Quantcast
Channel: አስተያየት
Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

የኤምሬትሱ ጁልፋር ኩባንያ የኢንሱሊን ማምረቻ በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው

$
0
0

- ለሄፒታይተስ ሲ በሽታ መድኃኒት ማምረት መጀመሩን አስታውቋል

ሥራ በጀመረ በሁለተኛ ዓመቱ የማስፋፊያ ግንባታ ለማካሄድ ከ12 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ ቦታ የተሰጠው የኢትዮጵያውያንና የኤምሬትስ ንጉሣውያን ቤተሰቦች ጥምረት የሆነውና መድኃኒት አምራቹ ጁልፋር ኢትዮጵያ ኩባንያ፣ በ50 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል በአፍሪካ ብቸኛውን የኢንሱሊን ማምረቻ ለመገንባት መዘጋጀቱን ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ የጁልፋር ኩባንያ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ሙከሚል አብደላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው በአብዛኛው የሚያመርታቸው መሠረታዊ መድኃኒቶች ሲሆኑ፣ የስኳር ሕመም መፈወሻ መድኃኒቶችን በማምረት የአገሪቱን ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር አብዛኛው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ከስኳር በሽታ ባሻገር ለሄፒታይተስ ሲ (በተለምዶ የጉበት በሽታ ወይም በልማድ የወፍ በሽታ) ሕክምና የሚውል አዲስ ምርት እዚሁ በማምረት ለገበያ ማዕቀረቡን አቶ ሙከሚል ገልጸዋል፡፡

እንደ አቶ ሙከሚል ማብራሪያ፣ የሄፒታይተስ ሲ መድኃኒት ከውጭ የሚገባ ከመሆኑም ባሻገር ለሦስት ወራት በተከታታይ የሚወሰደው የዚህ በሽታ መድኃኒት እስከ 1.5 ሚሊዮን ብር ወይም እስከ 84 ሺሕ ዶላር የሚገመት ገንዘብ እንደሚጠይቅ አብራርተው፣ ይሁንና ጁልፋር በአዲስ አበባ ያመረተው መድኃኒት በ25 ሺሕ ብር ለገበያ መቅረቡን ጠቅሰዋል፡፡ የሄፒታይተስ ሲ በሽታ ከ1 እስከ 6 ያሉ ልዩ ልዩ የበሽታው አመንጪ ጂኖ ታይፖች ሲኖሩት በኢትዮጵያ ጂኖ ታይፕ 1 እና 4 በስፋት የሚገኙ በመሆናቸው እነዚህን ጨምሮ ስድስቱም ለመፈወስ የሚያስችለው መድኃኒት በስፋት መመረት እንደሚጀመር ያብራሩት አቶ ሙከሚል፣ ምንም እንኳ መድኃኒቱ በዓለም የጤና ድርጅት የተመዘገበና የአዕምሯዊ ንብረት ባለቤትነት መብት ጥበቃ ቢኖረውም፣ ኢትዮጵያ የዓለም ጤና ድርጅት አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ፈራሚ ባለመሆኗ ምክንያት ጁልፋር ሊያመርተው እንደቻለ አቶ ሙከሚል አብራርተዋል፡፡  

የሕፃናትና የከፍተኛ ደረጃ ቃጠሎ ሕመምን ለማከም፣ የሕፃናት የሳምባ ምች መድኃኒትን ጨምሮ የደም ግፊት መቆጣጠሪያ፣ ፀረ ባክቴሪያዎች ማከሚያንና ሌሎችም በርካታ ከውጭ ይገቡ የነበሩ መድኃኒቶችን ለማምረት የሚያስችለውን የማስፋፊያ ፕሮጀክት በ18 ወራት ውስጥ እውን እንደሚያደርግ ኃላፊው አብራርተዋል፡፡ በአዲሱ ፋብሪካ፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ 10 ሚሊዮን ቫይል ኢንሱሊን እንደሚያመርትና ከዚህ ውስጥ ለውጭ ገበያ ስምንት ሚሊዮን ያህሉ እንደሚቀርብ አቶ ሙከሚል አስታውቀዋል፡፡ የአገር ውስጥ የኢንሱሊን ፍጆታ ከ1.5 እስከ ሁለት ሚሊዮን ቫይል እንደሚገመት ጠቅሰዋል፡፡

ከ8 እስከ 12 ሰዓት የሚያገለግለውንና ዴንቴ የተባለውን፣ ለአጭር ጊዜ የሚሰጠውን ወይም ሬጉላር የሚሰኘውንና የሁለቱም ቅልቅል የሆነውን ጨምሮ ሦስት ዓይነት የኢንሱሊን ምርት የሚያመርትበት ፋብሪካ በአፍሪካ ቀዳሚው እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ገርጂ ወደ ጃክሮስ መውጫው አካባቢ የተገነባው ጁልፋር መድኃኒት ማምረቻ ፋብሪካ፣ በዚሁ አካባቢ ተጨማሪ የማስፋፊያ መሬቱ ላይ ከሚያመርታቸውና ኢንሱሊንን ጨምሮ በመርፌ ወይም በደም ሥር በኩል የሚሰጡ ልዩ ልዩ መድኃኒቶችን አምርቶ ወደ ውጭ በመላክ በዓመት 20 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት አቅዷል፡፡ ይሁንና የኢንሱሊን ምርቱን በአገር ውስጥ ገበያ እንደ ልብ አምርቶ ለማቅረብ መንግሥት የመጀመሪያዎቹን ሦስት ዓመታት ቅድሚያ ለጁልፋር በመስጠት ምርቶቹን በመግዛት ዕድል እንዲጠሰው ጠይቆ ምላሽ እየተጠባበቀ እንደሚገኝም አቶ ሙከሚል ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መድኃኒት ፈንድ ኤጀንሲ በአገሪቱ ትልቁና ዋናው የመድኃኒት ግዥ ፈጻሚ ሲሆን፣ በዓመት በአማካይ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚወጡ መድኃኒቶችን በመግዛት እንደሚያቀርብ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ጁልፋርን ጨምሮ አብዛኞቹ መድኃኒት አምራቾችና አስመጪዎች በዚህ ተቋም ፍላጎት ላይ በመመሥረት እንደሚንቀሳቀሱና ዋናው የደም ሥራቸው መሆኑም ይነገርለታል፡፡

ጁልፋር ፋርማሲቱካል ኢንዱስትሪስ ግሩፕ (ገልፍ ፋርማሲቱካል ኢንዱስትሪስ) በሥሩ ካካተታቸው አንዱ ለመሆን የበቃውና አዲስ አበባ የከተመው ጁልፋር ፋርማሲቱካል ኩባንያ (ጁልፋር ኢትዮጵያ) በ40 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ገርጂ አካባቢ ሲገነባ፣ በዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ ንጉሣውያን ቤተሰቦችና በኢትዮጵያዊው የሜድቴክ ኢትዮጵያ ባለቤት ዶ/ር ሞሐመድ ኑሪ የጋራ ኢንቨስትመንት የተገነባ ነው፡፡

 ኩባንያው በንጉሣውያኑ የ55 በመቶ፣ በሜዲቴክ ኢትዮጵያ የ45 በመቶ ደርሻ 170 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት ተደርጎበት በአንድ ዓመት ውስጥ ተገንብቶ መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡ ጁልፋር የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያዎች አምራች ኩባንያ እንደመሆኑ፣ በኢትዮጵያ በሦስት ዓይነት መንገድ መድኃኒት ለማምረት የመጀመርያውን ምዕራፍ አጠናቆ ሥራ እንደጀመረ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ 25 ሚሊዮን የብልቃጥ ሽሮፕ፣ 500 ሚሊዮን ክኒንኖችና 200 ሚሊዮን ካፕሱል መድኃኒቶችን ለማምረት አቅም ያለው የቀድሞው ፋብሪካ ሥራ ለመጀመር ሲዘጋጅ፣ ከሰባቱ ኤምሬቶች የአንዱ ኤምሬት፣ የራስ አል ኬይማህ ገዥና የጁልፋር የቦርድ ሊቀመንበር፣ ሼክ ሳቅር ቢን ሞሐመድ አል ቃሲሚና የውጭ ንግድ ሚኒስቴሯ ባለቤታቸው ሼክ አሉብና አልቃሲሚ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከሁለት ዓመት በፊት አቀባበል የተደረገላቸው በወቅቱ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ እንደነበር አይዘነጋም፡፡

ሼክ ሳቅር ቢን ሞሐመድ አል ቃሲሚ በወቅቱ ሲናገሩ፣ ጁልፋር በኢትዮጵያ የተቋቋመው ኢትዮጵያን የአፍሪካ ማዕከል ለማድረግ በማሰብና፣ በመላ አፍሪካ ያለውን የገበያ ድርሻ በዚሁ በጁልፋር ኢትዮጵያ በኩል ለማዳረስ ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር አገራቸው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ለኢትዮጵያ ተምሳሌት የምትሆንባቸው መስኮች እንዳሉ፣ ከእነዚህ ውስጥም ኤርፖርቶች፣ ወደቦች፣ ሎጂስቲክስ፣ ቴሌኮሙኒኬሽንስ፣ ማኑፋክቸሪንግና ንግድ መስኮች ስኬታማ ታሪክ ስላላት ለኢትዮጵያ አብነት እንደምትሆን ንጉሣውያኑ ጠቅሰው እንደነበር ይታወሳል፡፡

ለመድኃኒቶቹ ማምረቻ የሚሆን ጥሬ ዕቃ ከውጭ የሚገባ ሲሆን፣ በአቅርቦት ረገድ ምንም ችግር እንደሌለበትም ኩባንያው አስታውቋል፡፡ ይሁንና በውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት መቸገሩ አልቀረም፡፡ ከዚህም ባሻገር ያቀረበው የማስፋፈፊያ ግንባታ ቦታ ጥያቄም ሲጓተት መቆየቱን ጠቅሷል፡፡ በአንፃሩ ግን ሥራ በጀመረ በዓመቱ ወጪውን መመለስ እንደቻለና በአሁኑ ወቅትም ትርፍ ገቢ በማግኘት ላይ እንደሚገኝ ያስታወቁት አቶ ሙከሚል፣ የኢትዮጵያ የመድኃኒት ገበያ ገና ያልተነካ ‹‹ድንግል ገበያ›› እንደሆነ ያምናሉ፡፡ የኩባንያው የኢትዮጵያ አፈጻጸም በሳዑዲ ዓረቢያ ካለው ፕሮጀክትም በመቅደም ጥሩ ውጤት እያሳየ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ላለፉት 25 ዓመታት የጁልፋርን መድኃኒቶች ከኤምሬትስ በማስመጣት የሚታወቀው ሜድቴክ ኢትዮጵያ፣ ከጁልፋር ጋር በእሽሙር ሽርክና ኢንቨስትመንት ውስጥ ከመግባቱ በፊት በያመቱ እስከ 12 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ መድኃኒቶችን ያስመጣ እንደነበር ይታወቃል፡፡

 ከሁለት ዓመት በፊት ሥራ ሲጀምር 170 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት የተደረገበት የምዕራፍ አንዱ ፋብሪካ ከሚያመርታቸው ባሻገር የሆኑትንና ለውጭ ገበያ ትኩረት የሚያደርግበትን የማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ለማካሔድ ከአዲስ አበባ አስተዳደር የ25 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ እስኪሰጠው እየተጠባበቀ እንደሚገኝ፣ መሬቱን ሲረከብም በሁለት ዓመት ውስጥ በ20 ሚሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚገነባ አስታውቆ ነበር፡፡ ይሁንና ከጠየቀው መሬት ውስጥ በአሁኑ ወቅት 12 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ በማግኘቱ፣ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ወጪውን ወደ 50 ሚሊዮን ዶላር ከፍ በማድረግ ለግንባታ ተዘጋጅቷል፡፡

ሥራ በጀመረበት ወቅት ለገበያ የሚቀርቡት የመድኃኒት ዓይነቶች 60 ያህል ነበሩ፡፡ በአብዛኛውም አንቲባዮቲክስ ላይ ያተኮሩና ከፍተኛ እጥረት አለባቸው ተብለው የሚታሰቡ እንደ ተላላፊ በሽታዎች መድኃኒት ምርት ላይ በማተኮር ሲሆን፣ ማስፋፊያው ሲጠናቀቅ የሚመረቱት መድኃኒቶች ቀድሞ በሜድቴክ ይመጡ ከነበሩ ከ243 መድኃኒቶች ውስጥ ከ80 እስከ 90 በመቶ በላይ እዚህ እንደሚመረት ይጠበቃል፡፡ አብዛኛውን ለውጭ ገበያ በማቅረቡ ላይ የሚያተኩረው የሁለተኛው ምዕራፍ ፕሮጀክት፣ ጁልፋር ገበያው በብዛት ያለው አፍሪካ ውስጥ በመሆኑ፣ ከዱባይ ከመላክ ይልቅ ኢትዮጵያን ማዕከል አድርጎ እንደ ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ናይጄርያ ያሉትን መዳረሻ ገበያዎች እንደሚያዳርስ ይጠበቃል፡፡ አይቪ ፍሉድ፣ ኬሞዲያሊሲስ፣ ኢንጄክቴብልስ፣ ስሞል ቮልዩም ፓረንታራልስና ሌሎች እስካሁን እዚህ የማይመረቱ መድኃኒቶችን ለማምረት መዘጋጀቱም ታውቋል፡፡  

ኤምሬቶች ለሚያካሂዱት የንግድና የኢንቨስትመንት ሥራ መንግሥት ተደራራቢ ቀረጥን ከማስቀረት፣ የኢንቨስትመንት ዋስትና ከመስጠት ባሻገር ከጁልፋር መድኃኒት ፋብሪካ የሚያገለግሉ ከ90 በላይ ልዩ ልዩ ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ዕድል መስጠቱ አይዘነጋም፡፡ ከዚህም ባሻገር በአሁኑ ወቅት ለጁልፋር የማስፋፊያ ግንባታ የተሰጠው መሬት ሌላ በጥቃቅንና አነስተኛ አምራችነት ተደራጅተው ሲሠሩ የነበሩ ወጣቶች የነበሩበት ቦታ ሲሆን፣ ምትክ ተሰጥቷቸው እንዲነሱ መደረጋቸውንና መሬቱም እጅጉን በወረደ ዋጋ በሊዝ እንደተሰጠው ለመረዳት ተችሏል፡፡ 12 ሺሕ ካሬ ሜትሩን በአምስት ሚሊዮን ብር እንዳገኘው የአቶ ሙከሚል ማብራሪያ ያስገነዝባል፡፡

ጁልፋር በአፍሪካ ደረጃ ለማከናወን ካሰባቸው ግንባታዎች መካከል የኢትዮጵያው ቀዳሚ ሲሆን፣ በመካከለኛው ምሥራቅ 12 ያህል የመድኃኒት ፋብሪካዎች ሲኖሩት፣ የመድኃኒት ጥሬ ዕቃዎችን በማምረትም በኤምሬትስ ብቸኛው ኩባንያ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1980 የተመሠረተው ጁልፋር፣ በ2011 ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ሽያጭ ያስመዘገበና ከ800 በላይ መድኃኒቶችን ያመረተ ዓለም አቀፍ ኩባንያ ነው፡፡ በኤምሬትስ ያሉትን 12 ፋብሪካዎች ጨምሮ በኢትዮጵያ፣ በሳዑዲ ዓረቢያና በአልጄሪያ ፋብሪካዎችን ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ በአፍሪካ የኢትዮጵያውን ጁልፋር ፋብሪካ ቀዳሚ ማድረጉም አይዘነጋም፡፡ 

 

Standard (Image)

Viewing all articles
Browse latest Browse all 720

Trending Articles