንዲረጋገጥ አሳሰበ

$
0
0

ንግድ ሚኒስቴር የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ያካሄዷቸው ምርጫዎች ሕጉን ተከትለው የተካሄዱ መሆናቸው እንዲረጋገጥና የዘገየውም የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር  ቤት ጠቅላላ ጉባዔና ምርጫም በዚሁ መሠረት እንዲካሄድ አሳሰበ፡፡

      በሚኒስቴሩ የንግድና የአክሲዮኖች ዘርፍ ማኅበራት ጉዳዮች ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በአቶ ኑረዲን መሐመድ ተጽፎ የወጣው ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና በተዋረድ የሚገኙ ምክር ቤቶች ሕጉን ተከትለው ምርጫ ማከናወናቸውን በቅድሚያ የማረጋገጥ ሥራ ከተሠራ በኋላ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ምርጫና ጉባዔ እንዲካሄድ ጠይቋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ የንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በተለያዩ ምክንያቶች መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በማካሄድ ፕሬዚዳንትና የቦርድ አመራር አባላት ምርጫ ያላካሄደ መሆኑ ይታወቃል፤›› በማለት የሚጀምረው ይኸው ደብዳቤ፣ የምርጫ አሠራርና ደንብን ያልተከተሉ የአሳታፊነት ጉድለት የሚስተዋልባቸው ምርጫዎች በየደረጃው ተከናውነዋል ሲል ከዚህ ቀደም የቀረቡ አቤቱታዎችን ዋቢ አድርጓል፡፡

‹‹በተለይም ክልሎችና የከተማ አስተዳድሮች እንዲሁም ሌሎች አባል ምክር ቤቶች ምርጫ ሳያካሂዱ ወደ ቀጣዩ እርከን ነባር አመራር ይዘው የሚቀርቡባቸው ምርጫዎች እየተከናወኑ ነው በማለት የተለያዩ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች እየቀረቡ ይገኛሉ፤›› በማለት የሚጠቅሰው የሚኒስቴሩ ደብዳቤ፣ ለቅሬታዎቹ አስፈላጊው መፍትሔ እንዲሰጣቸው በማለት ምክር ቤቶችን ጠይቋል፡፡

በንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 341/1995 እንዲሁም ከምክር ቤቱ መተዳደሪያ ውጭ ከሁለት ጊዜ በላይ የተመረጡ የቦርድ አመራር አባላት አሉ ተብሎ የቀረበው ቅሬታና አቤቱታም አስፈላጊ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ በማሰባሰብ ጉዳዩ እንዲጣራ ንግድ ሚኒስቴር ጽፏል፡፡

ሁሉም አባል ንግድና ምክር ቤቶች በአዋጁና በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት በየደረጃቸው በሕጋዊ መንገድ ምርጫ ያላከናወኑ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ሌሎች አባል የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ሕጉን ተከትለው ግልጽ፣ ፍትሐዊና አሳታፊ ምርጫ ስለማከናወናቸው የማረጋገጥ ሥራ እንዲሠራም አሳስቧል፡፡

የማጣራቱ ሥራ በየክልሉ ንግድ ቢሮዎች ድጋፍ ከተሠራ በኋላ የአገራዊ ንግድ ምክር ቤቱን መደበኛ ጉባዔና ምርጫ ማካሄድ እንደሚገባ የዳይሬክተሩ ደብዳቤ ጠቅሷል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መስከረም መጨረሻ ላይ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ይዞት የነበረውን መርሐ ግብር፣ የቦርድ አመራር አባላት ያጋጠሙኝ ችግሮች አሉ በማለት ምርጫና ጠቅላላ ጉባዔውን ማራዘሙ ይታወሳል፡፡

ተፈጠሩ ከተባሉ ችግሮች ውስጥ ሕግን መሠረት በማድረግ ከሥር ጀምሮ መደረግ የነበረባቸው ምርጫዎች ከሕግ ውጭ መከናወናቸው፣ በተደጋጋሚ በንግድ ምክር ቤቱ አመራር ቦታ ላይ ለመውጣት ሕግን ያልተከሉ ምርጫዎች ተደርገዋል የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ እንቅፋት ሆኑብኝ ያላቸውን እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ ለማድረግ አጣሪ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡  ሰባት አባላት ያሉት ይህ ኮሚቴ ከሕግ ውጭ ተከናወኑ ያላቸውን ጉዳዮች ለማጣራት የሁለት ወራት ጊዜ ተሰጥቶታል፡፡ ኮሚቴው በሕወጥ መንገድ ተመረጡ የተባሉ የምክር ቤቶች አመራሮችን ጉዳይ የሚያይ ሲሆን፣ የደረሰበትን ውጤት ሪፖርት በማድረግ ጠቅላላ ጉባዔው እንዲካሄድ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኮሚቴው በማጣራቱ ሥራ ወቅት አቤቱታ የቀረበባቸው ጉዳዮች እርግጥ ተፈጽመው ከተገኙ ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ሕገወጥ ምርጫ ተከናውኗል በማለት ንግድ ሚኒስቴር ድረስ አቤቱታ ከቀረበባቸው መካከል የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት፣ የአማራ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ይገኙባቸዋል፡፡

ከአቤቱታዎቹ መካከል በሚመሯቸው ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ከተቀመጠው መመርያ ውጭ ከስምንት ዓመታት በላይ በብቸኝነት ፕሬዚዳንት ሆነው የዘለቁ ግለሰቦች መኖራቸው አግባብ አይደለም የሚለው ሚዛን ደፍቷል፡፡

 

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles