የግብርና ውጤቶችን በማቀነባበር ሥራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች የውጭ ምንዛሪ እጥረት ማነቆ እንደፈጠረባቸው ገለጹ፡፡ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ ፋብሪካዎቹ የማምረቻ ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ ለማስገባትም ሆነ፣ ያመረቱትን ወደ ውጭ ለመላክ የሚውሉ እንደማሸጊያ ያሉ ግብዓቶችን ከውጭ ለማስገባት እንቅፋት እንደፈጠረባቸውና ሙሉ አቅማቸውን ከመጠቀም እንደገታቸው አስታውቀዋል፡፡
በሥራቸው ላይ እክል የሆነባቸውን ችግር እንደሚፈልጉት መጠን እንዳይሠሩ እንዳገዳቸው ቅሬታቸውን የገለጹት ኩባንያዎች፣ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ከዓመት ላላነሰ ጊዜ ወረፋ የሚጠብቁበት ሁኔታ መኖሩ እንዳማረራቸውና አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡
በሞያ ፉድ ኮምፕሌክስ የሽያጭና ግብይት ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ መገርሳ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ እንዳይሠራ እንዳገደው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ አራት ዓይነት ጣዕም ያላቸው ብስኩቶችን አምርቶ ለገበያ ያቀርባል፡፡ ማሸጊያና የተለያዩ ቅመሞችን የሚያስመጣውም ከአውሮፓ ነው፡፡ የምርቶቹን ዓይነት ለመጨመር ፍላጎት ቢኖረውም በተጋረጠበት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ የምርት መጠኑን መጨመር ቀርቶ የነበሩትንም የምርት ዓይነቶች ለማስቀጠል እንደተቸገረ ገልጸዋል፡፡
በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ለተለያዩ የምርት ሥራዎች የሚውሉ ኬሚካሎች፣ ማሸጊያዎችና የመሳሰሉትን ጥሬ ዕቃዎች ከውጭ በሚያስመጣው በትንሳዔ ኢንተርናሽናል የቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ኃላፊ አቶ ብሩክ ሞገስም ኩባንያው ስለሚገኝበት ችግር እንዲህ ብለዋል፡፡ ‹‹ድርጅቱ ዕቃዎቹን የሚያስመጣው ከስዊዘርላንድ ነው፡፡ አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ዕቃዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እየተቸገርን ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ የምናገኘው ጥያቄ ባቀረብን በዓመቱ ነው፡፡››
እንጀራና ሌሎችም ምግብ ነክ ነገሮችን ወደ ውጭ የሚልኩ ድርጅቶችም ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ ለመላክ ደረጃውን የጠበቀ ማሸጊያ እንደሚያስፈልጋቸው፣ ነገር ግን ባለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሚፈልጉትን ለማግኘት እየተቸገሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ይህንን ያሉት አራተኛው አዲስ አግሮ ፉድ ዓለም አቀፍ የግብርናና የግብርና ማምረቻ ቁሳቁሶች፣ የምግብና ምግብ ነክ ዕቃዎች እንዲሁም የማሸጊያ ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ዓርብ ኅዳር 23 ቀን 2009 ዓ.ም. በኤግዚቢሽን ማዕከል በተከፈተበት ወቅት ነው፡፡
በኤግዚቢሽኑ ላይ ከ60 በላይ የሚሆኑ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከቱርክ፣ ከኤንዶኔዥያ፣ ከቻይና፣ ከህንድና ከአፍሪካና ከሌሎችም አገሮች የመጡ የውጭ ኩባንያዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የአገር ውስጥ ተቋማትም ተሳታፊ ናቸው፡፡
ኤግዚቢሽኑን ያዘጋጁት ኢትኤል አድቨርታይዚንግ፣ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖችና ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት ከሚታወቀው የቱርኩ ላዲን ኢንተርናሽናል ፌር ኤንድ ኮንግረስ ጋር በመተባበር ነው፡፡ የኢትኤል አድቨርታይዚንግ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት ሃይማኖት ተስፋዬ እንደምትለው፣ የኤግዚቢሽኑ ዋና ዓላማ በውጭ አገሮች ያሉ በግብርናና በግብርና ምርቶች ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንዲሠሩ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲፈጠርና የገበያ ትስስር እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ እስከ ሰኞ ኅዳር 26 ቀን የሚቆየውን ኤግዚቢሽኑን የከፈቱት በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ፋቲህ ኡሎይ ናቸው፡፡
