በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች በመሰማራት የሚታወቀው በላይ አብ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ከአምስት ዓመታት በላይ ሲገጣጥማቸው የነበሩ የቻይና አውቶሞቢሎችን መገጣጠም በማቆም፣ ኪያ የተባሉትን የኮርያ ሥሪት ተሽከርካሪዎች መገጣጠም ሊጀምር ነው፡፡ የኪያ የቤት አውቶሞቢሎችን ለመገጣጠም የሚያስችለውንም ስምምነት ባለፈው ሐሙስ በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል ተፈራርሟል፡፡
በበላይ አብ ሞተርስና በኪያ ሞተርስ መካከል የተደረሰውን ስምምነት አስመልክቶ ይፋ የተደረገው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በላይ አብ ሞተርስ በመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካው የኪያ ሞዴል ያላቸውን ሁለት የቤት አውቶሞቢሎችን በመገጣጠም ይጀምራል፡፡
የኪያ ሞተርስ ኮርፖሬሽን የመካከለኛው ምሥራቅና የአፍሪካ ፕሬዝዳንት ሚስተር ሶናም ሊ እንደገለጹት፣ ከበላይ አብ ሞተርስ ጋር በመስማማት በኢትዮጵያ ዕውን የሚሆነው የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው ነው፡፡
በስምምነቱ መሠረት ለኢትዮጵያ ገበያ ምቹ የሆኑ አዳዲስ ሞዴሎችንም የሚገጣጠሙ መሆኑን ሚስተር ሶናም ተናግረዋል፡፡ ናዝሬት የሚገኘው የበላይ አብ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካም የኪያ የቤት አውቶሞቢሎች የሚገጣጠሙበት ይሆናል፡፡ ከኪያ ጋር የተደረገውን ይህንን ስምምነት ተከትሎ በላይ አብ ሞተርስ ከአምስት ዓመታት በላይ ሲገጣጥማቸው የነበሩትን ፋው፣ ቬላ ሳሎንስ የተባሉ የቻይና ሥሪት የቤት አውቶሞቢሎችን መገጣጠም እንደሚያቆም የበላይ አብ ሞተርስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈቃዱ ግርማ ገልጸዋል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታት በላይ አብ ሞተርስ ከሦስት ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎችን ገጣጥሞ መሸጡን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የቻይናዎቹን ተሽከርካሪዎች የመገጣጠም ሥራን ቢቋረጥም የተሽከርካሪዎቹን መለዋወጫዎች ግን ለደንበኞቹ ማቅረብ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡ ኩባንያቸው ከቻይናው ኩባንያ ጋር የነበራቸውን ውል በማቋረጥ ወደ ኪያ ሞተርስ የተሸጋገረው፣ የተሻለ ገበያ ለማግኘት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
በርካታ ደንበኞች ከቻይና አውቶሞቢሎች ይልቅ እንደ ኪያ ያሉ ተሽከርካሪዎች ምርጫቸው እያደረጉ መሆኑም፣ የሚገጣጥሙትን የተሽከርካሪ ዓይነትና ሞዴል ለመለወጥ እንዳስገደዳቸው ከአቶ ፈቃዱ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በርካታ የቻይና የቤት አውቶሞቢሎች እንደሌሎች አገሮች ምርቶች በመኪና ገበያ ውስጥ ያላቸው የግብይት ሒደት የተለየ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የመኪና ገበያ የሚታየው የግብይት ሒደት ውስጥ እንደ ቶዮታ ያሉ ተሽከርካሪዎች አሮጌም ቢሆኑ መጀመሪያ ከተሸጡበት ዋጋ በላይ እየተሸጡ ነው፡፡ አንዳንድ የቻይና ሥሪት የሆኑ የቤት አውቶሞቢሎችን ግን ከዓመት በኋላ ቢሸጡ ከቀድሞው ዋጋቸውም በታች ዋጋ እየወጣላቸው ሆኖ መገኘት፣ አሁን በመኪና መገጣጠም ሥራ ላይ ያሉ ኩባንያዎች የሚገጣጥሟቸው የተሽከርካሪዎች ዓይነት ወደ ሌሎች አገሮች ምርት እንዲሄዱ እያስገደዳቸው ነው፡፡ አሁን ባለው ገበያ በኢትዮጵያ የሚገጣጠም አንድ የቤት አውቶሞቢል ከ300 እስከ 350 ሺሕ ብር ሲያወጣ፣ በተመሳሳይ የሚታዩና ከአሥር ዓመት በላይ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች 450 ሺሕ ብር እየተሸጡ መሆኑም በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ቻይና ሥሪት ተሽከርካሪዎች ላይ ተፅዕኖ ያሳርፋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ተሽከርካሪዎችን በመገጣጠም ላይ ከተሰማሩ ኩባንያዎች ውስጥ አብዛኞቹ የሚገጣጥሙት የቻይና ሥሪት ተሽከርካሪዎችን ነው፡፡ መስፍን ኢንጂነሪንግ በቅርቡ የፈረንሳይ ኩባንያ ምርት የሆኑትን ፔዦ ተሽከርካሪዎች መገጣጠም ከመጀመሩ በፊት፣ እንደ ጂሊ ያሉ የቻይና ተሽከርካሪዎችን ሲገጣጥም ቆይቷል፡፡ ኩባንያው አሁንም እነዚህን ተሽከርካሪዎች እየገጣጠመ ቢሆንም፣ ፊቱን ወደ አውሮፓ በማዞር የሚገጣጥማቸውን ተሽከርካሪዎች በቻይና ምርት ላይ ብቻ እንዳይወሰን እያደረገ ነው፡፡
ሌሎቹም የተሽከርካሪ መገጣጠሚያዎች የቻይናዎቹን ፋው፣ ቢዋይዲ፣ ሊፋንና የመሳሰሉትን በመገጣጠም የሚታወቁ ናቸው፡፡
አቶ ፈቃዱም በመኪና ግብይት ዙሪያ ያለውን የግብይት ሒደት ይስማሙበታል፡፡ ከቀድሞ የተሻለ ገበያ መፍጠር እንደሚቻል የሚገልጹት አቶ ፈቃዱ፣ የኪያ ተሽከርካሪዎች በአውቶሞቢል ገበያ ውስጥ ለውጥ ያመጣል ብለው ያስባሉ፡፡ የአገር ውስጥ መኪና መገጣጠሚያዎች ግን የገበያ ችግር ያለባቸው መሆኑን ይጠቁማል፡፡ ከተሽከርካሪ ገበያው በአገር ውስጥ የሚጣጠሙ ተሽከርካሪዎች የገበያ ድርሻ ከ15 በመቶ ያነሰ ነው፡፡
የአገሪቱ የመኪና ገበያ ውስጥ ብልጫ ያለውን ድርሻ የያዙት የጃፓን ሥሪት አውቶሞቢሎች እንደሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ዲሎይት የተባለው የአማካሪ ድርጅት አድራጎት በነበረ አንድ ጥናት፣ በዓመት ወደ 18 ሺሕ ተሽከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ይገባሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ ሰባት ሺሕ የሚሆኑት ያገለገሉ ስለመሆናቸው ጥናቱ ይጠቅሳል፡፡
ከአጠቃላይ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡት አሮጌም ሆነ አዲስ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 65 በመቶው የጃፓን ሥሪት ተሽከርካሪዎች ናቸው፡፡ በአገር ውስጥ የሚገጣጠሙ ተሽከርካሪዎች የገበያ ድርሻ 15 በመቶ አይበልጥም፡፡ በሥራ ላይ አሉ የሚባሉት ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያዎች በዓመት ስምንት ሺሕ ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም አቅም ያላቸው ቢሆንም፣ የሚገጣጥሙት ግን ከአቅማቸው በታች ነው፡፡
የመንግሥት ውጥን ግን አሁንም ተጨማሪ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያዎች የሚከፈቱ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በኪያና በበላይ አብ የመኪና መገጣጠም ሥራ ፊርማ ላይ የተገኙ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው ዶ/ር ዓለሙ ስሜ፣ በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል የተደረገው ስምምነት በኢትዮጵያ የተሽከርካሪዎች የመገጣጠም ሥራ ክህሎት እያደገ እንደሄደና ለዕውቀት ሽግግር ዓይነተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ ዘርፉም እያደገ ስለመምጣቱ ይጠቅሳሉ፡፡
በ300 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወደ ሥራ የገባው በላይ አብ ሞተርስ ከኪያ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት፣ የኪያ አውቶሞቢሎችን ለመገጣጠም 150 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት ያደርጋል፡፡
አቶ ፈቃዱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በስምምነታቸው መሠረት የኪያ አውቶሞቢሎችን የመገጣጠሚያ አካላትን ኪያ ሞተርስ ለበላይ አብ በሽያጭ ያቀርባል፡፡ በላይ አብ ሞተርስም የሎያሊቲ ሁለት በመቶ ይከፍላል፡፡
የኪያ ሞተርስ በኢትዮጵያ ውስጥ መገጣጠሙ በገበያ ውስጥ ለውጥ ሊያመጣ ይችል እንደሆነ ለቀረበ ጥያቄ አቶ ፈቃዱ፣ ‹‹አዎ ለውጥ ይመጣል›› በማለት መልሰዋል፡፡ መገጣጠሚያው ኢትዮጵያ ውስጥ መከፈቱ እስካሁን በቀጥታ ሲመጡ ከነበሩት የኪያ አውቶሞቢሎች ዋጋ ጋር ከ20 እስከ 25 በመቶ ቅናሽ ስለሚኖረው፣ በተሽከርካሪ ገበያ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ይላሉ፡፡
ሌላው እስካሁን በኢንዱስትሪ ውስጥ ባለው ልምድ በርካታ ደንበኞች በዱቤ መገበያየትን የሚመርጡ በመሆኑ፣ ይህንን ዓይነት ዕድል የሚሰጥ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
ከገበያው ውጭ ተሽከርካሪዎችን ከሚገጣጠሙባቸው የመኪና አካላት ውስጥ እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን በአገር ውስጥ ለመሸፈን ውጥን ያላቸውና ለዚህም ዝግጅት የሚደረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የበላይ አብ ሞተርስ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካው በቀን በአንድ ፈረቃ 12 ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም አቅም አለው፡፡ ከኪያ ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት በሁለት የኪያ የቤት አውቶሞቢሎች የሚጀመረው የመገጣጠም ሥራ፣ በዓመት ሦስት ሺሕ ተሽከርካሪዎችን ገጣጥሞ ለገበያ ያቀርባል ተብሏል፡፡
‹‹በዚህ ብቻ አንወስንም›› ያሉት የኪያ ሞተርስ የመካከለኛውና የአፍሪካ ፕሬዚዳንት፣ የኪያ ምርቶችን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎችን ከበላይ አብ ጋር እንሠራለን ብለዋል፡፡ ኪያ በአውቶሞቢል ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ የሚያመለክተው መረጃ፣ ኩባንያው በየዓመቱ የሚያመርታቸውን የተሽከርካሪዎች ቁጥር እያሳደገ መምጣቱን ነው፡፡ ምርቶቹ ያላቸው ተቀባይነት እያደገ በመምጣቱ በየዓመቱ ምርቱን ሊያሳድጉለት የሚችል የማስፋፊያ ሥራዎች እየሠራ ነው ይላሉ፡፡
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግን በአሁኑ ወቅት ያሉት የተሽከርካሪ መገጣጠሚያዎች በዓመት ስምንት ሺሕ ተሽከርካሪዎችን ለመገጣጠም አቅም ያላቸው ቢሆንም፣ እያመረቱ ያሉት ግን ካላቸው አቅም ከግማሽ በታች እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህ ከሆነ በላይ አብ የገበያ ችግር አይፈጥርበትም ወይ የሚል ጥያቄ ቢያስነሳም፣ ምርቶቹን ለመሸጥ የተሻለ ዕድል መኖሩን ተመልክቷል፡፡ አሁንም ቢሆን የአውቶሞቢል ገበያ ከፍተኛ ክፍተት ያለበት በመሆኑ፣ ይህንን ለመጠቀም ኪያ ጥሩ አጋጣሚ ነው ይላሉ፡፡
በዓለም አቀፍ የሞተር ኢንዱስትሪ ውስጥ እ.ኤ.አ. 2008 ጀምሮ ኪያ ሞተርስ በፍጥነት እያደገ የመጣ የመኪና ፋብሪካ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እንደመረጃው ኪያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመት 3.08 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎችን የማምረት አቅም አለው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2010 1.5 ቢሊዮን ዶላር የነበረው ሽያጩ፣ በአሁኑ ወቅት 5.7 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ በኢትዮጵያ የቤት አውቶሞቢሎችን በመገጣጠም ቀዳሚ ከነበረው ሆላንድ ካር በኋላ፣ የተለያዩ ኩባንያዎች ታዋቂ ከሆኑ የአውቶሞቢል አምራቾች ጋር በመዋዋል ተሽከርካሪዎችን እየገጣጠሙ ነው፡፡
