Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

የጃፓን መንግሥት ድጋፍ ሲያደርግበት የቆየውን የቡና ጥራት መፈተሻ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ አስረከበ

$
0
0

ከስምንት ዓመታት በፊት ወደ ጃፓን በተላከ ቡና ላይ የተገኘውን የፀረ ተህዋስያንና ፀረ አረም መከላከለያ ኬሚካል መነሻ በማድረግ የጃፓን መንግሥት ለኢትዮጵያ የኤክስፖርት ቡና ጥራት መፈተሻ የላቦራቶር ፍተሻ ማካሄጃ ፕሮጀክት ተክሎና ባለሙያዎችን መድቦ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያውያን ባለሙዎች እንዲመራ የሚችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱም ለኢትዮጵያ መተላለፉ ታውቋል፡፡

የግብርና ፀረ ተህስያንና ፀረ አረም መከላከያ ቅሪቶችን ለመመርመር የተዘረጋው ፕሮጀክት ከቀናት በፊት ለኢትዮጵያ መንግሥት በይፋ ተላልፏል፡፡ የጃፓን ዓለም ዓቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ለሪፖርተር በላከው መረጃ መሠረት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለጃፓን ባቀረበው የድጋፍ ጥሪ መሠረት ፕሮጀክቱ ተዘረግቶ ላለፉት ስምንት ዓመታት ሲተገበር ቆይቷል፡፡

በፀረ አረምና ፀረ ተባይ ኬሚካል ሳቢያ ጃፓን ትገዛ የነበረው ቡና ለተወሰነ ጊዜ ከተቋረጠ በኋላ መልሶ ማገገም ቢጀምርም እስካለፈው ሁለት ዓመት ድረስ ግን ቀድሞ ወደነበረበት ደረጃ ሊመለስ አልቻለም ነበር፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ጥራት ያለውና ከፍተኛ ደረጃ የተሰጠው ቡና ተብሎ የሚላከው ነገር ግን ጥራቱም ደረጃውም ዝቅተኛ ከሆነው ጋር እየተደባለቀ በመሆኑ የጥራት ጉዳይ አሁንም ድረስ አሳሳቢ መሆኑን ተሰናባቹ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ካዙሂሮ ሱዙኪ ሲገልጹ ይደመጡ ነበር፡፡ በዚህ ሳቢያም የሚፈለገውን ያህል ቡና ወደ ጃፓን መላክ ባይቻልችም በየጊዜው ግን እያደገ መምጣቱ ተነግሯል፡፡ የንግድ ሚኒስቴርም ሆነ የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ጃፓን በአሁኑ ወቅት ዋነኛ የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ከሆኑ ገበያዎች ተርታ መሰለፏን ነው፡፡

የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚጠቁመው በዓመት ከ170 እስከ 190 ሺሕ ቶን ቡና ለዓለም ይቀርባል፡፡ ከዚህ መጠን ውስጥ የጃፓን ድርሻ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በ10 በመቶ እንደማይበልጥ ይታወቅ ነበር፡፡ ይሁንና ባለፈው ዓመት ይህ አሐዝ 20 ከመቶ ላይ እያስመዘገበ፣ ከስምንት ዓመታት በፊት ወደነበረበት ደረጃ መመለሱን ሚኒስቴሩ አስታውቆ ነበር፡፡ ከስምት ዓመት በፊት፣ የኬሚካሉ ጉዳይ ከመከሰቱ ቀድሞ ወደ ጃፓን ይላክ የነበረው የቡና መጠን ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ኤክስፖርት ውስጥ እስከ 25 ከመቶ ይሸፍን እንደነበር ይታወቃል፡፡

የኬሚካል ንክኪውን ለማስቀረት የጃፓን ባለሙያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በጃፓን መንግሥት ድጋፍ የላቦራቶሪ ማዕከል ተቋቁሞ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ጥራት ያለው ቡና ከመደበኛው ቡና ጋር ተቀላቅሎ እየተላከ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያ ቡና የጃፓንን የጥራት ደረጃዎች ማሟላት ተስኖት እንደሚገኝ አሁንም ድረስ ቅሬታቸውን የሚያቀርቡት የጃፓን ባለሥልታናት አልታጡም፡፡  ይህ ቢስተካከል ግን ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ ጥራት ያላቸው ልዩ ቡናዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ አምባሳደር ሱዙኪ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያ ከጥሬ ቡና ባሻገር አገር ውስጥ የተቀነባበረ ቡና የመላክ ሐሳብ እንዳላት ያስታወሱት አምባሳደሩ፣ ይህንን ለማድረግ ግን አግሮፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪው መዳበር እንደሚኖርበት መጥቀሳቸው አይዘነጋም፡፡

ይሁንና ላለፉት ስምንት ዓመታት በጃፓናውያን ባለሙያዎች መሪነት ለኢትዮጵያውን ሲሰጥ የነበረው የጥራት ፍተሻ ሥልጠናና ቁጥጥር እንዲሁም ላቦራቶር አቋቁሞ ጥራትን የመፈተሻው ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት ለመንግሥት ተላልፎ ተሰጥቷል፡፡ የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርም ይህንን ፕሮጀክት ተረክቧል፡፡ የፕሮጀክቱ ዋናው ዓላማ በአብዛኛው የቡና ጥራት ፍተሻና ቁጥጥር መረጃዎችን በማጠናቀር ለጃፓን ተቆጣጣሪ አካላት መላክ ነበር፡፡ ከዚህ ባሻገርም የኢትዮጵያ ባለሙያዎችን በቡና ቁጥጥር መስክ ሲያሰለጥን ቆይቷል፡፡

ለፕሮጀክቱ በዋና አማካሪ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ጃፓናዊው ዮሺዮ ኢዛዋ በርክክቡ ወቅት እንዳሉት፣ ትግበራው ሲካሄድ የቀየው አምስት ዋና ዋና ውጤቶችን ለማስመዝገብ ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ቅድሚያ የሚሰጣቸው የግብርና ፀረ ተህዋስያንና ፀረ አረም ቅሪቶችን መከላከያዎች መለየት፣ የሚካሔዱ ምርምሮችን ማረጋገጥ፣ የትንተና መረጃ ማደራጀት የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በእስካሁኑ የፕሮጀክቱ አተገባበር 23 ዓይነት ጥሬ ቡና ላይ የሚታዩ ፀረ ተህዋስያንና ፀረ አረም መድኃኒቶችን ለመተንተን የሚያስችሉ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

ጃፓን ከአሜሪካና ከጀርመን ቀጥላ በዓለም ሦስተኛ ቡና የምትገዛ አገር ስትሆን፣ ከጣልያን፣ ከፈረንሳይና ከዩናይትድ ኪንግደም በመቅደም በቡና ጠጪነት ከሚታወቁት አገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡ ዩሲሲ ኩባንያ በበኩሉ በጃፓንና በእስያ ቡና ቆልቶ በማዘጋጀት ግንባር ቀደምነቱ ተቆናጧል፡፡ በዓለም ሰባተኛ ደረጃ መያዙን የኩባንያው ወኪሎች ይናገራሉ፡፡ በተለያዩ ዘዴዎች ቡና አዘጋጅቶ ለጃፓናውያን፣ ለእስያውያንና ለአውሮፓውያን የሚያቀርበው ይህ ኩባንያ ቡናን በዱቄትና በፈሳሽ መልክ እንደለስላሳ አሽጎ በማቅረብም ስሙ የሚጠራ ተቋም ነው፡፡ በጃፓን የቡና ማሠልጠኛዎችንና የቡና ሙዚየም ያለው ዩሲሲ፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በስፔን፣ በኔዘርላንድስ፣ በስዊዘርላንድና በፈረንሳይ አምስት የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች አሉት፡፡ ከተመሠረተ ሰማንያኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው ይህ ኩባንያ በሥሩ 62 ኩባንያዎችን በማቀፍ በዓመት 185 ሺሕ ቶን ቡና በማገበያየት የ2.8 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ ያከናውናል፡፡

 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles