በብርሃኑ ፈቃደ
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፋብሪካ አቋቁመው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ ሞባይል አምራች ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ እንዲልኩ መንግሥት ጫና ማሳደር መጀመሩ ሥጋት እንዳሳደረባቸው ገለጹ፡፡
አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ከሰጡት መካከል አንዱ የሆነውና በኢትዮጵያ የሞባይል ስልኮችን መገጣጠም ከጀመረ አምስት ዓመታትን ያስቆጠረው ስማድል ኩባንያ፣ መንግሥት ወደ ውጭ ኤክስፖርት አድርጉ በማለት ጫና ማሳደሩ ሥጋት እንደፈጠረበት አስታውቋል፡፡
ኩባንያው በሰጠው ማብራሪያ መሠረት ምንም እንኳ እንደ ቴክኖ ሞባይል ያሉ ኩባንያዎች በሌሎች አገሮች ካሏቸው እህት ኩባንያዎች አኳያ ምርታቸውን ወደ ውጭ መላክ ቀላል ቢሆንላቸውም፣ መቶ በመቶ ከውጭ በሚገባ ጥሬ ዕቃና ማቴሪያል ላይ በተመሠረተ የምርት ሥርዓት፣ በአንጻራዊነት ውድ በሆነው የአውሮፕላን ትራንስፖርት እንዲጓጓዝ በሚደረገው ገቢና ወጪ ጭነት እንዲሁም ለማግኘት አስቸጋሪ በሆነውና ብዙ መጠበቅን በሚጠየው የውጭ ምንዛሪ ዕጥረት፣ ከዚህም ባሻገር የሠራተኞች ምርታማነት ዝቅተኛነት ሳቢያ ሞባይል ስልኮች በኢትዮጵያ አምርቶ ለውጭ ገበያዎች ማቅረብ አዋጭ አለመሆኑን በመግለጽ ፋብሪካዎች ሥጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ሆኖም እንዲህ ያሉ ማነቆዎች ሳይፈቱና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን በማያመች የአመራረት ሥርዓት ውስጥ እንደገኛለን ያሉት ሞባይል አምራቾች፣ መንግሥት በኮታ አንዳንዶቹ ላይ የጣለው የአምስት ሚሊዮን ዶላር ኤክስፖርት ግብ ሥጋት አሳድሮብናል ብለዋል፡፡ በአንጻሩ እንደ ቴክኖ ሞባይል ያሉት ተቋማት በዓመት እስከ አሥር ሚሊዮን ዶላር ኤክፖስርት በማድረግ ከዘርፉ እጅግ የላቀ አፈጻጸም በማሳየት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ ቢባልም ግን ሌሎቹ አምራቾች ቴክኖ በሌሎች አገሮች ካሉት እህት ኩባንያዎቹ በሚያገኘው ተወዳዳሪ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ባሻገር በአገር ውስጥ ካለው የጠቅላላ እሴት ጭማሪ አሠራር አብዛኛውን ድርሻ በመያዝ ጭምር የበላይነቱን ይዟል፡፡
በአገሪቱ ዘጠኝ ያህል የሞባይል ስልክ መገጣጠሚያ ፋብሪካዎች እንዳሉ ሲታወቅ በጠቅላላው እሴት የሚጨምሩት አሥር ከመቶ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይሁንና ቴክኖ ሞባይል ከዚህ ውስጥ የስድስት ከመቶ ድርሻውን በመያዝ የበላይነቱን ይዟል፡፡ መንግሥት እሴት ለሚጨምሩና ወደ ውጭ ኤክስፖርት ለሚያደርጉ የሚሰጠውን ልዩ ልዩ ማበረታቻ ሊያጡ እንደሚችሉ ሥጋት የገባቸው አምራቾች፣ መንግሥት አቅማቸው በአግባቡ እስኪጎለብትና ተወዳዳሪነታቸው እስኪሻሻል ድረስ ማበረታቻዎቹን ከመስጠት መቆጠብ እንደሌለበት አምራቾቹ ይማጸናሉ፡፡
ይሁንና የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፊጤ በቀለ ግን ይህ ብዙም እንደማያስኬድ ይገልጻሉ፡፡ እንደ አቶ ፊጤ ማብራሪያ ከሆነ፣ መንግሥት ከመነሻውም ማበረታቻዎችን የሚሰጠው በኤክስፖርት መስክ አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ተቋማትን ለመደገፍ ሲል ነው፡፡
መንግሥት ሙሉ በሙሉም ባይሆን ከሚያመርቱት ጠቅላላ ምርት ውስጥ እስከ 20 ከመቶ ወደ ውጭ እንዲልኩ ማለቱን የጠቀሱት አቶ ፊጤ፣ ወደ ውጭ መላክ ፈተናው ብዙ በመሆኑ ከአሁኑ ይህንኑ መላመድ እንዲችሉና ወደፊት ከዚህም የባሰ ጫና ሳይመጣ ገበያውን እንዲቀላቀሉ መጣር እንደሚጠበቅባቸው አቶ ፊጤ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ጣና እንዲሁም ህዳሴ ቴሌኮምን ጨምሮ ቴክኖ ሞባይል፣ ስማድል፣ ኬሼንዳ፣ ኦኪን፣ ጂ ታይድ የተባሉትን ጨምሮ ዘጠኝ ያህል የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች በቀን ከ200 እስከ 20 ሺሕ የሞባይል ስልኮች የመገጣጠም አቅም እንዳላቸው ይገመታል፡፡
