የአቢሲኒያ ባንክ ባለአክሲዮኖች የባንካቸውን ካፒታል ወደ አራት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ከባንኩ አመራር የቀረበላቸውን ሐሳብ ተቀብለው አፀደቁ፡፡ ባለአክሲዮኖቹ ባለፈው ቅዳሜ ባካሄዱት ጠቅላላ ጉባዔ የባንኩን ካፒታል ወደ አራት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ መወሰናቸው፣ አቢሲኒያ ባንክን ከግል ባንኮች በተፈቀደ ካፒታል መጠን ከፍተኛውን ደረጃ እንዲያዝ ያደርገዋል፡፡
እስካሁን ድረስ ግን በተፈቀደም ሆነ በተከፈለ የካፒታል መጠን ቀዳሚውን ደረጃ የያዘው አዋሽ ባንክ የተፈቀደ ካፒታል መጠኑ 3.5 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 2.3 ቢሊዮን ብር በማድረስ ብልጫውን ይዟል፡፡
ካፒታሉን ወደ አራት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የወሰነው አቢሲኒያ ባንክ የተፈቀደ ካፒታሉ 2.1 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ 1.27 ቢሊዮን ብር ነው፡፡
አቢሲኒያ ባንክ አሁን ያለውን 1.27 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታሉን ወደ አራት ቢሊዮን ብር ለማድረስ ሲወስን፣ የተጠቀሰውን ካፒታል በአምስት ዓመታት ውስጥ ለመሙላት አቅዶ ነው፡፡ ይህንንም ባለአክሲዮኖች ተጨማሪ አክሲዮኖች እንዲገዙና ተጨማሪ አዳዲስ አክሲዮኖችን በመሸጥ ለመሙላት ታሳቢ የተደረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህ ውሳኔ ጎን ለጎን ባንኩ የዕለቱ ምሽት ላይ ለግብዣ ያውለው ነበር የተባለውን 500 ሺሕ ብር ለተለያዩ በጐ አድራጐት ድርጅቶች እንዲሰጥ ፈቅደዋል፡፡
ባንኩ በ2008 በጀት ዓመት ከአጠቃላይ ትርፉ ላይ የመንግሥት ግብርን ጨምሮ አስፈላጊ ቅናሾችን ካደረገ በኋላ 374.78 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ አግኝቷል፡፡ ከዚህ ትርፍ ላይ ለሕጋዊ መጠባበቂያ 93.94 ሚሊዮን ብርና ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የሚከፈለው ዓመታዊ ክፍያ ከተቀነሰ በኋላ 280.63 ሚሊዮን ብር የባንኩ ባለአክሲዮኖች ባላቸው የተከፈለ የአክሲዮን ድርሻ መጠን እንዲከፋፈሉም ውሳኔ ተላልፏል፡፡
ከዚህ ውሳኔ ቀደም ብሎ የባንኩን የ2008 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም የተመለከተ ሰፊ ሪፖርት ቀርቧል፡፡ ሪፖርቱ የአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ የጐላ ውድድር የታየበትና የአገልግሎት አድማሱም ከቀደሙት ዓመታት ፈጣን በሚባል ዕድገት የወጣ ስለመሆኑ ያመለክታል፡፡
በተለይም የባንኮች ተወዳዳሪነትና ህልውና የተመሠረተው በተቀማጭ ገንዘብ ላይ የሚያርፍ መሆኑን ያስታወሱት የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ መሠረት ታዬ፣ የተቀማጭ ገንዘብ በማሰባሰቡ ረገድ ባንካቸው ትኩረት ሰጥቶ በመሠራቱ አበረታች ውጤት አግኝቷል ብለዋል፡፡
እንደ ቦርድ ሰብሳቢው ሪፖርት የአቢሲኒያ ባንክ በበጀት ዓመቱ የተቀማጭ ገንዘቡ መጠን 13.63 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ከቀደመው በጀት ዓመት በ2.52 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ለተቀማጭ ገንዘብ ዕድገቱ እንዲወጣ የተለያዩ ጥረቶች የተደረጉ ሲሆን፣ በተለይ ለተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት ወሳኝ ሚና ይኖረዋል ተብሎ የሚታመነውን ቅርንጫፎች የማሳደግ ሥራ በመሠራቱ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡
በ2008 በጀት ዓመት ብቻ 53 አዳዲስ ቅርንጫፎች መክፈቱን የሚያመለክተው ሪፖርት፣ ይህም የባንኩን አስቀማጮች ቁጥር በ108 ሺሕ እንዲጨምር ማድረግ በመቻሉ ለተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ በአንድ ዓመት 108 ሺሕ አዳዲስ አስቀማጮች ማግኘት በመቻሉ ደግሞ፣ አጠቃላይ የአስቀማጮች ቁጥር በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ላይ ወደ 586 ሺሕ ከፍ አድርጎታል፡፡
‹‹የተረጋጋ በቂ ተቀማጭ ገንዘብ ያለው ባንክ በዘርፉ ጥሩ ተፎካካሪ መሆን የገበያውን ድርሻ የመቆጣጠር ዕድሉ ሰፊ ነው ተብሎ ይታመናል፤›› ያሉት አቶ መሠረት፣ ባንካቸው ይህንን በማድረጉ የተሻለ ውጤት ቢያስመዘግብም በአዲሱ በጀት ዓመት የተቀማጭ ገንዘብ የማሰባሰቡ ግብ የተለጠጠ በመሆኑ ፈተና ይሆናል ብለዋል፡፡
ባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ለማሳደግ የተጣለውን ግብ ለማሳካት ጥረቱ የሚቀጥል ቢሆንም፣ የባንኩ አጋሮች ድጋፍ እንደሚያሻቸው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ረገድ ሊገጥም የሚችለውን ፈተና ለማለፍ ‹‹የባንኩ አጋሮችና ደጋፊዎች ሁሉ የራሳችሁን ገንዘብ በባንካችሁ ውስጥ እንድታስቀምጡ፤›› በማለት ባለአክሲዮኖችን እስከማሳሰብ መድረሳቸው የተቀማጭ ገንዘብ አሰባሰቡ ውድድር ከፍተኛ ስለመሆኑ የሚጠቁም ሆኗል፡፡
የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙሉጌታ አስማረ በበኩላቸው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽነታቸውና የተቀማጭ ገንዘብ የማሰባሰብ ጥረታቸው ይቀጥላል ብለዋል፡፡ በዕቅድ ዘመኑም መንግሥት በፋይናንስ ተቋማት በኩል ከ1.8 ትሪሊዮን ብር በላይ የተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ ማቀዱንም ገልጸዋል፡፡
አቢሲኒያ ግን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የብድርና ቅድሚያ ክፍያዎች መጠን ወደ ስምንት ቢሊዮን ብር ያደገ መሆኑን የሚያሳየው ሪፖርት፣ ካለፈው ዓመት አኃዝ ጋር ሲነጻጸርም የ2.1 ቢሊዮን ብር ብልጫ ወይም የ35 በመቶ ዕድገት ነው፡፡ አቶ ጌታቸው እንደገለጹትም የባንኩ የተበላሸ ብድር መጠን ከሁለት በመቶ በታች ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ 1.74 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ ማግኘቱን የሚያሳየው ሪፖርት፣ ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ37 በመቶ ወይም 468 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡
የውጭ ምንዛሪ የገንዘብ ግኝትን በተመለከተም በተሰጠው ማብራሪያ፣ ባንኩ በበጀት ዓመቱ 7.3 ቢሊዮን ብር የውጭ ምንዛሪ ሲያገኝ፣ ይህ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከቀዳሚው ዓመት በ2.3 ቢሊዮን ብር ወይም በ45.7 በመቶ አድጓል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ ወጪ 1.26 ቢሊዮን ሆኖ እንደደረሰና ይህም ወጪ ካለፈው በጀት ዓመት ጠቅላላ ወጪ ጋር ሲነጻጸር 354.9 ሚሊዮን ብር ወይም የ39.33 በመቶ ብልጫ ነበረው ተብሏል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 487.23 ሚሊዮን ብር ማግኘቱን የሚያሳየው የባንኩ ሪፖርት፣ ይህም ከቀደመው ዓመት 113.27 ሚሊዮን ብር ወይም የ30.28 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ የገቢ ግብር፣ የሕጋዊ መጠባበቂያና ሌሎች ወጪዎች ከተቀናነሱ በኋላ የባንኩ የተጣራ ትርፍ 280.63 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ የተጣራ ትርፉ በ65.2 ሚሊዮን ብር ማደጉም አንድ መቶ ብር ዋጋ ያለው አንድ አክሲዮን የሚያስገኘው ትርፍ 31.54 ብር እንዲሆን አስችሏል፡፡
ባንኩ ጠቅላላ ሀብቱ በ23.14 በመቶ አድጎ 16.83 ቢሊዮን ብር ማድረሱን ገልጿል፡፡ ባንኩ በበጀት ዓመቱ ሥር ነቀል የሆነ ለውጥ ለማድረግ በማሰብ ዲሎይት (Deloitte) ከሚባል ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት አጠቃላይ ባንኩ ሲከተለው የነበረውን የአሠራር ዘዴና አደረዳጀት በአዲስ መልክ እንዲጠና መደረጉን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ባንኩ ዘመናዊ መገበያያ መሣሪያዎች (POS) የማሠራጨት ሥራ እያከናወነ ስለመሆኑ የሚያመለክተው የባንኩ ሪፖርት፣ ባለፈው በጀት ዓመት ቀድመው ከነበሩት 50 የኤቲኤም ማሽኖች በተጨማሪ 35 የኤቲኤም ማሽኖችንና 138 ዘመናዊ የመገበያያ መሣሪያ (POS) ገዝቻለሁ ብሏል፡፡ እነዚህንም የባንኩ ቅርንጫፎች በሚገኙባቸውና ታዋቂ በሆኑ የገበያ ማዕከሎች፣ ሆቴሎች፣ የገበያ መደብሮችና የነዳጅ ማደያዎች በሥራ ላይ አውሏል፡፡
በበጀት ዓመቱ መጨረሻም 41 ሺሕ 797 የሞባይል ባንክና 58 ሺሕ 359 የካርድ ባንክ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞችን አፍርቷል፡፡
