ስለአገሪቱ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ምርት ሲነሳ ስለመጫሚያዎች ማውራትና ማምረቻ ኢትዮጵያ ቀዳሚ ናት ከሚባትባልላት የቀንድ ከብት ሀብቷ የሚገኘው የቆዳና ሌጦ ምርትን በመጠቀም የሚፈበረከው የጫማ ምርትና የወጪ ንግዱን ለማሳደግ ያስችላል የተባለ የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ጽሑፋቸውን ያቀረቡ አካላት በጽሑፋቸው ውስጥ ካካተቷቸው ውስጥ ይኸው አገሪቷ አላት ተብሎ የሚታመነው የእንስሳት ሀብትን መጠንና ብዛት ደጋግመው ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያ እስከቅር ጊዜ ድረስ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም አሥረኛ ደረጃ ላይ የሚያስቀምጣት የቀንድ ከብት ክምችት እንዳላት ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የዓለም ደረጃዋ ወደ ስምንተኛነት ከፍ እንዳለ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተካሄደው ውይይት ወቅትም፣መረጃው ተጨባጭ መሆኑን የሚያረጋግጡ ሆነዋል፡፡ በአገሪቱ የጫማ የወጪ ንግድ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ጥሩ ዕድል እንደሚፈጥር ታምኖበት የተሰናዳው የጫማ ቢዝነስ ፎረም ወቅት መገንዘብ እንደተቻለው፣ አገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያላት የቀንድ ከብት፣ ፍየሎችና በጐች ብዛት በአሁኑ ወቅት ካለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ጋር የተስተካከለ አስመስሎታል፡፡ በመድረኩ የአገሪቱን የቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም አጠቃላይ ያላትን የኢንቨስትመንት ምቹነት የተመለከተ ገለጻ ያደረጉት የኧርነስት ኤንድ ያንግ የኢትዮጵያ ማኔጂንግ ፓርትነር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ ወቅታዊ መረጃዎችን አጣቅሰው እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ 52 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች፣ 22 ሚሊዮን ፍየሎችና 24 ሚሊዮን በጐች ያሏት አገር መሆኗን የሚያሳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቀዳሚ መሆኗን የሚያሳየው የእንስሳት ሀብት መጠን ግን በአግባቡ ያልተጠቀመችበት ሲሆን፣ የሀብቱ ብዛት ስም ብቻ አትርፎላት መቆየቱን እንጂ ብዙም እንዳልተጠቀመችበት የሚገልጹም አሉ፡፡ ይህ ሀብት ለአገር ውስጥ ፍጆታ ከሚውለው የሥጋ አቅርቦት ባሻገር ትርጉም የሚሰጥ፣ ፍሬያማ የወጪ ንግድ አቅም መፍጠር ቢያስችልም በተፈለገው ፍጥነት ግን አላደገም፡፡ በተለይ ከየትኛውም አገር በጥራትም በብዛትም የተሻለ ቆዳና ሌጦ የሚገኝባት ሆና ሳለ በኢንዱስትሪ ዘርፍ መገኘት ያለበትን ያህል ያለመገኘቱም ሲያስቆጭ ቆይቷል፡፡ ፋብሪካዎች ቆዳ አቀነባብረውና እሴት ጨምረው የመላክ አቅማቸው በብዙ ምክንያቶች ተገድቦ ቆይቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ ያለውን ሀብት በተመጠነ መልክ ለመጠቀም የተያዙ ዕቅዶችን ማሳካት ሳይቻል በርካታ ዓመታት አልፈዋል፡፡ መረጃዎች የሚያመለክቱትም የቆዳና የቆዳ ውጤቶች የውጭ ምንዛሪ ገቢ ዕድገት አዝጋሚ መሆኑን ነው፡፡
አገሪቱ ከቆዳና ከቆዳ ውጤቶች ታገኛለች ተብሎ ከተገመተው በታች ሆኖ መገኘቱ፣ የተቀመጠው ዕቅድ ሳንካ ያለበት ስለመሆኑ የሚያመላክት ነው፡፡ የ2008 በጀት ዓመት አፈጻጸሙ እንደሚያሳየውም ከአጠቃላይ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች 185 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንደሚገኝ ተጠብቆ የተገኘው ግን 116 ሚለዮን ዶላር ነው፡፡ የጫማ ዘርፍ የወጪ ንግዱ ተነጥሎ ሲታይም በበጀት ዓመቱ ከታቀደው በታች የውጭ ምንዛሪ እንዳስገኘ ታውቋል፡፡ ከዕቅዱ 79 ሚሊዮን ዶላር ቀንሷል፡፡ ከዚህ አንፃር አገሪቱ በእምቅ ሀብቷ መጠቀም አልቻለችም፡፡ መስከረም 19 ቀን 2009 ዓ.ም. በተካሄደው የውይይት መድረክ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ እንደገለጹት ግን የአገሪቱ ሀብት ጥሩ የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ እንዲሆን ዕድል እየተፈጠረለት ነው፡፡ የኢንተርፕራይዝ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ቴድሮስ ይልማ በበኩላቸው፣ ያለውን ዕድል ተጠቅሞ ለዘርፉ የተቀመጠውን ዕቅድ ማሳካት የሚቻልባቸው መንገዶች ይፈተሸሉ ብለዋል፡፡
የአሜሪካ ገዥዎችና በውይይት መድረኩ
የመጀመርያው የመጫሚያ ቢዝነስ ፎርም ‹‹The Source of Permium Duty Free Footwear Manufacturing›› በሚል ስያሜ ሐሙስ፣ መስከረም 19 ቀን የተደረገውን ውይይት በጥምረት ያዘጋጁት የኢንተርፕራይዝ ኢትዮጵያና የሶል ሬብልስ ኩባንያ ባለቤት በሆኑት በወ/ሮ ቤቴልሔም ጥላሁን አዲስ የተቋቋመው ሜደ ባይ ኢትዮጵያ ኩባንያ ጥምረት አማካይነት ነው፡፡
የአገሪቱን የጫማ ኤክስፖርት ለማሳደግ ምን መደረግ እንዳለበት ከተሰኑ ጉዳዮች አንዱ በዓለም ከሦስቱ ዋና ዋና ጫማ ገዥ አገሮች መካከል አንዷ የሆነችውን አሜሪካ በመሳብ ገዥ ኩባንያዎቿ ወደ ኢትዮጵያ እንዲያተኩሩ ማድረግ ነበር፡፡ በስብሰባውም የአሜሪካ ኩባንያዎች የተገኙበት ነበር፡፡ በአገሪቱ የጫማ ኩባንያዎች ማኅበር የተመራው ቡድንም የኢትዮጵያን ጫማ በይበልጥ እንዲሸምቱ ለማድረግ ታልሞ በተዘጋጀው መድረከ አገሪቱ ያላትን አቅም እንዲገነዘቡ የሚስችል ውይይት አካሄዷል፡፡
የአሜሪካ የጫማ ኩባንያዎችን ቡድን በመምራት የመጡ የአሜሪካ የጫማ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ማኅበር ቶማስ ፕሮኬት በዕለቱ ባደረጉት ገለጻ፣ ወክለው የመጡት ማኅበር ወደ አሜሪካ ከሚገባው ጫማ 80 በመቶውን የሚያስገቡ ኩባንያዎችን የሚወክል ነው፡፡ የማኅበራቸው አባላት እ.ኤ.አ. በ2015 ብቻ 2.6 ቢሊዮን ጥንድ ጫማዎችን ከተለያዩ አገሮች ወደ አሜሪካ እንዳስገቡ ገልጸዋል፡፡ ይህም ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ቡድን ዋነኛው የጫማ ገዥ ስለመሆኑ ያረጋገጠ ነበር፡፡ በመድረኩ የነበሩ ተሳታፊዎችም በአንድ ምርት እንዲህ ያለ ትልቅ ደረጃና አቅም ያለው የኩባንያዎች ልዑክ ከዚህ ቀደም አለመምጣቱን ይጠቅሳሉ፡፡ አቶ ዘመዴነህም ይህ አጋጣሚ ዳግም የማይገኝ ስለመሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡
የዓለም የመጫሚያ ገበያ እያደገ እንደሚገኝ ያመለከቱት ተወካዩ፣ ያለውን የጫማ ገበያ ለመጋራት ኢትዮጵያ ሰፊ ዕድል እንዳላት ገልጸዋል፡፡ እርግጠኛ በመሆንም የእነሱ እዚህ መጥቶ የዘርፉን እንቅስቃሴ መመልከት፣ የኢትዮጵያ ጫማ በአሜሪካ ገበያ ውስጥ እየሰፋ እንዲሄድ ለማድረግ የሚያስችል ስለመሆኑ የሚያመላክት ነው፡፡ ይህም ለአገሪቱ የጫማ ኢንዱስትሪ ትልቅ ተስፋ ተደርጓል፡፡ ከምክክር መድረኩ በፊት የአገሪቱን የጫማ ፋብሪካዎች በመጎብኘታቸውም አገሪቱ ያላትን አቅም እንዲገነዘቡ ማድረጉን በኢንተርፕራይዝ ኢትዮጵያ ኩባንያ የፕሮጀክት ኃላፊው አቶ ቴድሮስ ይልማ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በትልቁ ገበያ የኢትዮጵያ ድርሻ
የዓለም አቀፍ መጫሚያዎች ገበያን የሚቃኘው ዓመታዊ መጽሔት እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ. በ2010 የመጫሚያዎች ገበያ 227 ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ይህ ገበያ በ2013 ወደ 259 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ሲል፣ በ2015 ደግሞ ከ280 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል፡፡ አኃዛዊ መረጃው የዓለማችን የመጫሚያ ገበያ ከፍተኛ መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2018 ይኖራል ተብሎ የሚጠበቀው የገበያ ስፋት ወደ 331 ቢሊዮን ዶላር ከፍ እንደሚል ተተንብየዮዋል፡፡ ከዚህ ዓለም አቀፍ ገበያ ኢትዮጵያ ምን ያህሉን እንደ ያዘች ሲሰላ ግን ከቁጥር የሚገባ አይደለም፡፡ ሆኖም ሰፊ ዕድል እንዳላቸው ከሚነገርላቸው አገሮች መካከል አንዷ ነች፡፡ የኢትዮጵያን የመጫሚያ ምርት ወደ አሜሪካ ገበያ ለማስገባት ሰሞኑን ወደ ኢትዮጵያ የመጣውን ቡድን የመሩት ሚስተር ቶማስ፣ አሜሪካ በ2015 2.6 ቢሊዮን ጥንድ ጫማዎችን ከተለያዩ የዓለማችን አገሮች አስገብታለች፡፡ ከዚህ ውስጥ የቻይና ድርሻ ከ67 በመቶ በላይ ይደርሳል፡፡ ቬትናም ደግሞ ወደ 13 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ትወስዳለች ካሉ በኋላ ኢትዮጵያም የዚህ ተቋዳሽ እንድትሆን የሚያስችል ዕድል አላት ብለዋል፡፡
ከሦስት ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የተላከው 150 ሺሕ ጥንድ ጫማ እንደነበር ያስታወሱት ሚስተር ቶማስ፣ በአሁኑ ወቅት የሚላኩ ጫማዎች መጠን ወደ 1.2 ሚሊዮን ጥንድ ጫማዎች ደርሷል፡፡ ይህ ግን አገሪቱ ካላት ሀብት ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ተጠቅሷል፡፡
በዕለቱ በተደረገው ውይይት ወቅት ለአገሪቱ አዲስ ዕድል መገኘቱ አንድ ነገር ሆኖ የጫማ ገበያው ወደ ሌሎች አገሮች መስፋፋት እንደሚኖርበትም ተገልጿል፡፡ በዓለም የመጫሚያ ምርቶች ዓመታዊ መረጃ እንደሚያሳየው፣ በዓለማችን የጫማ ፍጆታ ቀዳሚ የሆነችው ቻይና ነች፡፡ አሜሪካ፣ ህንድ፣ ብራዚል፣ ጃፓን፣ ኢንዶኔዥያ፣ እንግሊዝ፣ ሩስያ፣ ጀርመንና ፈረንሣይ ከሁለት እስከ አሥረኛ ያለውን ደረጃ ይይዛሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የጫማ ምርቶች ከእነዚህ ገበያዎች አኳያ ብዙ መጓዝ የሚጠበቅበት ነው፡፡
በእርግጥ ቻይና ከዋነኞቹ የኢትዮጵያ የጫማ ምርት ገዥዎች አንዷ ብትሆንም የምታቀርባቸው ጫማዎች ብዛት አነስተኛ ነው፡፡ የቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት እንደገለጸው፣ በ2008 ዓ.ም. ወደ ቻይና የተላከው ጫማና የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከቀደመው ዓመት አኳያ ሲታይ አነስተኛ ነው፡፡
በሀብቱ ለመጠቀም ምን ይደረግ?
አቶ ዘመዴነህ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ ስለመሆኗ በዝርዝር ገልጸዋል፡፡ የዓለማችን ዝቅተኛው የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ የሚከፈልባት አገር መሆኗ አንዱ ነው መስኅብ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ አምርቶ መላክ አሜሪካ የምትሰጠውን ከኮታና ከታሪፍ ውጭ የሆነውን የነጻ ገበያ ዕድል ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡
ሌላው ምቹ ሁኔታ ብለው የጠቀሱት በቅርቡ ሙከራ የጀመረውና በሚመጣው ረቡዕ ተመርቆ ሥራ የሚጀምረውን ከአዲስ አበባ ጂቡቲ የሚዘልቀው የባቡር ትራንስፖርት ነው፡፡ ይህ ኢትዮጵያን ለኢንቨስትመንት የበለጠ ምቹ ያደርጋታል ብለዋል፡፡ በቆዳው ኢንዱስትሪም የጥሬ ዕቃው ምንጭ መሆኗን በማስታወስ ዘርፉ ያለውን ሰፊ ዕድል ኩባንያዎች ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አስታውሰዋል፡፡ የአሜሪካ ኩባንያዎች ባለፈው ረቡዕ ወደ 12 የጫማ ፋብሪካዎችን ጎብኝተው ያለውን ክፍተት ለመድፈን በጋራ እንደሚሠሩም ተናግረዋል ተብሏል፡፡
አብዛኞቹ የቆዳ ፋብሪካዎች የግብዓት ችግር እንዳለባቸው እየገለጹ ነው፡፡ በተለይም የጥሬ ቆዳ አቅርቦት ችግር እየታየ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የቆዳ ኢንዱስትሪዎች የቆዳና ሌጦ ግብዓት ችግር የገጠማቸው ጥራት የጎደለው ቆዳ ስለሚቀርብላቸው ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ በያመቱ አገሪቱ ልታመነጭ ከምትችለው ቆዳና ሌጦ ውስጥ ግማሽ ያህሉ የሚባክን በመሆኑ፣ ወደ ኢንዱስትሪዎች የሚላከው የቆዳና ሌጦ ምርት እንዲቀንስ ከማድረጉም በላይ ጥራት ላይ እክል እየፈጠረ ነው፡፡ ከኢንስቲትዩቱ የተገኘው መረጃም ይህንን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የመብራት መቆራረጥ ለዘርፉ ሌላው ፈተና እንደነበር ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
ተስፋ የተጣለበት ገበያ
የሰሞኑ የውይይት መድረክ ብዙ ተስፋ የሰነቀ ስለመሆኑ የተሰባሰበው አስተያየት ይገልጻል፡፡ ሚስተር ቶማስ ኢትዮጵያ መልካም ዕድል አላት ሲባል ያለምንክንያት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ወደ አሜሪካ ከሚያስገቡት የጫማ ምርት ውስጥ 67 በመቶው ከቻይና የሚገባ ቢሆንም ይህ የገበያ ድርሻ እየቀነሰ እንደሚመጣ ያምናሉ፡፡
ወደፊትም በቻይና የተያዘው ከፍተኛ ድርሻ ሲቀንስ እንደ ቬትናም ያለው ገበያ ይጨምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ለአሜሪካ ገበያ አቅራቢ የነበሩ ኩባንያዎች ማምረቻዎቻቸውን ወደ ሌላ አገር ያዛውራሉ ተብሎ ስለሚታመን ለኢትዮጵያ ዕድል እንደሚኖር የሚገለጸውን የሚረጋግጥ ነው፡፡ እንደ ኩባንያዎቹ ተወካዮች ገለጻ ከቻይና ወደ አሜሪካ የሚገባው የጫማ መጠን ወደ 55 በመቶ ይወርዳል፡፡ ይህ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው፡፡ አቶ ዘመዴነህም ይህንን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ በቻይና የሚመረተው የጫማ መጠን እየቀነሰ ሲሄድ ማምረቻዎቻቸው ወደ ሌላ አገር ይዛወራሉ፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡
አሁን ባለው ደረጃ አነስተኛ የሠራተኛ ደመወዝ ከሚጠየቅባቸው መካከል ኢትዮጵያ ተጠቃች ነች፡፡ በቻይና የሠራተኛ ደመወዝ በመጨመሩ የጫማ ፋብሪካዎች ለማስፋፋት ኢትዮጵያ ምቹ ነች፡፡ ተመራጭ በመሆኗም የአሜሪካውያን ኩባንያዎቹ መምጣትና በኢትዮጵያ ዘርፉን የሚያሳድጉ ዕድሎች እየተጠፈሩ መሄድ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ወደ አሜሪካ የሚላከው የጫማ መጠን በእጅጉ ይጨምራል ተብሎ እንዲጠበቅ አድርጓል፡፡ ከኩባንያዎቹ ጋር በተናጠል የተደረጉ ውይይቶችም ለዚህ ዋስትና ይሰጣሉ ተብሏል
ዛሬ ላይ የሚመሩት 1.2 ሚሊዮን ጥንድ ጫማዎች ወደ 20 ሚሊዮን ሊያድጉ የሚችሉበት ዕድል አለ የሚሉት አቶ ዘመዴነህ፣ ኩባንያዎቹም ያለውን ዕድል በደንብ እንደሚገነቡ ተስፋ ይደረጋል፡፡ አቶ ቴድሮስ እንደሚገልጹትም ይህንን ዕድል ለማስጠበቅ የማያቋርጥ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ ‹‹አሁን የተፈጠረውን ግንኙነት ወደ ውጤት ለመቀየር በዕለቱ የተደረሱ ስምምነቶችን በተግባር መለወጥን ይጠይቃል፡፡ ዕድሉ እንዳያመልጥ መሠራት አለበት፤›› ብለዋል፡፡ በቀጣዮቹ ሁለትና ሦስት ዓመታት ውስጥ ለአሜሪካ ከሚቀርበው ጫማ ውስጥ የኢትዮጵያ ድርሻ የጐላ እንደሚሆንም አቶ ዘመዴነህና ወ/ሮ ቤቴልሔም ይናገራሉ፡፡
እንደ ዝግጅቱ አስተባባሪዎች ከሆነ ውጤታማ የሆነ የቢዝንስ ድርድር የተደረገበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ ኩባንያዎቹ ከኢትዮጵያ ጫማ ለመግዛት መስማማት ብቻ ሳይሆን በዚህ መድረክ ብቻ 400 ሺሕ ጥንድ ጫማዎችን ከኢትዮጵያ ለመግዛት ማዘዛቸው መድረኩ ውጤታማ መሆኑን ያሳያል ተብሏል፡፡ የአሜሪካቹ ኩባንያዎች በዓመት አንድ ሚሊዮን ጥንድ ጫማ ከኢትዮጵያ ለመግዛት ከተደረሰው ስምምነት ውስጥ ከወዲሁ 400 ሺሕ ጥንድ ጫማ መታዘዙ በዚሁ መድረክ ብቻ የተፈጠረው የወጪ ንግድ ዕድል ‹‹በዕድገትና ትራንስፎርሜሸን የዕቅድ ዘመን የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ትልቅ መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል አቶ ቴድሮስ ተናግረዋል፡፡
የሜድ ባይ ኢትዮጵያ ዕቅድ በመጀመርያው ዓመት 250 ሺሕ ጥንድ ጫማዎችን መላክ ነበር፡፡ አጋጣሚ ሆነና 400 ሺሕ ጥንድ ጫማዎች ጥያቄ ፕሮግራም ላይ ቀርቧል፡፡ በቀጣዩ ዓመት አንድ ሚሊዮን ጥንድ ጫማዎችን መላክ ታስቦ የነበረ ሲሆን፣ ከወዲሁ 400 ሺሕ ጥንድ ጫማዎች ገበያ አኝግተዋል፡፡ በሜድባይ ውጥን መሠረት በሦተኛው ዓመት ላይ ሦስት ሚሊዮን፣ አራተኛው ዓመት ላይ አምስት ሚሊዮን ጥንድ አምስተኛ ዓመት ላይ ደግሞ አሥር ሚሊዮን ጥንድ ጫማዎች ለአሜሪካ ገበያ ለማቅረብ ነው፡፡ በሰሞኑ የምክክር መድረክ ላይ መገንዘብ እንደተቻለው ይህንን ውጥን በቀላሉ ለማሳካት የሚቻል ቢሆንም፣ ስኬቱ ግን አሁንም በርትቶ መሥራት ያሻል ብለዋል፡፡ ይህንን ውጥን የአሜሪካ ኩባንያዎች የሚደረስበት ነው ብለውታል፡፡ አቶ ቴድሮስ ደግሞ ይህንን ወጥ ለማሳካት የሚያስችል አቅም መኖሩን ገልጸው፣ በዚህ ገበያ ብቻ 200 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ይገኛል፣ ይኽም አሁን በአጠቃላይ ከዘርፉ በዓመት እየተገኘ ካለው የውጭ ምንዛሪ ጋር ሲነፃፀር በዚህ ፕሮግራም ብቻ የሚገኘው ብልጫ ያለው ያደርገዋል፡፡ ይህ የሚሆነው ግን ምርቱን በሰዓቱ ማቅረብ ሲቻል ነው፡፡ አቶ ዘመዴነህም ዕድሉን ለመጠቀም ካሉት መልካም ዕድሎች ሌላ አሁንም መሠረተ ልማቱን በማስፋፋት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ ከዘርፉ ይገኛል ተብሎ የተቀመጠው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 800 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡
